በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

በትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝን ጭንቀት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

በትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝን ጭንቀት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“በትምህርት ቤት የሚያጋጥምህ ጭንቀት ዕድሜህ እየጨመረ ሲሄድ መልኩን ይለውጥ ይሆናል እንጂ መቼም አይቀንስም።”—ጄምስ፣ ኒው ዚላንድ *

“በትምህርት ቤት ውስጥ ያለው ሁኔታ እጅግ ስለሚያስጨንቀኝ አልቅሺ አልቅሺና ጩኺ ጩኺ ይለኛል።”—ሻሮን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ወላጆችህ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚያጋጥምህ ጭንቀት ምን ያህል ከባድ መሆኑን እንደማይረዱልህ ሆኖ ይሰማሃል? እውነት ነው፣ ወላጆችህ ‘አንተ ምን አለብህ? የባንክ ዕዳ መክፈል፣ ቤተሰብ መመገብ አሊያም አለቃህን ማስደሰት አይጠበቅብህ!’ ይሉህ ይሆናል። ይሁን እንጂ በትምህርት ቤት የሚያጋጥሙህ ሁኔታዎች ከወላጆችህ ባልተናነሰ ወይም ከዚያ በላይ እንደሚያስጨንቁህ ይሰማህ ይሆናል።

ሌላው ቀርቶ ወደ ትምህርት ቤት መሄድና መመለስ በራሱ ጭንቀት ሊፈጥር ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ታራ እንዲህ ትላለች:- “ብዙውን ጊዜ በትምህርት ቤት አውቶቡስ ውስጥ ጠብ ይነሳል። በዚህ ጊዜ ሹፌሩ መኪናውን ያቆምና ሁላችንንም ከመኪናው ያስወርደናል። በመሆኑም ትምህርት ቤት የምንደርሰው ግማሽ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ አርፍደን ነው።”

ትምህርት ቤት ከደረስክ በኋላስ ጭንቀቱ ይቀንስ ይሆን? እምብዛም አይቀንስም! ምናልባትም ከዚህ በታች ያሉት አስተያየቶች የአንተንም ስሜት የሚገልጹ ሆነው ታገኛቸው ይሆናል።

አስተማሪዎች የሚፈጥሩት ውጥረት።

“አስተማሪዎቼ ጠንክሬ በመሥራት ጥሩ ውጤት እንዳመጣ ይጠብቁብኛል። እኔም እነሱን ለማስደሰት ስል ውጥረት ውስጥ እገባለሁ።”—ሳንድራ፣ ፊጂ

“አስተማሪዎች፣ በተለይም ተማሪዎቻቸው አንድ ዓይነት ችሎታ እንዳላቸው ካስተዋሉ በዚያ ትምህርት ከሌሎች ልቀው እንዲገኙ ከፍተኛ ግፊት ያደርጉባቸዋል። መምህራን፣ በትምህርታችን ስኬታማ እንድንሆን ጫና ያሳድሩብናል።”—ኤፕርል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“በሕይወትህ ውስጥ ጠቃሚ ግብ ያለህ ቢሆንም እንኳ አንዳንድ አስተማሪዎች፣ እነሱ ጥሩ ነው ብለው ያሰቡትን ግብ ካልተከታተልክ የማትረባ እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደርጉሃል።”—ናኦሚ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

አስተማሪዎች የሚፈጥሩት ውጥረት በአንተ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮብሃል?

እኩዮችህ የሚፈጥሩት ውጥረት።

“በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ ተማሪዎች የበለጠ ነፃነት ያላቸው ሲሆን ዓመጸኞችም ናቸው። እነሱን ካልመሰልክ ኋላ ቀር እንደሆንክ አድርገው ይቆጥሩሃል።”—ኬቭን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የአልኮል መጠጥ እንድጠጣና የጾታ ግንኙነት እንድፈጽም በየዕለቱ ግፊት ያደርጉብኛል። ከእነሱ ጋር ለመመሳሰል የሚገፋፋኝ ውስጣዊ ፍላጎት መቋቋም አንዳንዴ ከባድ ይሆንብኛል።”—አሮን፣ ኒው ዚላንድ

“የ12 ዓመት ልጅ ስሆን ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀኝ የወንድ ጓደኛ እንድይዝ የሚደረግብኝ ግፊት ነው። በትምህርት ቤት ያሉ ልጆች ሁሉ ‘የወንድ ጓደኛ ሳትይዢ የምትኖሪው እስከ መቼ ነው?’ ይሉኛል።”—አሊግዛንድሪያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የወንድ ጓደኛ እንድይዝ ጫና ያሳድሩብኝ ነበር። እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳልሆን ስቀር ሌዝቢያን (ከሴቶች ጋር ወሲብ የሚፈጽሙ ሴቶች) ናት ተባልኩ። በዚያን ጊዜ ገና የአሥር ዓመት ልጅ ነበርኩ!”—ክሪስታ፣ አውስትራሊያ

እኩዮችህ የሚፈጥሩት ውጥረት በአንተ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮብሃል?

አብረውህ የሚማሩ ልጆች ስለ እምነትህ ሲያውቁ ምን ሊሉህ እንደሚችሉ በማሰብ መጨነቅ።

“አብረውህ ለሚማሩ ልጆች ስለ እምነትህ መናገር ከባድ ነው፤ ምክንያቱም ከነገርካቸው በኋላ ለአንተ ምን አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል አታውቅም። ከሰው የማትገጥም አድርገው እንዳይመለከቱህ ትፈራለህ።”—ካረል፣ ሃዋይ

“በመለስተኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ልጆች ዕፅ ይወስዳሉ፣ የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ እንዲሁም የአልኮል መጠጥ ይጠጣሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች በመመራትህ የተነሳ ተማሪዎቹ ከሌሎች የተለየህ አድርገው እንዳይመለከቱህና እንዳያሾፉብህ ትፈራለህ።”—ሱዘን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ከእምነትህ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች በአንተ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድረውብሃል?

ጭንቀት የሚፈጥሩ ሌሎች ሁኔታዎች። ከሚከተሉት መካከል ይበልጥ በሚያስጨንቅህ ነገር ላይ ምልክት አድርግ ወይም ሌላ የሚያስጨንቅህ ነገር ካለ ጻፍ።

 

  • የፈተና ጊዜ መቃረቡ

  • የቤት ሥራ

  • ወላጆችህ ከአንተ ብዙ የሚጠብቁ መሆናቸው

  • ከራስህ ብዙ የምትጠብቅ መሆንህ

  • ጉልበተኞች ወይም የጾታ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች

  • ሌላ ․․․․․

ጭንቀትን ለመቀነስ የሚረዱ አምስት ነጥቦች

ትምህርት ቤት ውስጥ ጭንቀት የሚፈጥር ምንም ዓይነት ነገር አያጋጥመኝም ብሎ ማሰብ ከእውነታው የራቀ ነው። እርግጥ ነው፣ ከመጠን ያለፈ ጭንቀት ከባድ ችግር ሊያስከትልብህ ይችላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” በማለት ጽፏል። (መክብብ 7:7 የ1954 ትርጉም) ይሁንና ጭንቀት እንዲያሳብድህ መፍቀድ የለብህም። ለዚህ ቁልፉ ነገር ጭንቀትን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምትችለው እንዴት እንደሆነ መማር ነው።

ጭንቀትን መቋቋም ክብደት ከማንሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ክብደት የሚያነሳ ሰው ስኬታማ ለመሆን ከፈለገ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት። ክብደቱን በትክክለኛው መንገድ ያነሳል፤ እንዲሁም ከመጠን በላይ የሆነ ክብደት ከማንሳት ይቆጠባል። እንዲህ ካደረገ ሰውነቱ ሳይጎዳ ጡንቻውን ማዳበር ይችላል። እነዚህን ነገሮች የማያደርግ ከሆነ ግን ጡንቻው ሊጎዳና ሌላው ቀርቶ አጥንቱ ሊሰበር ይችላል።

አንተም በተመሳሳይ ራስህን ሳትጎዳ፣ ያጋጠመህን ጭንቀት መቋቋምና መሥራት ያሰብከውን ነገር በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።

  1. የጭንቀቱን መንስኤ ማወቅ። አንድ ጥበብ ያዘለ ምሳሌ “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3 የ1954 ትርጉም) ሆኖም የጭንቀትህ መንስኤ ምን መሆኑን ካላወቅህ በጣም ከሚያስጨንቅህ ነገር መሸሸግ አትችልም። ስለሆነም ቀደም ሲል ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠኸውን መልስ አስብ። በጣም የሚያስጨንቅህ ነገር ምንድን ነው?

  2. ምርምር አድርግ። ለአብነት ያህል፣ የተሰጠህ የቤት ሥራ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ውጥረት ፈጥሮብህ ከሆነ መጋቢት 2004 የንቁ! መጽሔት ላይ በወጣው “የወጣቶች ጥያቄ—የቤት ሥራዬን ለመሥራት ጊዜ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?” በሚለው ርዕስ ላይ ምርምር አድርግ። አብረውህ የሚማሩ ልጆች የጾታ ብልግና እንድትፈጽም ጫና የሚያሳድሩብህ ከሆነ ደግሞ መጋቢት 2007 የንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ—አንድ ሰው ‘አብሬው እንድወጣ’ ቢጠይቀኝስ?” የሚለውን ርዕስ በማንበብ ጠቃሚ ምክር ማግኘት ትችላለህ።

  3. የምትሰጠውን መልስ አስቀድመህ ተዘጋጅ። አብረውህ የሚማሩ ልጆች ስለ እምነትህ ሲያውቁ ምን ሊሉህ እንደሚችሉ በማሰብ ከመጨነቅ ይልቅ ሁኔታው ከመከሰቱ በፊት ምን መልስ መስጠት ወይም ምን ማድረግ እንዳለብህ አስብ። (ምሳሌ 29:25) የ18 ዓመቷ ከልሲ እንዲህ ብላለች:- “ጥያቄዎች ከመነሳታቸው በፊት አስቀድሜ መዘጋጀቴ ጭንቀቴን እንድቋቋም ረድቶኛል። ስለማምንባቸው ነገሮች እንዴት ላስረዳቸው እንደምችል አስቀድሜ አስብ ነበር።” በቤልጅየም የሚኖረው የ18 ዓመቱ አሮን ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነገር ማድረጉን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ምን ጥያቄዎች ሊያነሱ እንደሚችሉ በማሰብ መልሱን እዘጋጅ ነበር። እንዲህ ባላደርግ ኖሮ ስለማምንበት ነገር ለመናገር ድፍረቱ አይኖረኝም ነበር።”

  4. ዛሬ ነገ አትበል። ጊዜ የሚፈታቸው ችግሮች በጣም ጥቂት ናቸው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ችግሮች ችላ ከተባሉ እየከፉ ሊሄዱና ጭንቀትህን ሊያባብሱት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ ማንነትህን ወዲያውኑ ማሳወቅህ ጥበቃ ሊሆንልህ ይችላል። የ20 ዓመቷ ማርሼ እንዲህ ትላለች:- “በየዓመቱ ትምህርት ሲጀመር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋሜን ለመናገር መንገድ የሚከፍቱልኝን ጉዳዮች አንስቼ ጭውውት እጀምራለሁ። የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ሳልናገር ጊዜ ባለፈ ቁጥር ማንነቴን መግለጽ የዚያኑ ያህል ከባድ እንደሚሆንብኝ ተገንዝቤያለሁ። አቋሜን ማሳወቄና ዓመቱን ሙሉ ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖሬ በጣም ረድቶኛል።”

  5. እርዳታ ጠይቅ። ጠንካራ የሚባል ክብደት አንሺ እንኳ የአቅም ገደብ አለው። አንተም ብትሆን የአቅም ገደብ አለህ። በመሆኑም ሸክሙን ብቻህን መሸከም የለብህም። (ገላትያ 6:2) ወላጆችህ ወይም የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲረዱህ ለምን አትጠይቅም? ቀደም ሲል በዚህ ርዕስ ላይ ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠኸውን መልስ አሳያቸው። ከሚያጋጥሙህ ጭንቀቶች አንዳንዶቹን ለማሸነፍ ምን እርዳታ ሊያደርጉልህ እንደሚችሉም ጠይቃቸው። በአየርላንድ የምትኖረው ሊዝ ‘አብረውኝ የሚማሩት ልጆች በእምነቴ ምክንያት ያፌዙብኝ ይሆናል’ የሚል ጭንቀት እንዳደረባት ለአባቷ ነገረችው። ሊዝ እንዲህ ትላለች:- “አባቴ በየቀኑ ትምህርት ቤት አድርሶኝ ከመሄዱ በፊት አብሮኝ ይጸልይ ነበር። ይህ ደግሞ የደኅንነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል።”

ተገቢ የሆነ ጭንቀት

አምነህ መቀበል ሊከብድህ ቢችልም ስለ አንዳንድ ጉዳዮች መጨነቅህ ተገቢ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መጨነቅህ ትጉህ እንደሆንክና ሕሊናህ እንዳልደነዘዘ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምንም ጉዳይ የማይጨነቅን ሰው እንዴት አድርጎ እንደገለጸው ልብ በል:- “እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ማንቀላፋት፤ ጥቂት ማንጐላቸት፤ እጅን አጣጥፎ ‘እስቲ ጥቂት ልረፍ’ ማለት፤ ድኽነት እንደ ወንበዴ፣ ዕጦትም መሣሪያ እንደ ታጠቀ ሰው ከተፍ ይልብሃል።”—ምሳሌ 6:9-11

የ16 ዓመቷ ሃይዲ ሁኔታውን እንደሚከተለው በማለት በጥሩ መንገድ ገልጻዋለች:- “ትምህርት ቤት በጣም መጥፎ ቦታ ሊመስል ይችላል። ሆኖም በዚያ የሚያጋጥምህ አስጨናቂ ሁኔታ በሥራ ቦታ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው።” እርግጥ ነው፣ ጭንቀትን መቋቋም ቀላል አይደለም፤ ሆኖም የሚያጋጥምህን ጭንቀት በተሳካ ሁኔታ መቋቋም ከቻልክ ለጉዳት አይዳርግህም። እንዲያውም ይበልጥ ጠንካራ ሰው ያደርግሃል።

 

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

  • እንደተጨነቅክ ሊያሳዩ የሚችሉ አንዳንድ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

  • ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች ፍጽምናን መጠበቅ ጭንቀታችንን ከማባባስ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም የምንለው ለምንድን ነው?

  • በጭንቀት እንደተዋጥክ ሲሰማህ ማንን ማማከር ትችላለህ?