በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የላባዎች አስደናቂ ንድፍ

የላባዎች አስደናቂ ንድፍ

የላባዎች አስደናቂ ንድፍ

ሲጋል የተባለ ወፍ ክንፎቹን በፍጥነት እያርገበገበ ሽቅብ ወደ ሰማይ ይወነጨፋል። አንድ ጊዜ ሰማይ ከደረሰ በኋላ በነፋስ ኃይል እየተገፋ ያለ አንዳች ችግር ይንሳፈፋል። ይህ ወፍ ክንፎቹንና ጅራቱን ትንሽ ዞር ዞር በማድረግ ብቻ አየር ላይ ቀጥ ብሎ መቆም ይችላል። ለመሆኑ እንዲህ ያለ ማራኪ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ የሚያስችለው ምንድን ነው? በአብዛኛው ይህን ለማድረግ የሚያስችሉት ላባዎቹ ናቸው።

በዛሬው ጊዜ ካሉት እንስሳት መካከል ላባ የሚያበቅሉት የወፍ ዝርያ ያላቸው ብቻ ናቸው። አብዛኞቹ ወፎች የተለያየ ዓይነት ላባ አላቸው። ጎላ ብሎ የሚታየውና እርስ በርሱ ተደራርቦ የሚገኘው የላባ ዓይነት ኮንቱር ፌዘር ይባላል፤ ይህ የላባ ዓይነት ወፎች አየሩን እንደ ልብ ለመሰንጠቅ የሚያስችል ቅርጽ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ለበረራ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱት የክንፍና የጅራት ላባዎች በዚህ የላባ ዓይነት ውስጥ ይካተታሉ። ሃሚንግበርድ የምትባለው ወፍ ወደ 1,000 ገደማ የሚሆኑ የዚህ ዓይነት ላባዎች ያሏት ሲሆን የዳክዬ ደግሞ ከ25,000 በላይ ይሆናሉ።

ላባዎች አስደናቂ ንድፍ ይንጸባረቅባቸዋል። ሬኪስ የሚባለው የላባ ዘንግ እንደ ልብ የሚተጣጠፍ ቢሆንም አስገራሚ ጥንካሬ አለው። ከዘንጉ ግራና ቀኝ ያለው ለስላሳ የላባ ክፍል ቫን የሚባል ሲሆን እርስ በርስ በተያያዙ ዘርፈ ላባዎች (barbs) የተዋቀረ ነው። ዘርፈ ላባዎች ባርቢዩልስ በሚባሉና እንደ ዚፕ እርስ በርስ በተቆላለፉ በርካታ የላባ ፀጉሮች አማካኝነት ተያይዘዋል። እነዚህ የላባ ፀጉሮች ሲበታተኑ ወፉ ላባውን በምንቃሩ በሚያጸዳበት ጊዜ እንደገና ያያይዛቸዋል። አንተም ብትሆን የተቀደዱ የሚመስሉ የላባ ዘርፎችን በጣቶችህ በቀስታ ሳብ ሳብ በማድረግ እንደገና ማያያዝ ትችላለህ።

በተለይ ክንፍ ላይ የሚገኙት ትላልቅ ላባዎች፣ በዘንጋቸው ግራና ቀኝ ያሉት ሁለት ክፍሎች መጠናቸው ተመጣጣኝ አይደለም፤ አንደኛው አጠር ሲል ሌላው ረዘም ይላል። እያንዳንዱ ላባ እንዲህ ያለ ለበረራ የሚያመች ቅርጽ ያለው መሆኑ፣ ብቻውን እንደ ትንሽ ክንፍ ሆኖ እንዲያገለግል ያስችለዋል። በተጨማሪም ትላልቆቹን ላባዎች ጠጋ አድርገህ ብታያቸው በዘንጉ የታችኛው ክፍል ላይ እንደ መሥመር የተጋደመ ነገር ትመለከታለህ። ላባው በዚህ መንገድ የተሠራ መሆኑ ለዘንጉ ጥንካሬ የሚሰጠው ከመሆኑም በላይ ሳይሰበር እንደ ልብ መተጣጠፍ እንዲችል ያደርገዋል።

ላባዎች ብዙ ጥቅም አላቸው

በርካታ ወፎች ኮንቱር በሚባሉት ትላልቅ ላባዎቻቸው መካከል ተሰበጣጥረው የሚገኙ ፊሎፕሉም ተብለው የሚጠሩ ረጃጅምና ቀጫጭን ላባዎች እንዲሁም ፓውደር ፌዘር የሚባሉ ዱቄት ላባዎች አሏቸው። ፊሎፕሉም የተባሉት ላባዎች በሥሮቻቸው ላይ ወፉ ብርሃንና ድምፅ የመሳሰሉት ነገሮች በላባዎቹ የላይኛው ክፍል ላይ የሚፈጥሩትን ስሜት የሚረዱ አልፎ ተርፎም የበረራ ፍጥነቱን እንዲያስተካክል የሚያስችሉት ሕዋሳት እንዳሏቸው ይገመታል። ከላባ ዓይነቶች መካከል ያለማቋረጥ የሚያድጉትና ፈጽሞ የማይረግፉት ዱቄት ላባዎች ዘርፎቻቸው የመሰባበር ባሕርይ አላቸው፤ ወፉ ገላው ውስጥ ውኃ እንዳይገባ የሚረዳው ይህ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል።

ከዚህ በተጨማሪ ላባዎች ወፉን ከሙቀት፣ ከብርድና እንደ አልትራቫዮሌት ካሉ አደገኛ ጨረሮች በመከላከል ጠቃሚ አገልግሎት ይሰጣሉ። ለአብነት ያህል የባሕር ላይ ዳክዬዎች ቆፈን የሚያስይዘው ቀዝቃዛ ነፋስ የሚያስጨንቃቸው አይመስልም። ለምን? ምንም ነገር የማይዘልቃቸው በሚመስሉት ትላልቅ ላባዎቻቸው ሥር ዳውን ፌዘር ተብሎ የሚጠራ ውፍረቱ እስከ 1.7 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ጥቅጥቅ ያለ ለስላሳ ጫጩት ላባ አለ። አብዛኛው የዳክዬዋ ገላ የተሸፈነው በዚህ የላባ ዓይነት ነው። ሰዎች ብርድን ለመከላከል ከሠሯቸው ነገሮች መካከል ተፈጥሯዊውን ጫጩት ላባ የሚተካከለው የለም።

ላባዎች የኋላ ኋላ ያረጃሉ፤ ስለዚህ ወፎች ያረጁ ላባዎቻቸው እንዲረግፉ በማድረግ በአዲስ ይተኳቸዋል። አብዛኞቹ ወፎች የመብረር ችሎታቸውን እንደያዙ ለመቀጠል የክንፍና የጅራት ላባዎቻቸውን በአዲስ የሚተኩት በየተወሰነ ጊዜና ሚዛናዊ በሆነ ቅደም ተከተል ነው።

“ምንም እንከን የላቸውም”

አስተማማኝ የሆኑ አውሮፕላኖች የረቀቀ ንድፍና የተዋጣለት የምሕንድስና ጥበብ ውጤት ናቸው። ስለ ወፎችና ላባዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? የቅሪተ አካል ማስረጃ ባለመኖሩ የላባዎችን አመጣጥ በሚመለከት በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አራማጆች መካከል የጦፈ ክርክር ተካሂዶ ነበር። ሳይንስ ኒውስ የተባለው መጽሔት ክርክሩ “የአክራሪነት መንፈስ፣” “የሰላ ትችት” እና “የቅሪተ አካል ተመራማሪዎቹ ስሜታዊነት” የተንጸባረቀበት እንደነበረ ይናገራል። ላባ በዝግመተ ለውጥ እንደመጣ ለማሳየት ሲምፖዚየም ያዘጋጁ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አራማጅ የሆኑ አንድ ባዮሎጂስት “ከሳይንስ ጋር የተያያዘ ማንኛውም ጉዳይ እንዲህ ያለ ያልታረመ ባሕርይና እንዲህ ያለ ምሬት ይወልዳል ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም” በማለት እውነቱን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ላባዎች በዝግመተ ለውጥ መገኘታቸው ሐቅ ቢሆን ኖሮ ሂደቱን በሚመለከት የተደረገው ውይይት ይህን ያህል የተጋጋለ ይሆን ነበር?

ዬሌ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ማኑዋል ኦቭ ኦርኒቶሎጂ—አቭያን ስትራክቸር ኤንድ ፈንክሽን የተባለ ጽሑፍ ምክንያቱን ሲገልጽ “ላባዎች ምንም እንከን የላቸውም ለማለት ይቻላል፤ ችግሩ ይህ ነው” በማለት ይናገራል። ላባዎች እየተሻሻሉ እንደመጡ የሚያመለክት ምንም ፍንጭ አይታይባቸውም። እንዲያውም “በቅሪተ አካል ጥናት ከተገኙት ላባዎች ሁሉ በጣም ጥንታዊ የሚባለው ላባ እንኳ በጣም ዘመናዊ ከመሆኑ የተነሳ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወፎች ካላቸው ላባ አይለይም።” * የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ግን ላባዎች በወፎች ቆዳ ላይ ቀስ በቀስ በተከሰቱ ለውጦች ሳቢያ የመጡ እንደሆኑ አድርጎ ያስተምራል። ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ “ላባዎች በየትውልዱ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነ ለውጥ እስካላደረጉ ድረስ በዝግመተ ለውጥ እየተሻሻሉ መጥተዋል ሊባል አይችልም” ብሏል።

በንድፈ ሐሳብ ደረጃም እንኳ ቢሆን፣ በላባ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ባጋጣሚ የሚከሰተውና ከዘር ወደ ዘር የሚተላለፈው እያንዳንዱ ለውጥ የእንስሳውን በሕይወት የመቀጠል ዕድል በእጅጉ እስካላሻሻለለት ድረስ ላባ በዝግመተ ለውጥ መጣ ሊባል አይችልም። ብዙ የዝግመተ ለውጥ አማኞችም እንኳን ሳይቀሩ ላባን የመሰለ እንከን የማይወጣለት፣ ውስብስብና አሠራሩ ፍጹም የሆነ ነገር በዚህ መንገድ ሊገኝ እንደማይችል ተገንዝበዋል።

በተጨማሪም ላባዎች በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ ቀስ በቀስ እየተሻሻሉ መጥተው ከሆነ በየደረጃው የተካሄዱ ለውጦችን የሚጠቁም የቅሪተ አካል ማስረጃ ሊኖር ይገባል። ይሁን እንጂ የተሟሉ ክፍሎች እንደነበሯቸው የሚጠቁሙ የላባ ቅሪቶችን ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ያለውን መላ ምት የሚደግፉ ማስረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም። ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ ላባዎች እንዲያው ባጋጣሚ ሊገኙ እንደማይችሉ ሲጠቁም “የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ከሚለው በተቃራኒ ላባዎች በጣም የተወሳሰቡ ናቸው” በማለት ተናግሯል።

ወፎች ለመብረር የሚያስፈልጋቸው ላባ ብቻ አይደለም

ለዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አራማጆች እንቅፋት የሆነባቸው፣ ላባ እንከን የማይወጣለት መሆኑ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ የወፍ አካል ለመብረር እንዲችል ሆኖ የተሠራ መሆኑ ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ወፍ ቀላልና ውስጣቸው ባዶ የሆኑ አጥንቶች እንዲሁም ከሌሎች እንስሳት በተለየ መልኩ አስተማማኝ የሆነ የአተነፋፈስ ሥርዓት፣ ብሎም ክንፎቿን ለማርገብገብና እንደ ልብ ለመቆጣጠር የሚያስችሏት ልዩ ጡንቻዎች አሏት። እንዲያውም የእያንዳንዱን ላባ ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ጡንቻዎች አሏት። ከዚህም ሌላ እያንዳንዱን ጡንቻ፣ እነዚህን ሁሉ የአካል ክፍሎች በአንድ ጊዜ በመቆጣጠር ዝንፍ ሳይል ከሚሠራውና አስፈላጊው ፕሮግራም ሁሉ ከተቀረጸለት በጣም ትንሽና አስገራሚ ከሆነው አንጎል ጋር የሚያገናኙ ነርቮች አሏት። አዎን፣ ለመብረር አስፈላጊ የሆኑት ላባዎች ብቻ ሳይሆኑ ለማመን በሚያዳግት መልኩ ውስብስብ የሆኑት የወፉ የአካል ክፍሎች ጭምር ናቸው።

በተጨማሪም እያንዳንዱ ወፍ እድገቱን አሃዱ ብሎ የሚጀምረው ማንኛውንም መረጃ ከያዘች አንዲት በጣም ትንሽ ሴል መሆኑን አትዘንጋ። ይህች ሴል፣ ወፉ አንድ ቀን በሰማይ ላይ የሚጀምረውን በረራ ጨምሮ ስለ አጠቃላይ እድገቱና በደመ ነፍስ ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ሁሉ የተሟላ መረጃ ይዛለች። ታዲያ ይህ ሁሉ እንዲያው በአጋጣሚ የመጣ ሊሆን ይችላል? ወይስ በጣም ቀላል፣ ምክንያታዊና ሳይንሳዊ የሆነው መደምደሚያ ወፎችና ላባዎቻቸው ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ፈጣሪ የእጅ አሻራ አለባቸው የሚለው ነው? ማስረጃው ራሱ ይናገር።—ሮሜ 1:20

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በቅሪተ አካል ምርምር መስክ የተገኘው ላባ የተወሰደው በዘመናችን ባሉ ወፎች የዘር ሐረግ ውስጥ “በመሃል የጎደለ” ዝርያ እንደሆነ ተደርጎ ከሚነገርለት አርኬዮፕቴሪክስ የተባለ ከምድር ገጽ የጠፋ ቁራ መሰል ፍጡር ላይ ነው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች ይህን ፍጡር የዘመናዊዎቹ ወፎች ዝርያ እንደሆነ አድርገው አይመለከቱትም።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተመሳስሎ የተሠራ “ማስረጃ”

ወፎች ከሌላ ፍጥረት ተሻሽለው እንደመጡ ለማሳመን በአንድ ወቅት እንደ ትልቅ ማስረጃ ተደርገው ይታዩ የነበሩ አንዳንድ የቅሪተ አካል “ማስረጃዎች” ተመሳስለው የተሠሩ መሆናቸው ተደርሶበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1999 ናሽናል ጂኦግራፊክ የተባለው መጽሔት የዳይኖሶርን የመሰለ ጅራት ስላለው በላባ የተሸፈነ ፍጥረት ቅሪተ አካል የሚገልጽ አንድ ጽሑፍ ይዞ ወጥቶ ነበር። መጽሔቱ ይህ ፍጥረት “ዳይኖሶሮችን ከወፍ ጋር በሚያገናኘው የዘር ሐረግ ላይ በመሃል ጎድሎ የነበረው እውነተኛው ዝርያ” እንደሆነ ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ቅሪተ አካሉ ከሁለት የተለያዩ እንስሳት በተውጣጡ አጽሞች ተገጣጥሞ የተሠራ የሐሰት ማስረጃ እንደሆነ ተደርሶበታል። እንዲያውም ከዚያ ወዲህ ‘ጎድሏል’ የሚባለው እንዲህ ያለው ፍጥረት ተገኝቶ አያውቅም።

[ምንጭ]

O. Louis Mazzatenta/National Geographic Image Collection

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በወፎች ዓይን ሲታይ

ሰዎች ደማቅ በሆነውና ብዙውን ጊዜ በኅብረ ቀለማት ባሸበረቀው የላባዎች መልክ በጣም ይደነቃሉ። ይሁን እንጂ ወፎች እንዲህ ባሉ የላባዎች መልክ ከሰዎች ይበልጥ ይማረካሉ። ሰዎች በዓይናቸው ውስጥ ቀለም ለመለየት የሚያገለግሉ ሦስት ዓይነት ሴሎች ብቻ ሲኖሯቸው አንዳንድ ወፎች ግን አራት ዓይነት ሴሎች አሏቸው። ይህ ተጨማሪ የሴል ዓይነት ወፎች፣ ሰዎች ሊያዩት የማይችሉትን አልትራቫዮሌት የሚባለውን የፀሐይ ጨረር እንዲለዩ ያስችላቸዋል። ሰዎች የአንዳንዶቹን የወፍ ዝርያዎች ወንድና ሴት መለየት ይቸግራቸዋል፤ ይሁን እንጂ የወንዱ ወፍ ላባዎች የአልትራቫዮሌት ጨረሮችን የሚያንጸባርቁበት መንገድ ከሴቷ ይለያል። ወፎች ይህን ልዩነት መለየት ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ተጓዳኝ የሚሆኗቸውን ወፎች ለመለየት ሳይረዳቸው አይቀርም።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዘርፈ ላባ (Barb)

ባርቢዩል

የላባው ዘንግ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትላልቅ ላባዎች (Contour feathers)

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፀጉረ ላባ (Filoplume)

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዱቄት ላባ (Powder feather)

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጫጩት ላባ (Down feather)

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጋኔት