የማርቆስ ወንጌል 12:1-44

  • ነፍሰ ገዳይ የሆኑት ገበሬዎች ምሳሌ (1-12)

  • ‘የቄሳርን ለቄሳር፣ የአምላክን ለአምላክ’ (13-17)

  • ትንሣኤን በተመለከተ የቀረበ ጥያቄ (18-27)

  • ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት (28-34)

  • ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው? (35-37ሀ)

  • “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ” (37ለ-40)

  • የአንዲት ድሃ መበለት ሁለት ሳንቲሞች (41-44)

12  ከዚያም ምሳሌ በመጠቀም እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ሰው የወይን እርሻ አለማ፤+ ዙሪያውንም አጠረው፤ ጉድጓድ ቆፍሮም የወይን መጭመቂያ አዘጋጀ፤ ማማም ሠራለት፤+ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።+  ወቅቱ ሲደርስ ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን ከገበሬዎቹ እንዲያመጣለት አንድ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ።  እነሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት።  በድጋሚ ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ፤ እሱንም ራሱን ፈነከቱት፤ ደግሞም አዋረዱት።+  ሌላም ባሪያ ላከ፤ እሱን ደግሞ ገደሉት፤ ሌሎች ብዙዎችንም ላከ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ ገደሉ።  አሁን የቀረው የሚወደው ልጁ ነበር።+ ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት በመጨረሻ እሱን ላከው።  እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው።+ ኑ እንግደለው፤ ርስቱም የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ።  ስለዚህ ይዘው ገደሉት፤ ከወይን እርሻውም አውጥተው ጣሉት።+  እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣና ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይን እርሻውንም ለሌሎች ይሰጣል።+ 10  እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ።+ 11  ይህ የይሖዋ* ሥራ ነው፤ ለዓይናችንም ድንቅ ነው።’”+ 12  በዚህ ጊዜ ምሳሌውን የተናገረው እነሱን አስቦ እንደሆነ ስለተረዱ ሊይዙት* ፈለጉ። ሆኖም ሕዝቡን ስለፈሩ ትተውት ሄዱ።+ 13  ከዚያም በንግግሩ ሊያጠምዱት ፈልገው አንዳንድ ፈሪሳውያንን እና የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎችን ወደ እሱ ላኩ።+ 14  እነሱም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና ለመወደድ ብለህ ምንም ነገር እንደማታደርግ፣ የሰውንም ውጫዊ ማንነት አይተህ እንደማትፈርድ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?* 15  እንክፈል ወይስ አንክፈል?” እሱም ግብዝነታቸውን ተረድቶ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር* አምጡና አሳዩኝ” አላቸው። 16  እነሱም አመጡለት፤ እሱም “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉት። 17  ከዚያም ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣+ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ+ ስጡ” አላቸው። እነሱም በእሱ ተደነቁ። 18  በትንሣኤ የማያምኑት+ ሰዱቃውያን ደግሞ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦+ 19  “መምህር፣ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሚስትየዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር መተካት እንዳለበት ጽፎልናል።+ 20  ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አገባና ዘር ሳይተካ ሞተ። 21  ከዚያም ሁለተኛው አገባት፤ ሆኖም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 22  ሰባቱም ዘር አልተኩም። በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። 23  እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት በትንሣኤ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” 24  ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ባለማወቃችሁ አይደለም?+ 25  ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ።+ 26  ስለ ሙታን መነሳት ግን በሙሴ መጽሐፍ፣ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም?+ 27  እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እናንተ እጅግ ተሳስታችኋል።”+ 28  ከጸሐፍት ወገን የሆነ አንድ ሰው መጥቶ ሲከራከሩ ይሰማ ነበር፤ ኢየሱስ ጥሩ አድርጎ እንደመለሰላቸው አስተውሎ “ከትእዛዛት ሁሉ የመጀመሪያው* የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።+ 29  ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጀመሪያው ይህ ነው፦ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ይሖዋ* አምላካችን አንድ ይሖዋ* ነው፤ 30  አንተም አምላክህን ይሖዋን* በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣* በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።’+ 31  ሁለተኛው ደግሞ ‘ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው።+ ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።” 32  ጸሐፊውም እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ የተናገርከው እውነት ነው፤ ‘እሱ አንድ ነው፤ ከእሱ ሌላ አምላክ የለም’፤+ 33  እሱን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ አእምሮና* በሙሉ ኃይል መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ፣ ሙሉ በሙሉ ከሚቃጠል መባና ከመሥዋዕት ሁሉ እጅግ ይበልጣል።”+ 34  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በማስተዋል እንደመለሰ ተረድቶ “አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅክ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ግን ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም።+ 35  ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እያስተማረ ሳለ እንዲህ አለ፦ “ጸሐፍት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?+ 36  ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ+ ሲናገር ‘ይሖዋ* ጌታዬን “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ብሏል።+ 37  ዳዊት ራሱ ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”+ ሕዝቡም በደስታ ያዳምጠው ነበር። 38  ማስተማሩንም በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ ዘርፋፋ ልብስ ለብሰው መዞር ይወዳሉ፤ በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ፤+ 39  በምኩራብ ከፊት መቀመጥ፣* በራት ግብዣ ላይም የክብር ቦታ ይፈልጋሉ።+ 40  የመበለቶችን ቤት* ያራቁታሉ፤ ለታይታ ብለውም* ጸሎታቸውን ያስረዝማሉ። እነዚህ የከፋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።” 41  ኢየሱስ በመዋጮ ሣጥኖቹ*+ ትይዩ ተቀምጦ ሕዝቡ በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንደሚከቱ ይመለከት ጀመር፤ ብዙ ሀብታሞችም ብዙ ሳንቲሞች ይከቱ ነበር።+ 42  በዚህ ጊዜ አንዲት ድሃ መበለት መጥታ በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች* ከተተች።+ 43  ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዋጮ ሣጥኖቹ* ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።+ 44  ሁሉም የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ሰጥታለች።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የማዕዘኑ ራስ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ሊያስሩት።”
ወይም “ትክክል ነው ወይስ አይደለም?”
ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የሚበልጠው።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ቃል በቃል “በሙሉ የመረዳት ችሎታና።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የተሻለውን መቀመጫ መያዝ።”
ወይም “ንብረት።”
ወይም “ማሳበቢያ እንዲሆናቸውም።”
ወይም “በዕቃዎቹ።”
ቃል በቃል “ሁለት ሌፕተን ይኸውም አንድ ኳድራንስ።” ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በዕቃዎቹ።”