በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወት መኖር ዋጋ አለው!

በሕይወት መኖር ዋጋ አለው!

ፋይዘል ሚስቱን በሞት አጥቷል፤ ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ከባድ የልብ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈለገው። እንዲህ ብሏል፦ “የኢዮብን መጽሐፍ ሳነብ ይሖዋ የኢዮብ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው በምክንያት እንደሆነ ተገነዘብኩ። በጣም በተጨነቅንበት ጊዜ፣ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት የነበረን ሰው ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማንበባችን ያጽናናል።” አክሎም “በሕይወት መኖር በእርግጥም ዋጋ አለው” ብሏል።

ታርሻ እናቷን በሞት ያጣችው ገና ትንሽ ልጅ እያለች ነው። እንዲህ ብላለች፦ “የተለያዩ ችግሮች ቢፈራረቁብንም ፈጣሪያችንን ማወቃችን ተስፋችን እንዲለመልም፣ ደስተኞች እንድንሆንና ዓላማ ያለው ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል። ይሖዋ እያንዳንዱን ቀን በጽናት ለማለፍ የሚያስፈልገንን ድጋፍና እርዳታ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።”

ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ እንደተመለከትነው፣ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን አንዳንድ አሳዛኝ ሁኔታዎች ሕይወት ልንወጣው የማንችለው አቀበት እንዲሆንብን ሊያደርጉ ይችላሉ። ችግሮች እንደ ከባድ ሸክም ሲጫኑህ በሕይወት መኖር ምንም ዋጋ እንደሌለው አልፎ ተርፎም የአንተ ነገር ግድ የሚሰጠው ማንም እንደሌለ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ የአንተ ሁኔታ እንደሚያሳስበው እርግጠኛ ሁን። ምክንያቱም በእሱ ፊት እጅግ ውድ ነህ።

የመዝሙር 86 ጸሐፊ “አንተ መልስ ስለምትሰጠኝ፣ በተጨነቅኩ ቀን አንተን እጣራለሁ” በማለት በአምላክ ላይ ያለውን እምነት ገልጿል። (መዝሙር 86:7) ይሁንና ‘አምላክ “በተጨነቅኩ ቀን” መልስ የሚሰጠኝ እንዴት ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

ምንም እንኳ አምላክ ችግሮችህን ወዲያውኑ ባያስወግድልህም ችግሮቹን መቋቋም የምትችልበት ውስጣዊ ሰላም እንደሚሰጥህ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት አረጋግጦልሃል፤ ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና ሐሳባችሁን ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7 የግርጌ ማስታወሻ) ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አምላክ እንደሚያስብልህ የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

አምላክ ያስብልሃል

“አንዷም [ድንቢጥ] እንኳ በአምላክ ዘንድ ችላ አትባልም። . . . እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።”ሉቃስ 12:6, 7 የግርጌ ማስታወሻ

እስቲ አስበው፦ እንደ ድንቢጦች ያሉ እዚህ ግቡ የማይባሉ ትናንሽ ወፎች እንኳ በአምላክ ዘንድ ችላ አይባሉም። አምላክ አንዷን ድንቢጥ እንኳ ትኩረት ሰጥቶ ይመለከታታል፤ ምክንያቱም እያንዳንዷ ወፍ በእሱ ዘንድ ውድ የሆነች ፍጡር ናት። ሰዎች ደግሞ በአምላክ ዘንድ ከድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላቸው። ከአምላክ ምድራዊ ፍጥረታት ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙት ሰዎች ናቸው፤ ምክንያቱም በአምላክ ‘መልክ’ ስለተፈጠሩ የአምላክን የላቁ ባሕርያት የማዳበርና የማንጸባረቅ ችሎታ አላቸው።—ዘፍጥረት 1: 26, 27

“ይሖዋ ሆይ፣ በሚገባ መርምረኸኛል፤ ደግሞም ታውቀኛለህ። . . ሐሳቤን ከሩቅ ታስተውላለህ። . . . መርምረኝ፤ የሚያስጨንቁኝንም ሐሳቦች እወቅ።”መዝሙር 139:1, 2, 23

እስቲ አስበው፦ አምላክ በግለሰብ ደረጃ በደንብ ያውቅሃል። ለማንም አውጥተህ ያልተናገርከውን ውስጣዊ ስሜትህንና ጭንቀትህን ያውቃል። ሰዎች የሚያስጨንቅህን ነገር ላይረዱልህ ቢችሉም አምላክ ግን ስለ አንተ ያስባል እንዲሁም ከጎንህ ሆኖ ሊደግፍህ ይፈልጋል። ይህም መኖርህ ዋጋ እንዳለው እንዲሰማህ ያደርጋል።

አምላክ ይደግፍሃል እንዲሁም ይመራሃል

“ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ፤ እርዳታ ለማግኘት የማሰማው ጩኸት ወደ አንተ ይድረስ። . . . ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ ስጣራ ፈጥነህ መልስልኝ። የድሆችን ጸሎት በትኩረት ያዳምጣል።”መዝሙር 102:1, 2, 17

እስቲ አስበው፦ የሰው ዘር በመከራ የተሞላ ሕይወት መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ የሰው ልጆች የሚያፈስሱትን እያንዳንዱን የእንባ ጠብታ ሲመዘግብ ቆይቷል ማለት ይቻላል። (መዝሙር 56:8) ከዚህ ውስጥ የአንተም እንባ ይገኝበታል። አንተ በአምላክ ዘንድ እጅግ ውድ ስለሆንክ እሱ የሚደርስብህን መከራና የምታፈስሰውን እንባ በሙሉ እንደሚያስታውስ እርግጠኛ ሁን።

“እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ . . . ‘አትፍራ። እረዳሃለሁ’ የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ [ነኝ]።”ኢሳይያስ 41:10, 13

እስቲ አስበው፦ አምላክ አንተን ለመርዳት ዝግጁ ነው። ደግሞም ስትወድቅ ያነሳሃል።

ወደፊት የተሻለ ጊዜ ይመጣል

“አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”ዮሐንስ 3:16

እስቲ አስበው፦ አምላክ ለአንተ ትልቅ ቦታ የሚሰጥህ ከመሆኑ የተነሳ ልጁን ኢየሱስን ለአንተ ሲል መሥዋዕት አድርጎልሃል። ይህ መሥዋዕት ደግሞ ለዘላለም ዓላማ ያለውና ደስተኛ ሕይወት የምትኖርበት አጋጣሚ ከፍቶልሃል። *

ያለህበት ሁኔታ አስጨናቂ ከመሆኑ የተነሳ በሕይወት መቀጠል ከባድ መስሎ ቢታይህም የአምላክን ቃል በጥንቃቄ ለማጥናትና አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ለመገንባት ጥረት አድርግ። እንዲህ ማድረግህ ደስተኛ እንድትሆንና በሕይወት መኖርህ ዋጋ እንዳለው እርግጠኛ እንድትሆን ይረዳሃል።

^ የኢየሱስ መሥዋዕት ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ ይበልጥ ለማወቅ www.dan124.com/am ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት። ቪዲዮው ስለ እኛ > የመታሰቢያው በዓል በሚለው ሥር ይገኛል።