በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የባሕር አቆስጣ ፀጉር

የባሕር አቆስጣ ፀጉር

በቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ አጥቢ እንስሳት ከቆዳቸው ሥር ብርድ ለመከላከል የሚረዳ ወፍራም ስብ አላቸው። የባሕር አቆስጣ ግን ለየት ያለ የብርድ መከላከያ አለው፤ ይህም ሰውነቱን የሸፈነው ጥቅጥቅ ያለ ፀጉር ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የባሕር አቆስጣ ፀጉር ከሌሎች አጥቢ እንስሳት ይበልጥ ጥቅጥቅ ብሎ የበቀለ ነው፤ ይህ እንስሳ በአንድ ካሬ ሴንቲ ሜትር ውስጥ 155,000 ፀጉሮች አሉት። አቆስጣው በሚዋኝበት ወቅት ሰውነቱን የሸፈኑት ፀጉሮች አየር አፍነው ያስቀራሉ። በፀጉሮቹ ውስጥ የታፈነው አየር ደግሞ ቀዝቃዛው ውኃ የእንስሳውን ቆዳ በቀጥታ እንዳይነካውና የሰውነቱን ሙቀት እንዳያሳጣው ይከላከልለታል።

ሳይንቲስቶች የባሕር አቆስጣን ፀጉር በመመልከት ብዙ ነገሮችን መማር እንደሚቻል ያምናሉ። እነዚህ ሳይንቲስቶች ብርድ በሚከላከሉ ፀጉራማ ኮቶች ላይ ያሉትን ፀጉሮች ቁመትና በመካከላቸው ያለውን ክፍተት በመቀያየር የተለያዩ ሰው ሰራሽ ኮቶችን ለመሥራት ሞክረዋል። ተመራማሪዎቹ ባደረጉት ጥናት የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፦ “የፀጉሮቹ ቁመት በጨመረና ፀጉሮቹ ይበልጥ ጥቅጥቅ ባሉ ቁጥር በፀጉር የተሸፈነው ክፍል ያለው ውኃ የመከላከል አቅምም እየጨመረ ይሄዳል።” በእርግጥም የባሕር አቆስጣዎች ብርድን በሚገባ የሚከላከል ምርጥ ፀጉራማ ኮት አላቸው ሊባል ይችላል።

ተመራማሪዎች አሁን እያደረጉ ያሉት ጥናት ውኃ የማያስገቡ አዲስ ዓይነት ጨርቃ ጨርቆችን ለማምረት በሚደረገው ጥረት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተስፋ ያደርጋሉ። ከዚህ በመነሳት አንዳንዶች ‘እንዲህ ከሆነማ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ ጠልቀው የሚገቡ ሰዎች የባሕር አቆስጣ ያለው ዓይነት ፀጉራማ ልብስ ቢለብሱ ይሻላቸዋል’ ብለው ሳያስቡ አይቀሩም።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ሙቀትን አፍኖ የሚይዘው የባሕር አቆስጣ ፀጉር በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?