በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታምነው ነገር ለውጥ ያመጣል?

የምታምነው ነገር ለውጥ ያመጣል?

ሕይወት ዓላማ ያለው ይመስልሃል? ዊልያም ፕሮቫይን የተባሉት የዝግመተ ለውጥ አራማጅ “ስለ ዝግመተ ለውጥ ሂደት የተረዳነው ነገር ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው፤ ስለ ሕይወት ዓላማ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? “የጽንፈ ዓለምም ሆነ የሰው ልጆች መኖር ይህ ነው የሚባል ዓላማ እንዳለው አይሰማኝም” ብለዋል።32

ይህ አባባል ምን ትርጉም እንዳለው ልብ በል። ሕይወት ይህ ነው የሚባል ዓላማ ከሌለው በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ መልካም ተግባሮችን ለማከናወን ከመጣርና ምናልባትም ዘር ከመተካት ያለፈ ዓላማ አይኖርህም ማለት ነው። ስትሞት ደግሞ ለዘላለም ከሕልውና ውጭ ትሆናለህ። የማሰብ፣ የማመዛዘንና ስለ ሕይወት ዓላማ የማሰላሰል ችሎታ ያለው አንጎልህ ይህን ችሎታ ያገኘው እንዲሁ በአጋጣሚ ይሆናል ማለት ነው።

መች ይሄ ብቻ፤ በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አምላክ የለም፣ ቢኖርም በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም ብለው ያምናሉ። በዚህም ሆነ በዚያ የወደፊት ዕጣችን በፖለቲካና በሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በምሑራን እጅ ይወድቃል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ካሳለፉት ታሪክ አንጻር ሁኔታውን ስንመለከተው ደግሞ ለሰብዓዊው ማኅበረሰብ ነቀርሳ የሆነው ብጥብጥ፣ ግጭትና ሙስና እንዳለ ይቀጥላል ማለት ነው። በእርግጥም የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እውነት ከሆነ “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚለውን ተስፋ ቢስነት የሚንጸባረቅበት መርሕ ለመከተል በቂ ምክንያት ያለ ይመስላል።—1 ቆሮንቶስ 15:32

ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ “የሕይወት ምንጭ [ከአምላክ] ዘንድ ነው” ይላል። (መዝሙር 36:9) እነዚህ ቃላት በጣም ጥልቅ ትርጉም አላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው እውነት ከሆነ ሕይወት ዓላማ አለው ማለት ነው። ፈጣሪያችን ከፈቃዱ ጋር ተስማምተው ለመኖር ለመረጡ ሁሉ በፍቅር ተነሳስቶ ያዘጋጀው ዓላማ አለው። (መክብብ 12:13) ይህ ዓላማ ከብጥብጥ፣ ከግጭትና ከሙስና ነፃ በሆነ ሌላው ቀርቶ ሞት እንኳ በማይኖርበት ዓለም ውስጥ የመኖርን ተስፋ ያካትታል።—መዝሙር 37:10, 11፤ ኢሳይያስ 25:6-8

በእርግጥም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ስለ አምላክ መማርና እሱን መታዘዝ መሆኑን ማመናቸው የተገባ ነው! (ዮሐንስ 17:3) እንዲህ ያለው እምነት ዝም ብሎ በምኞት ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። ማስረጃው ግልጽ ነው፤ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው።