ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 4:1-22

  • “አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም” (1-5)

    • ቃሉን በጥድፊያ ስሜት ስበክ (2)

  • “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ” (6-8)

  • ጳውሎስ ስላለበት ሁኔታ የሰጠው መግለጫ (9-18)

  • የስንብት ቃላት (19-22)

4  በአምላክ ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን+ ላይ በሚፈርደው+ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አጥብቄ አሳስብሃለሁ፤ ደግሞም በእሱ መገለጥና+ በመንግሥቱ+ አማካኝነት አዝሃለሁ፦  ቃሉን ስበክ፤+ አመቺ በሆነ ጊዜም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ በጥድፊያ ስሜት አገልግል፤ በብዙ ትዕግሥትና በማስተማር ጥበብ ውቀስ፣+ ገሥጽ እንዲሁም አጥብቀህ ምከር።+  ትክክለኛውን ትምህርት* የማይታገሡበት ጊዜ ይመጣልና፤+ ከዚህ ይልቅ ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው* በዙሪያቸው አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።+  እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ይመልሳሉ፤ ለተረትም ጆሮ ይሰጣሉ።  አንተ ግን በሁሉም ነገር የማስተዋል ስሜትህን ጠብቅ፣ መከራን በጽናት ተቋቋም፣+ የወንጌላዊነትን ሥራ አከናውን* እንዲሁም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።+  እኔ እንደ መጠጥ መባ እየፈሰስኩ ነውና፤*+ ደግሞም ነፃ የምለቀቅበት ጊዜ+ በጣም ቀርቧል።  መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤+ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤+ እምነትን ጠብቄአለሁ።  ከዚህ በኋላ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፤+ ጻድቅ ፈራጅ+ የሆነው ጌታ በፍርድ ቀን ይህን እንደ ሽልማት አድርጎ ይሰጠኛል፤+ ይሁንና ለእኔ ብቻ ሳይሆን የእሱን መገለጥ ለሚናፍቁ ሁሉ ነው።  ወደ እኔ ቶሎ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። 10  ዴማስ+ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት* ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዷልና፤ ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ደግሞ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል። 11  አብሮኝ ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎት ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና። 12  ቲኪቆስን+ ግን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ። 13  ስትመጣ በጥሮአስ፣ ካርጶስ ጋ የተውኩትን ካባ እንዲሁም የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን* አምጣልኝ። 14  የመዳብ አንጥረኛው እስክንድር ብዙ ጉዳት አድርሶብኛል። ይሖዋ* እንደ ሥራው ይከፍለዋል።+ 15  አንተም ከእሱ ተጠንቀቅ፤ መልእክታችንን ክፉኛ ተቃውሟልና። 16  የመጀመሪያ መከላከያዬን ባቀረብኩበት ወቅት ሁሉም ትተውኝ ሄዱ እንጂ ከእኔ ጎን የቆመ ማንም አልነበረም፤ አምላክ ይህን አይቁጠርባቸው። 17  ሆኖም የስብከቱ ሥራ በእኔ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸምና ብሔራት ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ አጠገቤ ቆሞ ኃይል ሰጠኝ፤+ ከአንበሳ አፍም ዳንኩ።+ 18  ጌታ ከክፉ ሥራ ሁሉ ይታደገኛል፤ እንዲሁም አድኖኝ ለሰማያዊ መንግሥቱ ያበቃኛል።+ ለእሱ ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን። 19  ለጵርስቅላና ለአቂላ+ እንዲሁም ለኦኔሲፎሮስ+ ቤተሰብ ሰላምታ አቅርብልኝ። 20  ኤርስጦስ+ በቆሮንቶስ ቀርቷል፤ ጢሮፊሞስ+ ግን ስለታመመ በሚሊጢን ትቼዋለሁ። 21  ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። ኤውቡሉስ ሰላም ብሎሃል፤ እንዲሁም ጱዴስ፣ ሊኖስ፣ ቅላውዲያና ወንድሞች ሁሉ ሰላምታቸውን ልከውልሃል። 22  ጌታ ከምታሳየው መንፈስ ጋር ይሁን። ጸጋው ከእናንተ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጤናማውን ትምህርት፤ ጠቃሚውን ትምህርት።”
ወይም “መስማት የሚፈልጉትን እንዲነግሯቸው።”
ወይም “ምሥራቹን መስበክህን ቀጥል።”
ፊልጵ 2:17 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “የአሁኑን ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከቆዳ የተዘጋጁትን ጥቅልሎች ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።