የጴጥሮስ የመጀመሪያው ደብዳቤ 1:1-25

  • ሰላምታ (1, 2)

  • “ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናል” (3-12)

  • እንደ ታዛዥ ልጆች ቅዱሳን ሁኑ (13-25)

1  የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፤+ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣+ በእስያና በቢቲኒያ ተበትነው ለሚገኙ፣ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ለሆኑ የአምላክ ምርጦች፣  ይኸውም አባት የሆነው አምላክ አስቀድሞ ባወቀው መሠረት ለተመረጡት+ ደግሞም ታዛዥ እንዲሆኑና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንዲረጩ+ በመንፈስ ለተቀደሱት፦+ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ+ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ+ እንደ አዲስ ወልዶናልና፤+  እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል።+ ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል፤+  እናንተንም አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካኝነት በኃይሉ እየጠበቃችሁ ነው።  አሁን ለአጭር ጊዜ በልዩ ልዩ ፈተናዎች መጨነቃችሁ የግድ ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የተነሳ እጅግ እየተደሰታችሁ ነው፤+  እነዚህ ፈተናዎች የሚደርሱባችሁ፣ በእሳት የተፈተነ ቢሆንም እንኳ ሊጠፋ ከሚችለው ወርቅ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለውና ተፈትኖ* የተረጋገጠው እምነታችሁ+ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ግርማንና ክብርን ያስገኝ ዘንድ ነው።+  እሱን አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ። አሁን ባታዩትም እንኳ በእሱ ላይ እምነት እያሳያችሁና በቃላት ሊገለጽ በማይችል ታላቅ ደስታ እጅግ ሐሴት እያደረጋችሁ ነው፤  ምክንያቱም የእምነታችሁ ግብ ላይ እንደምትደርሱ ይኸውም ራሳችሁን* እንደምታድኑ ታውቃላችሁ።+ 10  ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ የተነበዩት ነቢያት ይህን መዳን በተመለከተ ትጋት የተሞላበት ምርምርና ጥልቅ ጥናት አካሂደዋል።+ 11  በውስጣቸው ያለው መንፈስ በክርስቶስ ላይ ስለሚደርሱት መከራዎችና+ ከዚያ በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ ሲመሠክር ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ስለ የትኛው ጊዜ ወይም ወቅት እያመለከተ እንዳለ ይመረምሩ ነበር።+ 12  እነሱ ራሳቸውን እያገለገሉ እንዳልሆነ ተገልጦላቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ+ ምሥራቹን ባበሰሩላችሁ ሰዎች አማካኝነት ከተነገሯችሁ ነገሮች ጋር በተያያዘ እናንተን እያገለገሉ ነበር። መላእክትም እነዚህን ነገሮች ለማየት ይጓጓሉ። 13  በመሆኑም አእምሯችሁን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ ታጠቁ፤+ የማስተዋል ስሜታችሁን በሚገባ ጠብቁ፤+ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በምታገኙት ጸጋ ላይ አድርጉ። 14  ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤ 15  ከዚህ ይልቅ የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤+ 16  “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ልትሆኑ ይገባል” ተብሎ ተጽፏልና።+ 17  ደግሞም ምንም ሳያዳላ+ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት የምትለምኑ ከሆነ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ሆናችሁ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ አምላክን በመፍራት ኑሩ።+ 18  እናንተ ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት* ከንቱ አኗኗር ነፃ የወጣችሁት*+ ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ይኸውም በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና። 19  ከዚህ ይልቅ ነፃ የወጣችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ+ ደም ባለ ውድ ደም+ ይኸውም በክርስቶስ ደም ነው።+ 20  እርግጥ እሱ አስቀድሞ የታወቀው፣ ዓለም ከመመሥረቱ* በፊት+ ነው፤ ሆኖም ለእናንተ ሲባል በዘመናት መጨረሻ ላይ እንዲገለጥ ተደረገ።+ 21  እናንተም እምነታችሁና ተስፋችሁ በአምላክ ላይ ይሆን ዘንድ እሱን ከሞት ባስነሳውና+ ክብር ባጎናጸፈው+ አምላክ ያመናችሁት በእሱ አማካኝነት ነው።+ 22  እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ራሳችሁን* ስላነጻችሁ ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ አላችሁ፤+ በመሆኑም እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።+ 23  ሕያው በሆነውና ጸንቶ በሚኖረው አምላክ ቃል አማካኝነት እንደ አዲስ የተወለዳችሁት+ በሚበሰብስ ሳይሆን በማይበሰብስ ዘር*+ ነው።+ 24  “ሥጋ ሁሉ* እንደ ሣር ነውና፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው፤ ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ 25  የይሖዋ* ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”+ ለእናንተም የተሰበከላችሁ ምሥራች ይህ “ቃል” ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ተጣርቶ።”
ወይም “ነፍሳችሁን።”
ወይም “በወግ ከወረሳችሁት።”
ቃል በቃል “የተዋጃችሁት።”
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
ወይም “ነፍሳችሁን።”
ዘር የሚተካን ወይም ፍሬ የሚያፈራን ዘር ያመለክታል።
ወይም “ሰው ሁሉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።