በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1 | ጸሎት—‘የሚያስጨንቃችሁን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ’

1 | ጸሎት—‘የሚያስጨንቃችሁን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ’

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7

ምን ማለት ነው?

ይሖዋ አምላክ ልባችንንና አእምሯችንን እንደ ሸክም ስለሚጫነን ስለ ማንኛውም ጉዳይ እንድናነጋግረው ጋብዞናል። (መዝሙር 55:22) ትንሽ ትልቅ ሳንል ስለ ማንኛውም ችግር መጸለይ እንችላለን። እኛን የሚያሳስበን ጉዳይ ሁሉ ይሖዋንም ያሳስበዋል። ወደ ይሖዋ መጸለይ የአእምሮ ሰላም ለማግኘት የሚረዳ ወሳኝ እርምጃ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

የሚረዳን እንዴት ነው?

የአእምሮ ጤና መቃወስ ሲያጋጥመን ብቻችንን እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ያለንበትን ሁኔታ ሌሎች ሰዎች ሙሉ በሙሉ ላይረዱልን ይችላሉ። (ምሳሌ 14:10) ሆኖም የሚሰማንን ሁሉ አውጥተን ለአምላክ በጸሎት ስንነግረው በደግነት ያዳምጠናል፤ ስሜታችንንም ይረዳልናል። ይሖዋ በትኩረት ይመለከተናል፤ የሚሰማንን ሥቃይና ያለብንን ትግል ይረዳል፤ እንዲሁም ስለሚያስጨንቀን ስለ ማንኛውም ነገር ወደ እሱ እንድንጸልይ ይፈልጋል።—2 ዜና መዋዕል 6:29, 30

ወደ ይሖዋ መጸለያችን እሱ እንደሚያስብልን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። “ጉስቁልናዬን አይተሃልና፤ በጭንቀት መዋጤን ታውቃለህ” በማለት የጸለየውን መዝሙራዊ ስሜት እንጋራለን። (መዝሙር 31:7) ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ በትኩረት እንደሚመለከት ማወቃችን በራሱ ያጋጠመንን አስቸጋሪ ሁኔታ በጽናት ለመቋቋም ይረዳናል። ሆኖም ይሖዋ ጭንቀታችንን በመመልከት ብቻ አይወሰንም። ያጋጠመንን ችግር ከማንም በተሻለ ይረዳል፤ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ማጽናኛና ማበረታቻ እንድናገኝ ይረዳናል።