ዘፍጥረት 14:1-24

  • አብራም ሎጥን ታደገው (1-16)

  • መልከጼዴቅ አብራምን ባረከው (17-24)

14  በዚያን ጊዜ የሰናኦር+ ንጉሥ አምራፌል፣ የኤላሳር ንጉሥ አርዮክ፣ የኤላም+ ንጉሥ ኮሎዶጎምር+ እና የጎይም ንጉሥ ቲድአል  ከሰዶም+ ንጉሥ ከቤራ፣ ከገሞራ+ ንጉሥ ከቢርሻ፣ ከአድማህ ንጉሥ ከሺንአብ፣ ከጸቦይም+ ንጉሥ ከሸሜበር እና ከቤላ ማለትም ከዞአር ንጉሥ ጋር ጦርነት ገጠሙ።  እነዚህ* ሁሉ በሲዲም ሸለቆ*+ ማለትም በጨው ባሕር*+ ሠራዊታቸውን አሰባሰቡ።  እነሱም ኮሎዶጎምርን 12 ዓመት አገለገሉት፤ በ13ኛው ዓመት ግን ዓመፁ።  ስለሆነም በ14ኛው ዓመት ኮሎዶጎምርና አብረውት የነበሩት ነገሥታት መጥተው ረፋይምን በአስተሮትቃርናይም፣ ዙዚምን በሃም፣ ኤሚምን+ በሻዌቂሪያታይም፣  ሆራውያንን+ ደግሞ ሴይር+ ከሚባለው ተራራቸው አንስቶ በምድረ በዳ እስከሚገኘው እስከ ኤልጳራን ድረስ በሚዘልቀው ስፍራ ድል አደረጓቸው።  ከዚያም ቃዴስ+ ወደምትባለው ወደ ኤንሚሽጳጥ ተመልሰው በመምጣት መላውን የአማሌቃውያን+ ግዛትና በሃጻጾንታማር+ ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያንን+ ድል አደረጉ።  በዚህ ጊዜ የሰዶም ንጉሥ፣ የገሞራ ንጉሥ፣ የአድማህ ንጉሥ፣ የጸቦይም ንጉሥ እንዲሁም የቤላ ማለትም የዞአር ንጉሥ ከእነሱ ጋር ለመዋጋት ሠራዊታቸውን አስተባብረው በሲዲም ሸለቆ* ውስጥ ለጦርነት ተሰለፉ፤  የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፣ የጎይምን ንጉሥ ቲድአልን፣ የሰናኦርን ንጉሥ አምራፌልን እንዲሁም የኤላሳርን+ ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት ተነሱ፤ አራቱ ነገሥታት ከአምስቱ ጋር ተዋጉ። 10  የሲዲም ሸለቆ* በቅጥራን ጉድጓዶች የተሞላ ነበር፤ የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ሸሽተው ለማምለጥ ሲሞክሩ እነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ ወደቁ፤ የቀሩት ደግሞ ወደ ተራራማው አካባቢ ሸሹ። 11  ከዚያም ድል አድራጊዎቹ የሰዶምንና የገሞራን ንብረት በሙሉ እንዲሁም ምግባቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ።+ 12  በተጨማሪም በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን+ ከነንብረቱ ይዘውት ሄዱ። 13  ከዚያም አንድ ያመለጠ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ነገረው። በዚያን ጊዜ አብራም የኤሽኮል እና የአኔር ወንድም በሆነው በአሞራዊው በማምሬ+ ትላልቅ ዛፎች አጠገብ ይኖር* ነበር።+ እነዚህ ሰዎች የአብራም አጋሮች ነበሩ። 14  በዚህ መንገድ አብራም ዘመዱ*+ በምርኮ መወሰዱን ሰማ። ስለሆነም በቤቱ የተወለዱትን 318 የሠለጠኑ አገልጋዮች ሰብስቦ ተነሳ፤ ወራሪዎቹንም ተከትሎ እስከ ዳን+ ድረስ ሄደ። 15  በሌሊትም ሠራዊቱን ከፋፈለ፤ እሱና አገልጋዮቹም በወራሪዎቹ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ድል አደረጓቸው። እሱም ከደማስቆ በስተ ሰሜን እስከምትገኘው እስከ ሆባ ድረስ አሳደዳቸው። 16  የወሰዷቸውን ንብረቶችም ሁሉ አስመለሰ፤ በተጨማሪም ዘመዱን ሎጥንና ንብረቶቹን እንዲሁም ሴቶቹንና ሌሎቹን ሰዎች አስመለሰ። 17  አብራም ኮሎዶጎምርንና ከእሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ድል አድርጎ ከተመለሰ በኋላ የሰዶም ንጉሥ ከአብራም ጋር ለመገናኘት ወደ ሻዌ ሸለቆ* ማለትም ወደ ንጉሡ ሸለቆ+ ወጣ። 18  የሳሌም ንጉሥ+ መልከጼዴቅም+ ምግብና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ እሱም የልዑሉ አምላክ ካህን+ ነበር። 19  አብራምንም ባረከው፤ እንዲህም አለው፦ “ሰማይንና ምድርን የሠራውልዑሉ አምላክ አብራምን ይባርክ፤ 20  የሚጨቁኑህን በእጅህ አሳልፎ የሰጠህ፣ልዑሉ አምላክ ይወደስ!” አብራምም ከሁሉም ነገር ላይ አንድ አሥረኛውን ሰጠው።+ 21  ከዚያም የሰዶም ንጉሥ አብራምን “ሰዎቹን* ስጠኝ፤ ንብረቶቹን ግን ለራስህ ውሰድ” አለው። 22  አብራም ግን የሰዶምን ንጉሥ እንዲህ አለው፦ “ሰማይንና ምድርን ወደሠራው ወደ ልዑሉ አምላክ ወደ ይሖዋ እጄን አንስቼ እምላለሁ፣ 23  ‘አብራምን አበለጸግኩት’ እንዳትል የአንተ ከሆነው ነገር ምንም አልወስድም፤ ሌላው ቀርቶ ብጣሽ ክርም ሆነ የጫማ ማሰሪያ አልወስድም። 24  ወጣቶቹ ከበሉት ምግብ በስተቀር ምንም ነገር አልወስድም። ከእኔ ጋር የዘመቱት አኔር፣ ኤሽኮልና ማምሬ+ ግን ድርሻቸውን ይውሰዱ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሙት ባሕርን ያመለክታል።
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
“እነዚህ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በዘፍጥረት 14:1 ላይ የተጠቀሱትን ነገሥታት ነው።
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ወይም “በድንኳኖች ውስጥ ይኖር።”
ቃል በቃል “ወንድሙ።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ወይም “ነፍሳቱን።”