በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ ሃያ ሦስት

ይቅር ባይነትን ከጌታው ተምሯል

ይቅር ባይነትን ከጌታው ተምሯል

1. ጴጥሮስ በሕይወቱ ውስጥ በጣም ያዘነበት ቀን የትኛው ሳይሆን አይቀርም?

ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ዓይን ለዓይን ሲጋጩ የተሰማውን የሚረብሽ ስሜት መቼም ቢሆን አይረሳውም። ኢየሱስ እንዳዘነበት ወይም ቅር እንደተሰኘበት የሚጠቁም ነገር ከዓይኑ አንብቦ ይሆን? ይህንን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ “ጌታም ዞር ብሎ ጴጥሮስን አየው” ከማለት ውጭ ምንም አይናገርም። (ሉቃስ 22:61) ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የሠራው ስህተት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ዓይን ለዓይን በተጋጩበት በዚያች ቅጽበት መገንዘብ ችሎ ነበር። ጴጥሮስ የፈጸመው ድርጊት ልክ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረውን፣ እሱ ግን ፈጽሞ እንደማያደርገው ሲናገር የነበረውን ነገር መሆኑ ገብቶታል፤ አዎ፣ የሚወደውን ጌታውን ክዷል። በመሆኑም ይህ፣ ጴጥሮስ በሕይወቱ ውስጥ በጣም ያዘነበት ቀን ሳይሆን አይቀርም።

2. ጴጥሮስ ምን መማር አስፈልጎት ነበር? እሱ ያጋጠመውን ሁኔታ መመርመራችንስ ጥቅም ሊያስገኝልን የሚችለው እንዴት ነው?

2 ሆኖም ጴጥሮስ ከዚህ በኋላ ምንም ተስፋ የለውም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ጴጥሮስ ታላቅ እምነት ያለው ሰው በመሆኑ ስህተቱን አስተካክሎ ወደ ቀድሞው አቋሙ የመመለስና ኢየሱስ ካስተማራቸው ወሳኝ ትምህርቶች መካከል አንዱን ማለትም ይቅር ባይነትን የመማር አጋጣሚ ነበረው። ሁላችንም ይህን ትምህርት መማር ያስፈልገናል፤ እንግዲያው ጴጥሮስ ይህን ትምህርት እንዲማር ያስቻለውን በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ እስቲ እንመልከት።

ብዙ የሚማረው ነገር ነበር

3, 4. (ሀ) ጴጥሮስ ኢየሱስን ምን ጥያቄ ጠየቀው? ይህን ጥያቄ ሲጠይቅስ ምን አስቦ ሊሆን ይችላል? (ለ) ኢየሱስ በወቅቱ ሰፍኖ የነበረው መንፈስ በጴጥሮስ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ያሳየው እንዴት ነው?

3 ይህ ከመሆኑ ከስድስት ወራት ገደማ በፊት ጴጥሮስ በትውልድ ከተማው በቅፍርናሆም ሳሉ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” በማለት ጠይቆት ነበር። ጴጥሮስ ይህን ጥያቄ ሲያቀርብ ራሱን በጣም ይቅር ባይ እንደሆነ አድርጎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ደግሞም በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች አንድ ሰው ይቅርታ ማድረግ ያለበት ሦስት ጊዜ ብቻ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር! ኢየሱስ ግን “እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” በማለት መለሰለት።—ማቴ. 18:21, 22

4 ኢየሱስ ይህን ሲል ጴጥሮስ የደረሰበትን እያንዳንዱን በደል መመዝገብ እንዳለበት መናገሩ ነበር? በፍጹም፤ ጴጥሮስ 7 ጊዜ ይቅር ለማለት ሲጠይቅ ኢየሱስ 77 ጊዜ ይቅር ሊል እንደሚገባ መናገሩ ፍቅር ያለው ሰው የበደለውን ግለሰብ ይቅር ለማለት የተወሰነ ገደብ እንደማያወጣ የሚያሳይ ነው። (1 ቆሮ. 13:4, 5) ኢየሱስ በወቅቱ ሰፍኖ የነበረው ርኅራኄና ይቅር ባይነት የጎደለው መንፈስ በጴጥሮስም ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ጠቁሟል፤ በመዝገቡ ላይ ያሰፈረውን ሒሳብ እንደሚያወራርድ የሒሳብ ሠራተኛ በደልን የመቁጠር አዝማሚያ በብዙዎች ዘንድ ይታይ ነበር። አምላክ ግን ያለ ገደብ ይቅር እንድንል ይፈልጋል።—1 ዮሐንስ 1:7-9ን አንብብ።

5. ይቅር ባይነትን ይበልጥ የምንማረው መቼ ሊሆን ይችላል?

5 ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የሰጠውን ሐሳብ አልተቃወመም። ይሁንና የተሰጠውን ትምህርት ከልብ ተቀብሎ ይሆን? አንዳንድ ጊዜ ስለ ይቅር ባይነት ይበልጥ የምንማረው እኛ ራሳችን ይቅር መባል የሚያስፈልገን ሁኔታ ሲያጋጥመን ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የተከናወኑትን ሁኔታዎች እስቲ መለስ ብለን እንመልከት። በዚያ አስጨናቂ ወቅት ጴጥሮስ በርካታ ስህተቶችን ስለፈጸመ የጌታውን ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገው ነበር።

ብዙ ጊዜ ይቅር መባል አስፈልጎታል

6. ኢየሱስ ሐዋርያቱን ትሕትና ሊያስተምራቸው በሞከረ ጊዜ ጴጥሮስ ምን ምላሽ ሰጠ? ኢየሱስስ ምን አደረገ?

6 ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት የሚጠናቀቅበት ወሳኝ የሆነ ምሽት ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ሊያስተምራቸው የሚፈልገው ገና ብዙ ነገር የነበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዱ ትሕትና ነው። ኢየሱስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ በትሕትና ረገድ ምሳሌ ትቶላቸዋል፤ ብዙውን ጊዜ ይህ ሥራ የሚሰጠው ከአገልጋዮች መካከል ዝቅ ተደርጎ ለሚታየው ሰው ነው። ጴጥሮስ መጀመሪያ ላይ የኢየሱስ ድርጊት ትክክል መሆኑን እንደተጠራጠረ የሚያሳይ ነገር ተናገረ። ከዚያም እግሩን እንዳያጥበው ለመከላከል ሞከረ። በመጨረሻም እግሩን ብቻ ሳይሆን እጁንና ራሱንም ጭምር እንዲያጥበው ኢየሱስን ለመነው! በዚህ ወቅት ኢየሱስ ትዕግሥቱ አልተሟጠጠም፤ ከዚህ ይልቅ እግራቸውን ማጠቡ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያትና ይህን ማድረጉ ምን ትርጉም እንዳለው ረጋ ባለ መንፈስ ገለጸላቸው።—ዮሐ. 13:1-17

7, 8. (ሀ) ጴጥሮስ የኢየሱስን ትዕግሥት የተፈታተነው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የደግነትና የይቅር ባይነት መንፈስ ማሳየቱን የቀጠለው እንዴት ነው?

7 ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስ የኢየሱስን ትዕግሥት የሚፈታተን ሌላ ነገር አደረገ። ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ታላቅ ማን እንደሆነ መከራከር ጀመሩ፤ ኩራት በተንጸባረቀበት በዚህ አሳፋሪ ድርጊት ጴጥሮስም ተካፍሎ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን ኢየሱስ በደግነት እርማት የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ መልካም ጎናቸውን በመጥቀስ አመሰገናቸው፤ ሐዋርያቱ በታማኝነት ከጌታቸው ጎን ቆመዋል። ሆኖም ኢየሱስ ሁሉም ጥለውት እንደሚሸሹ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ሞትም እንኳ ቢመጣ ከኢየሱስ እንደማይለይ ገለጸ። ኢየሱስ ግን በዚያ ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ተናገረ። ይሁንና ጴጥሮስ ይህን ሐሳብ መቃወም ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹ ሐዋርያት ይልቅ እሱ ለጌታው ታማኝ እንደሚሆን በጉራ ተናገረ!—ማቴ. 26:31-35፤ ማር. 14:27-31፤ ሉቃስ 22:24-28፤ ዮሐ. 13:36-38

8 ኢየሱስ በጴጥሮስ ሁኔታ ትዕግሥቱ ተሟጥጦ ይሆን? በፍጹም፤ እንዲያውም በእነዚህ አስቸጋሪ ወቅቶች ሁሉ ኢየሱስ ፍጽምና የጎደላቸው ሐዋርያቱ ባላቸው መልካም ጎን ላይ ትኩረት አድርጓል። ጴጥሮስ እንደሚክደው ቢያውቅም እንዲህ አለው፦ “እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ፤ አንተም በተመለስክ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።” (ሉቃስ 22:32) በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ስህተቱን እንደሚያርምና እንደ ቀድሞው በታማኝነት ማገልገሉን እንደሚቀጥል ያለውን እምነት ገልጿል። እንዴት ያለ የደግነትና የይቅር ባይነት መንፈስ ነው!

9, 10. (ሀ) ጴጥሮስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ እርማት የሚያሻው ምን ስህተት ፈጽሟል? (ለ) የጴጥሮስ ሁኔታ ምን ያስታውሰናል?

9 ከዚያም በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ በነበሩበት ወቅት ጴጥሮስ በተደጋጋሚ ጊዜ እርማት የሚያሻው ድርጊት ፈጽሟል። ኢየሱስ በሚጸልይበት ወቅት ለጴጥሮስም ሆነ ለያዕቆብና ለዮሐንስ ነቅተው እንዲጠብቁ ነግሯቸው ነበር። ኢየሱስ እጅግ ከመጨነቁ የተነሳ ማበረታቻ ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ግን ከአንዴም ሁለቴ እንቅልፍ ጣላቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” በማለት ሁኔታቸውን እንደተረዳላቸውና ይቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ሐሳብ ተናገረ።—ማር. 14:32-41

10 ብዙም ሳይቆይ ችቦና ቆመጥ የያዙ እንዲሁም ሰይፍ የታጠቁ በርካታ ሰዎች መጡ። በዚህ ወቅት በጥንቃቄና በብልሃት መመላለስ ያስፈልግ ነበር። ጴጥሮስ ግን በችኮላ እርምጃ ወሰደ፤ ሰይፉን መዞ ማልኮስ የተባለውን የሊቀ ካህናቱን ባሪያ በመምታት አንዱን ጆሮውን ቆረጠው። ኢየሱስ በእርጋታ ጴጥሮስን ካረመውና የባሪያውን ጆሮ ከፈወሰ በኋላ ከዓመፅ መራቅ እንደሚያስፈልግ የሚገልጸውን ተከታዮቹ እስከ ዛሬ ድረስ የሚመሩበትን መሠረታዊ ሥርዓት ተናገረ። (ማቴ. 26:47-55፤ ሉቃስ 22:47-51፤ ዮሐ. 18:10, 11) ጴጥሮስ እስካሁን ድረስ ጌታው ይቅርታ እንዲያደርግለት የሚጠይቁ በርካታ ስህተቶችን ፈጽሟል። የእሱ ሁኔታ ሁላችንም ብዙ ጊዜ ኃጢአት እንደምንፈጽም ያስታውሰን ይሆናል። (ያዕቆብ 3:2ን አንብብ።) ከመካከላችን በእያንዳንዷ ዕለት የአምላክ ይቅርታ የማያስፈልገው ማን አለ? ጴጥሮስ በዚያ ምሽት የፈጸመው ስህተት ይህ ብቻ አልነበረም። ከዚህ የከፋም ነገር አድርጓል።

ከሁሉ የከፋው የጴጥሮስ ስህተት

11, 12. (ሀ) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከታሰረ በኋላ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ጴጥሮስ፣ ራሱ የተናገረውን ቃል ሳይፈጽም የቀረው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን ሰዎች የሚፈልጉት እሱን ከሆነ ሐዋርያቱን እንዲተዉአቸው ጠየቃቸው። ሰዎቹ ኢየሱስን ሲያስሩት ጴጥሮስ ቆሞ ከመመልከት ውጭ ምንም ማድረግ አልቻለም። ከዚያም እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ እሱም ጥሎት ሸሸ።

12 ጴጥሮስና ዮሐንስ መሸሻቸውን ያቆሙት ሐና የተባለው የቀድሞው ሊቀ ካህናት ቤት ጋ ሲደርሱ ሳይሆን አይቀርም፤ ኢየሱስም መጀመሪያ ላይ የተወሰደው ወደዚህ ቤት ነበር። ኢየሱስ ከዚያ ወደ ሌላ ቦታ ሲወሰድ ጴጥሮስና ዮሐንስ “በርቀት” ሆነው ይከተሉ ጀመር። (ማቴ. 26:58፤ ዮሐ. 18:12, 13) ጴጥሮስ ፈሪ አልነበረም። ምክንያቱም ኢየሱስ ወደሚወሰድበት ቦታ ተከትሎ መሄድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ድፍረት እንደሚጠይቅ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስን የያዙት ሰዎች መሣሪያ የታጠቁ ከመሆናቸውም ሌላ ጴጥሮስ ከእነሱ በአንዱ ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር። ያም ቢሆን ግን ጴጥሮስ እስከ ሞት ድረስ ለጌታው ታማኝ እንደሚሆን የተናገረውን ቃል ፈጽሟል ማለት አይደለም።—ማር. 14:31

13. ክርስቶስን በተገቢው መንገድ መከተል የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው?

13 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ልክ እንደ ጴጥሮስ ክርስቶስን “በርቀት” ማለትም ማንም ሳያውቅባቸው መከተል ይፈልጋሉ። ይሁንና ጴጥሮስ ራሱ በኋላ ላይ እንደጻፈው ክርስቶስን በተገቢው መንገድ መከተል የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ምንም ይምጣ ምን በሁሉም ነገር እሱ የተወውን ምሳሌ በመኮረጅ የቻልነውን ያህል እሱን በቅርብ መከተል ነው።—1 ጴጥሮስ 2:21ን አንብብ።

14. ጴጥሮስ የኢየሱስ ጉዳይ እየታየ በነበረበት ሌሊት ምን ሲያደርግ ነበር?

14 ጴጥሮስ ሰዎቹን በጥንቃቄ ሲከተል ከቆየ በኋላ በኢየሩሳሌም ከሚገኙት ትላልቅ ቤቶች ወደ አንዱ ደረሰ። ይህ ቤት ባለጸጋ የሆነውና ተደማጭነት ያለው የሊቀ ካህናቱ የቀያፋ ነበር። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉት ቤቶች ከፊት በኩል ትልቅ በር ያለው ግቢ ይኖራቸዋል። ጴጥሮስ የግቢው በር ላይ ሲደርስ እንዳይገባ ተከለከለ። ከሊቀ ካህናቱ ጋር የሚተዋወቀውና ግቢው ውስጥ ገብቶ የነበረው ዮሐንስ ወጥቶ በር ጠባቂዋን በማነጋገር ጴጥሮስን አስገባው። ከዚያ በኋላ ግን ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር አብሮ የቆየ አይመስልም፤ ወይም ደግሞ ከጌታው ጎን ለመቆም ሲል ወደ ቤት ውስጥ ለመግባት አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ በኢየሱስ ላይ የሚመሠክሩት ሐሰተኛ ምሥክሮች ችሎቱ ወደሚካሄድበት ቤት ሲገቡና ሲወጡ እየተመለከተ የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም እሳት ከሚሞቁት አንዳንድ ባሪያዎችና የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ጋር ግቢው ውስጥ ቆሞ ነበር።—ማር. 14:54-57፤ ዮሐ. 18:15, 16, 18

15, 16. ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ እንደሚክደው የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

15 ጴጥሮስን ወደ ግቢው ያስገባችው አገልጋይ ጴጥሮስ ወደ እሳቱ ብርሃን ሲጠጋ በደንብ አየችው። በዚህ ጊዜም ማንነቱን ስላወቀች “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርክ!” በማለት አጋለጠችው። ጴጥሮስ ያልጠበቀው ነገር ስለሆነበት ኢየሱስን እንደማያውቀው በመናገር ካደ፤ እንዲያውም ሴትየዋ ስለ ምን እያወራች እንደሆነ እንዳልገባው ተናገረ። ከዚያም ሰው እንዳይለየው በማሰብ ወደ ግቢው መግቢያ አካባቢ ሄደ፤ ያም ሆኖ አንዲት ሌላ ሴት አየችውና “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” በማለት ተመሳሳይ ነገር ተናገረች። ጴጥሮስም “ሰውየውን አላውቀውም!” በማለት ማለ። (ማቴ. 26:69-72፤ ማር. 14:66-68) ጴጥሮስ ዶሮ ሲጮኽ የሰማው ኢየሱስን በዚህ መንገድ ለሁለተኛ ጊዜ ከካደው በኋላ ሳይሆን አይቀርም፤ ይሁንና በጣም ተረብሾ ስለነበር ከተወሰኑ ሰዓታት በፊት ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ማስታወስ አልቻለም።

16 ይህ ከሆነ የተወሰነ ጊዜ ቢያልፍም ጴጥሮስ አሁንም ሰዎች ማንነቱን እንዳይለዩት ለማድረግ እየሞከረ ነበር። ሆኖም በግቢው ውስጥ ሰብሰብ ብለው ቆመው የነበሩ ሰዎች ወደ እሱ ቀረቡ። ከሰዎቹ መካከል አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው ማልኮስ የተባለው ባሪያ ዘመድ ነበር። እሱም ጴጥሮስን “በአትክልቱ ስፍራ ከእሱ ጋር አይቼህ የለም እንዴ?” አለው። ጴጥሮስም ሰዎቹ እንደተሳሳቱ ለማሳመን ይጥር ጀመር። በመሆኑም የተናገረው ነገር ውሸት ከሆነ እርግማን እንዲደርስበት በመግለጽ ሳይሆን አይቀርም መሃላውን ደረደረ። በዚህ መንገድ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለሦስተኛ ጊዜ ካደው። ጴጥሮስ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ በዚያ ሌሊት ዶሮ ለሁለተኛ ጊዜ ሲጮኽ ሰማ።—ዮሐ. 18:26, 27፤ ማር. 14:71, 72

“ጌታም ዞር ብሎ ጴጥሮስን አየው”

17, 18. (ሀ) ጴጥሮስ ጌታውን በጣም እንዳሳዘነው ሲገነዘብ ምን ተሰማው? (ለ) ጴጥሮስ ምን አስቦ ሊሆን ይችላል?

17 ኢየሱስ ልክ በዚህ ጊዜ ችሎቱ ከሚካሄድበት ክፍል ወጥቶ በረንዳው ላይ ቆመ፤ እዚያም ሆኖ በግቢው ውስጥ የሚከናወነውን ነገር ቁልቁል መመልከት ይችል ነበር። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ከጴጥሮስ ጋር ዓይን ለዓይን የተጋጩት በዚህ ጊዜ ነበር። በዚያች ቅጽበት ጴጥሮስ ጌታውን በጣም እንዳሳዘነው ተሰማው። ጴጥሮስ በጥፋተኝነት ስሜት ተውጦ ግቢውን ለቆ ወጣ። ከዚያም በማዘቅዘቅ ላይ ያለችው ጨረቃ በምትሰጠው ብርሃን እየተመራ ወደ ከተማዋ አውራ ጎዳናዎች አቀና። ዓይኖቹ እንባ አቀረሩ፤ የሚያየው ነገር ሁሉ ብዥ አለበት። ከዚያም ስሜቱ ፈንቅሎት ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።—ማር. 14:72፤ ሉቃስ 22:61, 62

18 አንድ ሰው እንዲህ ያለ ከባድ ስህተት መፈጸሙን ሲገነዘብ የሠራው ኃጢአት እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ይቅር ሊባል እንደማይችል ይሰማው ይሆናል። ጴጥሮስም እንዲህ ብሎ ሳያስብ አልቀረም። ይሁን እንጂ የሠራው ስህተት ይቅር የማይባል ነበር?

ጴጥሮስ የሠራው ኃጢአት ይቅር የማይባል ነበር?

19. ጴጥሮስ ስለሠራው ስህተት ምን ተሰምቶት መሆን አለበት? ሆኖም የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲቆጣጠረው እንዳልፈቀደ እንዴት እናውቃለን?

19 ጴጥሮስ ጎህ ከቀደደ በኋላ በቀኑ ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች ሲመለከት ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማው መገመት አያዳግትም። ኢየሱስ ያን ዕለት ከሰዓት በኋላ ብዙ ሲሠቃይ ቆይቶ ሕይወቱ ሲያልፍ ጴጥሮስ ምን ያህል በጸጸት ስሜት ተውጦ ይሆን! ጴጥሮስ፣ ጌታው ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ዕለት በሥቃዩ ላይ ሥቃይ እንደጨመረበት በማሰብ በቁጭት ሳይብሰለሰል አይቀርም። እርግጥ ነው፣ ጴጥሮስ በሐዘን ተውጦ የነበረ ቢሆንም የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም። ይህን የምንለው ብዙም ሳይቆይ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር መገናኘቱን እንደቀጠለ ዘገባው ስለሚናገር ነው። (ሉቃስ 24:33) ሁሉ ነገር የጨለመ በሚመስልበት በዚያ ሌሊት ባደረጉት ነገር ሐዋርያቱ በሙሉ ተቆጭተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ አንድ ላይ መሆናቸው በተወሰነ መጠንም ቢሆን እርስ በርሳቸው እንዲጽናኑ ረድቷቸው መሆን አለበት።

20. ጴጥሮስ ካደረገው ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ምን ልንማር እንችላለን?

20 ጴጥሮስ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ካደረገባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ይህ ነው ማለት ይቻላል። አንድ የአምላክ አገልጋይ በኃጢአት ሲወድቅ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ነገር ስህተቱ ምን ያህል ከባድ ነው የሚለው ሳይሆን ከወደቀበት በመነሳት ሁኔታዎችን ለማስተካከል ምን ያህል ጥንካሬ አለው የሚለው ነው። (ምሳሌ 24:16ን አንብብ።) ጴጥሮስ መንፈሱ ቢደቆስም ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር አብሮ በመሆን ጠንካራ እምነት እንዳለው አሳይቷል። አንድ ሰው በሐዘን ወይም በጸጸት ስሜት ሲደቆስ ቶሎ የሚቀናው ራሱን ማግለል ነው፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ አደጋ አለው። (ምሳሌ 18:1) ከዚህ ይልቅ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ተቀራርበን በመኖር መንፈሳዊ ጥንካሬያችንን መልሰን ለማግኘት መጣር የጥበብ አካሄድ ነው።—ዕብ. 10:24, 25

21. ጴጥሮስ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር በመሆኑ የትኛውን ዜና መስማት ቻለ?

21 ጴጥሮስ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር ስለነበር የኢየሱስ አስከሬን በመቃብሩ ውስጥ እንዳልተገኘ የሚገልጸውን አስደንጋጭ ዜና ሰማ። ከዚያም ጴጥሮስና ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ተቀብሮበት ወደነበረው ወደታሸገው መቃብር እየሮጡ ሄዱ። ወደ መቃብሩ ቦታ ቀድሞ የደረሰው ዮሐንስ ነበር፤ ከሁለቱ በዕድሜ የሚያንሰው እሱ ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም የመቃብሩ በር ተከፍቶ ሲያገኘው ለመግባት አመነታ። ጴጥሮስ ግን ከመሮጡ የተነሳ ትንፋሽ ቢያጥረውም እየተንደረደረ ወደ ውስጥ ገባ። መቃብሩ ባዶ ነበር!—ዮሐ. 20:3-9

22. በጴጥሮስ ልብ ውስጥ የነበረው ሐዘንና ጥርጣሬ እንደ ጉም በኖ እንዲጠፋ ያደረገው ምንድን ነው?

22 ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን አምኖ ነበር? ታማኝ የሆኑ አንዳንድ ሴቶች፣ መላእክት ተገልጠውላቸው ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን እንዳበሰሯቸው ቢናገሩም እንኳ ጴጥሮስ መጀመሪያ ላይ ይህን መቀበል ከብዶት ነበር። (ሉቃስ 23:55 እስከ 24:11) ቀኑ እየተገባደደ ሲሄድ ግን በጴጥሮስ ልብ ውስጥ የነበረው ሐዘንና ጥርጣሬ እንደ ጉም በኖ ጠፋ። ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ ተነስቷል! ከዚያም ለሐዋርያቱ ሁሉ ተገለጠላቸው። ይህን ከማድረጉ በፊት ግን ለአንድ ሐዋርያ ለብቻው ተገልጦለት ነበር። በዚያን ቀን ሐዋርያቱ “ጌታ በእርግጥ ተነስቷል፤ ለስምዖንም ተገልጦለታል!” ብለው ነበር። (ሉቃስ 24:34) በተመሳሳይም ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚያ ልዩ ቀን ሲጽፍ ኢየሱስ “ለኬፋም ታየ፤ ከዚያም ለአሥራ ሁለቱ ታየ” ብሏል። (1 ቆሮ. 15:5) ኬፋ እና ስምዖን የሚሉት ስሞች የጴጥሮስ ሌላ መጠሪያዎች ናቸው። ኢየሱስ በዚያኑ ቀን ለጴጥሮስ የተገለጠለት ሲሆን ይህንም ያደረገው ጴጥሮስ ብቻውን በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።

ጴጥሮስ ጌታው ይቅርታ እንዲያደርግለት የሚጠይቁ በርካታ ስህተቶችን ፈጽሟል፤ ከመካከላችንስ በእያንዳንዷ ዕለት የአምላክ ይቅርታ የማያስፈልገው ማን አለ?

23. በዛሬው ጊዜ ያሉ ኃጢአት የሠሩ ክርስቲያኖች የጴጥሮስን ሁኔታ ማስታወስ ያለባቸው ለምንድን ነው?

23 ኢየሱስና ጴጥሮስ በድጋሚ ሲገናኙ የነበረውን ልብ የሚነካ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ይህን የሚያውቁት ጴጥሮስና ኢየሱስ ብቻ ናቸው። ጴጥሮስ የሚወደውን ጌታውን እንደገና ሕያው ሆኖ በማየቱ እንዲሁም ባደረገው ነገር ማዘኑንና መጸጸቱን ለመግለጽ የሚያስችል አጋጣሚ በማግኘቱ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን ግን መገመት እንችላለን። ጴጥሮስ በዚህ ወቅት ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው የኢየሱስን ይቅርታ ማግኘት ነበር። ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ምሕረት እንዳደረገለት ማን ሊጠራጠር ይችላል? ዛሬም፣ ኃጢአት የሠሩ ክርስቲያኖች የጴጥሮስን ሁኔታ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። አምላክ ይቅር ሊለን እንደማይችል ፈጽሞ ሊሰማን አይገባም። ኢየሱስ “ይቅርታው ብዙ” የሆነውን የአባቱን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ አንጸባርቋል።—ኢሳ. 55:7

ይቅር እንደተባለ የሚያሳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎች

24, 25. (ሀ) ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ በማጥመድ ያሳለፈው ሌሊት ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ። (ለ) ጴጥሮስ በማግስቱ ጠዋት ኢየሱስ የፈጸመውን ተአምር ሲመለከት ምን አደረገ?

24 ኢየሱስ ሐዋርያቱን ዳግመኛ ከእሱ ጋር ወደሚገናኙበት ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ነገራቸው። እዚያ ሲደርሱ ጴጥሮስ ዓሣ ለማጥመድ ወደ ገሊላ ባሕር ለመሄድ ተነሳ። አንዳንዶቹም አብረውት ሄዱ። ጴጥሮስ አብዛኛውን ሕይወቱን ባሳለፈበት ሐይቅ ላይ እንደገና ዓሣ ማጥመድ ጀመረ። የጀልባው ሳንቃ ሲንቃቃና ማዕበሉ ከጀልባው ጋር ሲላተም የሚፈጥረውን ድምፅ ሲሰማ እንዲሁም ሻካራ የሆኑትን መረቦች በእጁ ሲዳስስ የቀድሞ ትዝታው ሳይቀሰቀስበት አልቀረም። ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማስገር ቢሞክሩም ምንም አልያዙም ነበር።—ማቴ. 26:32፤ ዮሐ. 21:1-3

ጴጥሮስ ከጀልባዋ ላይ ዘሎ ባሕሩ ውስጥ በመግባት እየዋኘ ወደ ዳርቻው ሄደ

25 ይሁን እንጂ ሊነጋጋ ሲል በባሕሩ ዳርቻ ላይ የቆመ አንድ ሰው ተጣርቶ መረባቸውን በሌላኛው አቅጣጫ እንዲጥሉ ነገራቸው። እነሱም በተባሉት መሠረት መረባቸውን ሲጥሉ 153 ዓሣዎች ያዙ! በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ፣ ሰውየው ማን እንደሆነ ተገነዘበ። በመሆኑም ከጀልባዋ ላይ ዘሎ ባሕሩ ውስጥ በመግባት እየዋኘ ወደ ዳርቻው ሄደ። በባሕሩ ዳርቻ ላይ ኢየሱስ ዓሣውን በከሰል ፍም ጠብሶ ታማኝ የሆኑትን ወዳጆቹን መገባቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ይበልጥ ትኩረት ያደረገው ጴጥሮስ ላይ ነበር።—ዮሐ. 21:4-14

26, 27. (ሀ) ኢየሱስ ለጴጥሮስ ምን ሦስት አጋጣሚዎችን ሰጠው? (ለ) ኢየሱስ ጴጥሮስን ሙሉ በሙሉ ይቅር እንዳለው የሚያሳይ ምን ነገር አደረገ?

26 ኢየሱስ ወደተከመሩት ዓሣዎች እያመለከተ ሳይሆን አይቀርም “ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?” በማለት ጴጥሮስን ጠየቀው። ጴጥሮስ ዓሣ ለማስገር ሥራው ያለው ፍቅር ለኢየሱስ ካለው ፍቅር ይበልጥበት ይሆን? ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ እንደካደው ሁሉ ኢየሱስም ለእሱ ያለውን ፍቅር በወዳጆቹ ፊት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሦስት አጋጣሚዎችን ሰጠው። ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደሚወደው ሲገልጽ ኢየሱስ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ቅዱስ አገልግሎቱን በማስቀደም እንዲሁም የክርስቶስን መንጋ ይኸውም ታማኝ ተከታዮቹን በመመገብ፣ በማበረታታትና በመጠበቅ ይህን ፍቅሩን ማሳየት እንደሚችል ነገረው።—ሉቃስ 22:32፤ ዮሐ. 21:15-17

27 በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ አሁንም ቢሆን በእሱም ሆነ በአባቱ ዘንድ ተፈላጊ እንደሆነ አረጋግጦለታል። ጴጥሮስ በክርስቶስ አመራር ሥር በመሆን በጉባኤው ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህ፣ ኢየሱስ ጴጥሮስን ሙሉ በሙሉ ይቅር እንዳለው የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነው! ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ባሳየው ምሕረት ልቡ እንደተነካና ከዚህም ትልቅ ትምህርት እንዳገኘ ምንም ጥርጥር የለውም።

28. ጴጥሮስ እንደ ስሙ ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

28 ጴጥሮስ የተሰጠውን ኃላፊነት ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት አከናውኗል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ወንድሞቹን አበረታቷል። ጴጥሮስ የክርስቶስን ተከታዮች በደግነትና በትዕግሥት መግቧል እንዲሁም ጠብቋል። ስምዖን ይባል የነበረው ይህ ሰው ኢየሱስ ከሰጠው ጴጥሮስ ወይም ዐለት ከሚለው ስም ጋር በሚስማማ መንገድ ፈጽሞ የማይናወጥ፣ ጠንካራና አስተማማኝ በመሆን በጉባኤው ላይ መልካም ተጽዕኖ አሳድሯል። ጴጥሮስ ራሱ የጻፋቸው ፍቅር የተንጸባረቀባቸው ሁለት ደብዳቤዎች ለዚህ ግሩም ምሥክር የሚሆኑ ሲሆን እነዚህ ደብዳቤዎች ጠቃሚ ትምህርት ያዘሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ለመሆን በቅተዋል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ደብዳቤዎች ጴጥሮስ ይቅር ባይነትን በተመለከተ ከኢየሱስ ያገኘውን ትምህርት ፈጽሞ እንዳልረሳው ያሳያሉ።—1 ጴጥሮስ 3:8, 9፤ 4:8ን አንብብ።

29. ጴጥሮስ እምነት በማሳየት፣ ኢየሱስ ደግሞ ምሕረት በማድረግ ረገድ የተዉትን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

29 ይህ ለእኛም ትልቅ ትምህርት ይዞልናል። የምንሠራቸውን በርካታ ስህተቶች ይቅር እንዲለን አምላክን በየዕለቱ እንጠይቀዋለን? ከዚያስ ይሖዋ ይቅር እንደሚለንና ይቅርታው ከኃጢአታችን ሙሉ በሙሉ እንደሚያነጻን እንተማመናለን? ሌሎችንስ ይቅር እንላለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጴጥሮስ እምነት በማሳየት፣ ኢየሱስ ደግሞ ምሕረት በማድረግ ረገድ የተዉትን ምሳሌ መከተል እንችላለን።