በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ልማዶችህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?

ልማዶችህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
  • ኦስቲን ማለዳ ላይ ከእንቅልፉ እንዲቀሰቅሰው የሞላው ሰዓት ሲጮኽ በደንብ ባይነቃም ከአልጋው ዘሎ በመውረድ ማታ ያዘጋጀውን የስፖርት ልብስ ከለባበሰ በኋላ ደጅ ወጥቶ ይሮጣል፤ በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚሮጥ ሲሆን ይህን ማድረግ ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል።

  • ሎሪ ከባለቤቷ ጋር ተጣልታለች። በሁኔታው በጣም ስለተበሳጨች ወደ ኩሽናዋ ሄዳ የታሸገ ቸኮሌት በማውጣት ሙሉውን በላችው፤ በተበሳጨች ቁጥር እንዲህ የማድረግ ልማድ አላት።

ኦስቲን እና ሎሪ የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው? አወቁትም አላወቁት፣ ልማድ በሁለቱም ሕይወት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።

አንተስ? በሕይወትህ ውስጥ ልታዳብራቸው የምትፈልጋቸው ጥሩ ልማዶች አሉ? ምናልባትም አዘውትረህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ የማግኘት ወይም ቤተሰብህን አዘውትረህ የመጠየቅ ግብ ይኖርህ ይሆናል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሲጋራ ማጨስን፣ ለጤና ጠቃሚ ያልሆኑ ምግቦች በብዛት መብላትን ወይም ኢንተርኔት በመቃኘት ብዙ ጊዜ ማሳለፍን የመሳሰሉ መጥፎ ልማዶችን ማስወገድ ትፈልግ ይሆናል።

መጥፎ ልማድን ማሸነፍ ከባድ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። እንዲያውም መጥፎ ልማድ፣ በብርድ ቀን የሞቀ አልጋ ውስጥ የመግባትን ያህል ቀላል እንደሆነ ይነገራል፤ ከሞቀ አልጋ መውጣት ከባድ እንደሆነ ሁሉ ከመጥፎ ልማድ መላቀቅም አስቸጋሪ ነው!

ልማዶችህን መቆጣጠር ብሎም ጠቃሚ እንጂ ጎጂ እንዳይሆኑብህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የቀረቡትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ መመሪያዎች ላይ የተመሠረቱ ሦስት ነጥቦች እንድታነብ እንጋብዝሃለን።