የማቴዎስ ወንጌል 5:1-48

  • የተራራው ስብከት (1-48)

    • ኢየሱስ በተራራ ላይ ማስተማር ጀመረ (1, 2)

    • ለደስታ ምክንያት የሚሆኑ ዘጠኝ ነገሮች (3-12)

    • ጨውና ብርሃን (13-16)

    • ኢየሱስ ሕጉን ሊፈጽም መጣ (17-20)

    • ቁጣን (21-26)፣ ምንዝርን (27-30)፣ ፍቺን (31, 32)፣ ቃለ መሐላን (33-37)፣ አጸፋ መመለስን (38-42)፣ ጠላትን መውደድን በተመለከተ የተሰጠ ምክር (43-48)

5  ሕዝቡንም ባየ ጊዜ ወደ ተራራ ወጣ፤ በዚያ ከተቀመጠ በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ መጡ።  ከዚያም ኢየሱስ መናገር ጀመረ፤ እንዲህም ሲል አስተማራቸው፦  “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ* ደስተኞች ናቸው፤+ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።  “የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናኛ ያገኛሉና።+  “ገሮች*+ ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።+  “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤+ ይጠግባሉና።*+  “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤+ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።  “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤+ አምላክን ያያሉና።  “ሰላም ፈጣሪዎች* ደስተኞች ናቸው፤+ የአምላክ ልጆች ይባላሉና። 10  “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤+ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና። 11  “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣+ ስደት ሲያደርሱባችሁና+ ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ።+ 12  በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ+ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤+ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።+ 13  “እናንተ የምድር ጨው+ ናችሁ፤ ሆኖም ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን እንዴት መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ ተጥሎ+ በሰው ከመረገጥ በቀር ለምንም ነገር አያገለግልም። 14  “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ።+ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም። 15  ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ* አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል፤ በቤት ውስጥ ላሉትም ሁሉ ያበራል።+ 16  በተመሳሳይም ሰዎች መልካም ሥራችሁን+ አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ+ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።+ 17  “ሕጉን ወይም የነቢያትን ቃል ልሽር እንደመጣሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም።+ 18  እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስኪከናወኑ ድረስ ከሕጉ አነስተኛዋ ፊደል ወይም የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም አትቀርም።+ 19  በመሆኑም አነስተኛ ከሆኑት ከእነዚህ ትእዛዛት አንዷን የሚጥስና ሌሎች ሰዎችም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ታናሽ* ይባላል። እነዚህን ትእዛዛት የሚያከብርና የሚያስተምር ሰው ግን በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ* ይባላል። 20  ጽድቃችሁ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ+ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማትገቡ+ ልነግራችሁ እወዳለሁ። 21  “በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘አትግደል፤+ ሰው የገደለ ሁሉ ግን በፍርድ ቤት ይጠየቃል’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 22  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት+ ሁሉ በፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ወንድሙንም ጸያፍ በሆነ ቃል የሚያጥላላ ሁሉ በከፍተኛ ፍርድ ቤት* ይጠየቃል፤ ‘አንተ የማትረባ ጅል’ የሚለው ደግሞ ለእሳታማ ገሃነም* ሊዳረግ ይችላል።+ 23  “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ+ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ 24  መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።+ 25  “ክስ ከመሠረተብህ ባላጋራ ጋር ወደ ፍርድ ቤት እየሄዳችሁ ሳለ ፈጥነህ ታረቅ፤ አለዚያ ባላጋራህ ለዳኛው፣ ዳኛው ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ዘብ አሳልፎ ይሰጥህና እስር ቤት ልትገባ ትችላለህ።+ 26  እውነት እልሃለሁ፣ የመጨረሻዋን ሳንቲምህን* ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ፈጽሞ ከዚያ አትወጣም። 27  “‘አታመንዝር’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 28  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት+ ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።+ 29  ስለዚህ ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።+ መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም* ከሚወረወር ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።+ 30  እንዲሁም ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው።+ መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም* ከሚጣል ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።+ 31  “በተጨማሪም ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ይስጣት’+ ተብሏል። 32  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና* ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ምንዝር ለመፈጸም እንድትጋለጥ ያደርጋታል፤ እንዲሁም በዚህ መንገድ የተፈታችን ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።+ 33  “ከዚህም ሌላ በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤+ ይልቁንም ለይሖዋ* የተሳልከውን ፈጽም’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 34  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ፈጽሞ አትማሉ።+ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የአምላክ ዙፋን ነውና፤ 35  በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግሩ ማሳረፊያ ነችና፤+ በኢየሩሳሌምም ቢሆን አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነችና።+ 36  በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከፀጉርህ አንዷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ማድረግ አትችልምና። 37  ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤+ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው+ ነው። 38  “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 39  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት።+ 40  አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሊያቀርብህና እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢፈልግ መደረቢያህንም ጨምረህ ስጠው፤+ 41  እንዲሁም አንድ ባለሥልጣን አንድ ኪሎ ሜትር* እንድትሄድ ቢያስገድድህ* ሁለት ኪሎ ሜትር አብረኸው ሂድ። 42  ለሚለምንህ ስጥ፤ ሊበደርህ የሚፈልገውንም ሰው* ፊት አትንሳው።+ 43  “‘ባልንጀራህን ውደድ፤+ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 44  እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ+ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤+ 45  ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤+ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።+ 46  የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ?+ ቀረጥ ሰብሳቢዎችስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 47  ደግሞስ ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 48  በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም* እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መንፈስ ለማግኘት የሚለምኑ፤ ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ።”
ወይም “የዋሆች።”
ወይም “ይረካሉና።”
ወይም “ሰላማውያን።”
እንደ ስንዴ ያሉ የእህል ዓይነቶችን ለመስፈር የሚያገለግል ዕቃ።
“መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ብቁ ያልሆነ” ማለት ነው።
“መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ብቁ የሆነ” ማለት ነው።
ከኢየሩሳሌም ውጭ ቆሻሻ የሚቃጠልበት ቦታ ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የአይሁዳውያንን የሳንሄድሪን ሸንጎ ያመለክታል።
ወይም “የመጨረሻዋን ትንሽ ሳንቲምህን።” ቃል በቃል “የመጨረሻዋን ኳድራንስ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የግዳጅ አገልግሎት እንድትፈጽም ቢያስገድድህ።”
ወይም “አንድ ማይል።” ለ14ን ተመልከት።
ያለወለድ መበደር የሚፈልግን ሰው ያመለክታል።
ወይም “ሙሉ።”