የዮሐንስ የመጀመሪያው ደብዳቤ 3:1-24

  • የአምላክ ልጆች ነን (1-3)

  • የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች (4-12)

    • ኢየሱስ የዲያብሎስን ሥራ ያፈርሳል (8)

  • እርስ በርስ ተዋደዱ (13-18)

  • “አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው” (19-24)

3  የአምላክ ልጆች ተብለን እንድንጠራ+ አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ!+ ደግሞም ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀን ለዚህ ነው፤+ ምክንያቱም ዓለም እሱን አላወቀውም።+  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እኛ አሁን የአምላክ ልጆች ነን፤+ ሆኖም ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም።+ እሱ በሚገለጥበት ጊዜ እንደ እሱ እንደምንሆን እናውቃለን፤ ምክንያቱም እሱን በእርግጥ እናየዋለን።  በእሱ ላይ እንዲህ ያለ ተስፋ ያላቸው ሁሉ እሱ ንጹሕ እንደሆነ እነሱም ራሳቸውን ያነጻሉ።+  በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ ሁሉ ዓመፀኛ ነው፤ ኃጢአትም ዓመፅ ነው።  በተጨማሪም እሱ እንዲገለጥ የተደረገው ኃጢአታችንን እንዲያስወግድ መሆኑን ታውቃላችሁ፤+ እሱ ደግሞ ኃጢአት የለበትም።  ከእሱ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ የሚኖር ሁሉ በኃጢአት ጎዳና አይመላለስም፤+ በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ ሁሉ እሱን አላየውም ደግሞም አላወቀውም።  ልጆቼ ሆይ፣ ማንም አያሳስታችሁ፤ እሱ ጻድቅ እንደሆነ ሁሉ በጽድቅ ጎዳና የሚመላለስ ሰውም ጻድቅ ነው።  በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ የዲያብሎስ ወገን ነው፤ ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያው አንስቶ* ኃጢአት ሲሠራ ቆይቷል።+ የአምላክ ልጅ የተገለጠው የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ* ነው።+  ከአምላክ የተወለደ ሁሉ በኃጢአት ጎዳና አይመላለስም፤+ የአምላክ ዘር* እንዲህ ባለው ሰው ውስጥ ይኖራልና፤ በኃጢአት ጎዳናም ሊመላለስ አይችልም፤ ይህ ሰው ከአምላክ የተወለደ ነውና።+ 10  የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ በግልጽ ይታወቃሉ፦ በጽድቅ ጎዳና የማይመላለስ ሁሉ የአምላክ ወገን አይደለም፤ ወንድሙን የማይወድም የአምላክ ወገን አይደለም።+ 11  ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን የሚል ነውና፤+ 12  ከክፉው* ወገን እንደሆነውና ወንድሙን በጭካኔ እንደገደለው እንደ ቃየን መሆን የለብንም።+ ቃየን ወንድሙን በጭካኔ የገደለው በምን ምክንያት ነበር? የእሱ ሥራ ክፉ፣+ የወንድሙ ሥራ ግን ጽድቅ ስለነበረ ነው።+ 13  ወንድሞች፣ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።+ 14  እኛ ወንድሞችን ስለምንወድ+ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን።+ ወንድሙን የማይወድ በሞት ውስጥ ይኖራል።+ 15  ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤+ ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።+ 16  እሱ ሕይወቱን* ለእኛ አሳልፎ ስለሰጠ በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤+ እኛም ሕይወታችንን* ለወንድሞቻችን አሳልፈን የመስጠት ግዴታ አለብን።+ 17  ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ቁሳዊ ንብረት ያለው ሰው ወንድሙ ሲቸገር ተመልክቶ ሳይራራለት ቢቀር ‘የአምላክ ፍቅር በእሱ ውስጥ አለ’ እንዴት ሊባል ይችላል?+ 18  ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና+ በእውነት+ እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።+ 19  ከእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንም በፊቱ እንዲረጋጋ* እናደርጋለን፤ 20  ይህን የምናደርገው ልባችን እኛን በሚኮንንበት ነገር ሁሉ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል።+ 21  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ልባችን የማይኮንነን ከሆነ ከአምላክ ጋር በነፃነት መነጋገር እንችላለን፤+ 22  እንዲሁም ትእዛዛቱን ስለምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች ስለምናደርግ የምንጠይቀውን ሁሉ ከእሱ እንቀበላለን።+ 23  በእርግጥም ትእዛዙ ይህ ነው፦ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናምንና+ እሱ ባዘዘን መሠረት እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው።+ 24  በተጨማሪም ትእዛዛቱን የሚጠብቅ ሰው ከእሱ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል፤ እሱም እንዲህ ካለው ሰው ጋር አንድነት ይኖረዋል።+ እሱ ከእኛ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ እንደሚኖር በሰጠን መንፈስ አማካኝነት እናውቃለን።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለማጥፋት።”
ወይም “ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ።”
ዘር የሚተካን ወይም ፍሬ የሚያፈራን ዘር ያመለክታል።
ሰይጣንን ያመለክታል።
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሳችንን።”
ወይም “ሙሉ እምነት እንዲያድርበት።”