በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ትዳር

አክብሮት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

አክብሮት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

ባል እንዲህ ይላል፦ “እኔና ባለቤቴ ትዳር በመሠረትንበት ወቅት አክብሮት ስለ ማሳየት ያለን አመለካከት የተለያየ ነበር። የአንዳችን ትክክል፣ የሌላኛችን ደግሞ ስህተት ባይሆንም የተለያየ አመለካከት ነበረን። ባለቤቴ ስታነጋግረኝ ይበልጥ አክብሮት ልታሳየኝ እንደሚገባ ይሰማኝ ነበር።”

ሚስት እንዲህ ትላለች፦ “ባደግኩበት አካባቢ በነበረው ባሕል የምናወራው ጮክ ብለን ነው፤ እንዲሁም በፊታችን ብዙ ነገር እንገልጻለን፤ ሌሎች ሲናገሩ ጣልቃ መግባትም ቢሆን የተለመደ ነገር ነበር። እንዲህ ማድረግ በእኛ ባሕል አክብሮት የጎደለው እንደሆነ ተደርጎ አይታይም። ባለቤቴ ባደገበት አካባቢ ያለው ልማድ ግን ከዚህ ጨርሶ የተለየ ነው።”

አክብሮት አንዳንድ ጊዜ ብቻ ልናሳየው የሚገባ ነገር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ለትዳር ወሳኝ የሆነ ባሕርይ ነው። ታዲያ የትዳር ጓደኛችሁን እንደምታከብሩ ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ወንዶች መከበር ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ” የሚል ምክር ለባሎች ይሰጣል። በሌላ በኩል ደግሞ “ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር” ይላል። (ኤፌሶን 5:33) ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ፍቅርና አክብሮት ማግኘት ይፈልጋሉ፤ በተለይ ደግሞ ባሎች አክብሮት ሲያገኙ ይበልጥ ደስተኞች ይሆናሉ። ካርሎስ * የተባለ አንድ ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “ወንዶች ሁኔታዎችን መቆጣጠር፣ ችግሮችን መፍታት እንዲሁም ቤተሰቡን መንከባከብ እንደሚችሉ ሲሰማቸው ደስ ይላቸዋል።” አንዲት ሚስት፣ ባለቤቷ እነዚህን ነገሮች በማድረጉ የምታከብረው ከሆነ እሱ ብቻ ሳይሆን እሷም ትጠቀማለች። ኮሪን የተባለች አንዲት ባለትዳር “ለባለቤቴ አክብሮት ባሳየሁት መጠን እሱም በምላሹ ይበልጥ ፍቅር ያሳየኛል” በማለት ተናግራለች።

ሚስቶችም ቢሆኑ መከበር ይፈልጋሉ። እንዲህ መባሉ ትክክል ነው፤ ምክንያቱም አንድ ባል ሚስቱን ካላከበረ ከልቡ ሊወዳት አይችልም። ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “የባለቤቴን አመለካከትና የምታቀርበውን ሐሳብ ማክበር ይኖርብኛል። ስሜቷንም ቢሆን ማክበር አለብኝ። አንድ ስሜት የተሰማት ለምን እንደሆነ ላይገባኝ ይችላል፤ ይህ ሲባል ግን ስሜቷን ችላ እላለሁ ማለት አይደለም።”

ሰዎች ስለ አክብሮት ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። ዋናው ነገር አንተ የትዳር ጓደኛህን እንዳከበርካት የሚሰማህ መሆኑ ሳይሆን የትዳር ጓደኛህ አክብሮት እንዳሳየሃት የሚሰማት መሆኑ ነው። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ባለው “ተፈታታኙ ነገር” በሚለው ክፍል ሥር የተጠቀሰችው ሚስት ይህን መማር አስፈልጓታል። እንዲህ ብላለች፦ “እኔ አክብሮት እንዳጓደልኩ ባይሰማኝም እንኳ ባለቤቴ እንደዚያ ከተሰማው፣ ማስተካከያ ማድረግ ያለብኝ እኔ ነኝ።”

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • የትዳር ጓደኛችሁን እንድታደንቁ የሚያነሳሷችሁን ሦስት ነገሮች ጻፉ። የጠቀሳችኋቸው ነገሮች፣ ለትዳር ጓደኛችሁ አክብሮት ለማዳበር የሚያስችል መሠረት ሊሆኑላችሁ ይችላሉ።

  • ለአንድ ሳምንት ያህል፣ በሚከተሉት መስኮች (የትዳር ጓደኛችሁን ሳይሆን) የራሳችሁን ምግባር ገምግሙ።

አነጋገራችሁ። በባለትዳሮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው “ደስተኛና የተረጋጋ ትዳር ያላቸው ሰዎች፣ ባልተግባቡበት ጉዳይ ላይ ሲነጋገሩ የሚያነሱት አዎንታዊ ሐሳብ ከአሉታዊው ሐሳብ በአምስት እጥፍ (1 ለ 5) ይበልጣል። በአንጻሩ ደግሞ ትዳራቸው ወደ ፍቺ እያመራ ያለ ሰዎች በሚነጋገሩበት ወቅት የሚያነሱት አዎንታዊ ሐሳብ ከአሉታዊው ሐሳብ ያነሰ (1 ለ 0.8) ነው።” *የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 12:18

ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ባለቤቴን የማነጋግረው አክብሮት በተሞላበት መንገድ ነው? የሚቀናኝ የትዳር ጓደኛዬን ማድነቅ ነው ወይስ የነቀፋ ሐሳብ መሰንዘር? አስተያየት ወይም ቅሬታ ካለኝ ሐሳቤን የምገልጸው በምን ዓይነት የድምፅ ቃና ነው?’ የትዳር ጓደኛችሁ ለጥያቄዎቹ በሰጣችሁት መልስ ይስማማል?—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ቆላስይስ 3:13

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኛችሁን ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ለማድነቅ ሞክሩ። ጠቃሚ ምክር፦ ቀደም ሲል የጠቀሳችኋቸውንና የትዳር ጓደኛችሁን እንድታደንቁ የሚያነሳሷችሁን ባሕርያት መለስ ብላችሁ አስቡ። ለትዳር ጓደኛችሁ፣ የምትወዱላትን ነገር የመናገር ልማድ አዳብሩ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ቆሮንቶስ 8:1

ድርጊታችሁ። አሊስያ የተባለች አንዲት ባለትዳር እንዲህ ትላለች፦ “የቤት ውስጥ ሥራ በመሥራት ብዙ ጊዜ አሳልፋለሁ፤ ባለቤቴ የተመገበበትን ዕቃ በማንሳት ወይም በማጠብ ለማደርገው ጥረት አድናቆት እንዳለው ሲያሳይ ጥረቴ ዋጋ እንዳለውና በትዳራችን ውስጥ ጠቃሚ ቦታ እንዳለኝ ይሰማኛል።”

ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘የትዳር ጓደኛዬን የምይዝበት መንገድ አክብሮት እንዳለኝ በግልጽ ያሳያል? ለትዳር ጓደኛዬ በቂ ጊዜና ትኩረት እሰጣለሁ?’ የትዳር ጓደኛችሁ ለጥያቄዎቹ በሰጣችሁት መልስ ይስማማል?

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኛችሁ አክብሮት እንዲያሳያችሁ የምትፈልጉባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች ጻፉ። የትዳር ጓደኛችሁም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ ንገሩት። ከዚያም የጻፋችሁትን ተቀያየሩና የትዳር ጓደኛችሁ በጠቀሳቸው አቅጣጫዎች አክብሮት ለማሳየት ጥረት አድርጉ። አክብሮት ለማሳየት በግለሰብ ደረጃ ማድረግ በምትችሉት ነገር ላይ ትኩረት አድርጉ። ቅድሚያውን ወስዳችሁ አክብሮት የምታሳዩ ከሆነ የትዳር ጓደኛችሁም ተመሳሳይ ነገር ማድረጉ አይቀርም።

^ አን.8 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.14 ቴን ሌሰንስ ቱ ትራንስፎርም ዮር ሜሬጅ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።