የያዕቆብ ደብዳቤ 1:1-27

  • ሰላምታ (1)

  • ጽናት ደስታ ያስገኛል (2-15)

    • ተፈትኖ የተረጋገጠ እምነት (3)

    • “በእምነት መለመኑን ይቀጥል” (5-8)

    • ምኞት ወደ ኃጢአትና ሞት ይመራል (14, 15)

  • መልካም ስጦታ ሁሉ ከላይ ነው (16-18)

  • ቃሉን መስማትና በተግባር ማዋል (19-25)

    • ፊቱን በመስተዋት የሚያይ ሰው (23, 24)

  • “ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ” (26, 27)

1  የአምላክና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የሆነው ያዕቆብ፣+ በየቦታው ለተበተኑት ለ12ቱ ነገዶች፦ ሰላምታ ይድረሳችሁ!  ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፤+  ይህን ስታደርጉ ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ።+  ይሁንና በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና* እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም።+  እንግዲህ ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤+ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ* ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና፤+ ይህም ሰው ይሰጠዋል።+  ሆኖም ምንም ሳይጠራጠር በእምነት መለመኑን ይቀጥል፤+ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነውና።  እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከይሖዋ* አንዳች ነገር አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ የለበትም፤  ይህ ሰው በሁለት ሐሳብ የሚዋልልና በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ነው።+  ይሁንና ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በመደረጉ ደስ ይበለው፤*+ 10  እንዲሁም ባለጸጋ የሆነው ዝቅ በመደረጉ+ ደስ ይበለው፤ ምክንያቱም ባለጸጋ ሰው እንደ ሜዳ አበባ ይረግፋል። 11  ፀሐይ ወጥታ በኃይለኛ ሙቀቷ ተክሉን ታጠወልጋለች፤ አበባውም ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ ባለጸጋ ሰውም ልክ እንደዚሁ በዕለት ተዕለት ተግባሩ ሲዋትት ከስሞ ይጠፋል።+ 12  ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤+ ምክንያቱም ይህ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ፣ ይሖዋ* እሱን ለሚወዱት ቃል የገባውን የሕይወት አክሊል ይቀበላል።+ 13  ማንም ሰው ፈተና ሲደርስበት “አምላክ እየፈተነኝ ነው” አይበል። አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም። 14  ሆኖም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል* ይፈተናል።+ 15  ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ሲፈጸም ደግሞ ሞት ያስከትላል።+ 16  የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ አትታለሉ። 17  መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤+ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት+ ሲሆን እሱ ደግሞ ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም።+ 18  ፈቃዱ ስለሆነም ከፍጥረታቱ መካከል እኛ እንደ በኩራት እንድንሆን+ በእውነት ቃል አማካኝነት ወለደን።+ 19  የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ይህን እወቁ፦ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና+ ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት፤+ 20  የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግምና።+ 21  ስለዚህ ጸያፍ የሆነውን ነገር ሁሉና ክፋትን ሁሉ* አስወግዳችሁ+ እናንተን* ሊያድን የሚችለውን በውስጣችሁ የሚተከለውን ቃል በገርነት ተቀበሉ። 22  ሆኖም ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ+ እንጂ የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን በማታለል ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ። 23  ማንም ሰው ቃሉን የሚሰማ እንጂ የማያደርገው ከሆነ+ የገዛ ፊቱን በመስተዋት እያየ ካለ ሰው ጋር ይመሳሰላል። 24  ይህ ሰው ራሱን ካየ በኋላ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። 25  ሆኖም ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ+ በትኩረት የሚመለከትና በዚያ የሚጸና ሰው ሰምቶ የሚረሳ ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውል ሰው ነው፤ በሚያደርገውም ነገር ደስተኛ ይሆናል።+ 26  አንድ ሰው አምላክን እያመለከ እንዳለ* ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ* ከሆነ+ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው። 27  በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ* ‘ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና+ መበለቶችን+ በመከራቸው መርዳት+ እንዲሁም ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ’ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ምሉዓንና።”
ወይም “ስህተት ሳይፈላልግ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ይኩራራ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ሲማረክና በወጥመድ ሲያዝ።”
“እጅግ ተስፋፍቶ የሚገኘውን ክፋት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሳችሁን።”
ወይም “ሃይማኖተኛ እንደሆነ።”
ወይም “አንደበቱ ላይ ልጓም የማያስገባ።”
ወይም “ሃይማኖት።”