በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መረቦቹ ባዶ የሆኑት ለምንድን ነው?

መረቦቹ ባዶ የሆኑት ለምንድን ነው?

መረቦቹ ባዶ የሆኑት ለምንድን ነው?

“ጥሩም መጥፎም ዓመታትን አይቻለሁ፤ ያሁኑን ያክል ግን ዓሣ የተመናመነበት ጊዜ አጋጥሞኝ አያውቅም።” ይህን የተናገሩት በእንግሊዝ ሰሜናዊ ምሥራቅ የባሕር ዳርቻ ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ጆርጅ የተባሉ የ65 ዓመት አረጋዊ ናቸው። “ምንም የቀረ ነገር የለም፤ ሳልሞንም፣ ዋይትፊሽም፣ ኮድም፣ ሎብስተርም፣ ሁሉም ነገር አልቋል።”

ጉዳዩ የሚያሳስበው ጆርጅን ብቻ አይደለም፤ ተመሳሳይ የሆኑ አስደንጋጭ ዘገባዎች ከሰባቱም ባሕሮች እየመጡ ነው። በፔሩ የሚኖረው አጉስቲን 350 ቶን ጭነት የሚይዝ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባ ካፒቴን ነው። አጉስቲን እንዲህ ብሏል፦ “ሰርዲን የሚባሉት ትንንሽ ዓሣዎች እጥረት ማጋጠም የጀመረው ከ12 ዓመት በፊት ነው። በፔሩ ዓመቱን ሙሉ ዓሣ በብዛት ይገኝ ነበር፤ አሁን ግን ለበርካታ ወራት ዓሣ አጥተን የምንቆይባቸው ጊዜያት አሉ። ዓሣ ለማግኘት ከባሕሩ ዳርቻ ወደ ውስጥ ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘን አናውቅም ነበር፤ አሁን ግን እስከ 300 ኪሎ ሜትር ያህል እንጓዛለን።”

በገሊሺያ፣ ስፔን የሚኖረው አንቶኒዮ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ዓሣ ሳጠምድ ቆይቻለሁ። የባሕሩ ሀብት ቀስ በቀስ ሲሟጠጥ ተመልክቻለሁ። ባሕሩ ሊተካ ከሚችለው በላይ እያጠመድን ነው።”

አንድ ደን በቡልዶዘር አማካኝነት ምን ያህል እንደተመነጠረ በፎቶግራፍ አማካኝነት ማየት ይቻላል፤ በውቅያኖስ ውስጥ ያለው የዓሣ ብዛት ምን ያህል እንደተመናመነ ግን በዚህ መንገድ ማወቅ አይቻልም። ሆኖም የሚደርሰው ጥፋት ከዚያ የሚተናነስ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ከመጠን በላይ ዓሣ ማጥመድን አስመልክቶ እንዲህ በማለት በቅርቡ አስጠንቅቋል፦ “ዓሣ ከሚጠመድባቸው ቦታዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ወይም ከመጠን በላይ ጥቅም ላይ መዋላቸው አሊያም መሟጠጣቸው ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢና አደገኛ ያደርገዋል።”

አንድ አምስተኛ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ከእንስሳት የሚገኘውን ፕሮቲን በዋነኝነት የሚያገኘው ከዓሣ ነው። በመሆኑም በጣም ወሳኝ የሆነው ይህ የምግብ ምንጭ የመጥፋት አደጋ ተደቅኖበታል። ዓሣ በባሕር ውስጥ በሁሉም ቦታ እኩል አይገኝም። እንዲያውም በውስጡ ካለው ሕይወት አንጻር ሲታይ አብዛኛው የውቅያኖስ ክፍል በረሃ ነው ለማለት ይቻላል። ዓሣ በብዛት የሚገኘው በባሕር ዳርቻዎች አቅራቢያ እንዲሁም በአልሚ ምግቦች የበለጸገ ውኃ ከውቅያኖስ ውስጥ በሚፈልቅባቸው አካባቢዎች ነው። በባሕር ውስጥ ላለው የምግብ ሰንሰለት መሠረት የሆኑት ፋይቶፕላንክተን የተባሉ ረቂቅ ዕፅዋት አልሚ ምግቦቹን ይመገቧቸዋል። ታዲያ ዓሣ አጥማጆቹ ለመተዳደሪያቸው መሠረት የሆኑትን የዓሣ ማጥመጃ ቦታዎች እያጠፉ ያሉት በምን መንገድ ነው? የአንድን ዓሣ ማጥመጃ ቦታ ታሪክ መመልከታችን መልሱን እንድናገኝ ይረዳናል።

ግራንድ ባንክስ—ውድመቱ ጀመረ

ጆን ካቦት * የተባለ አንድ ጣሊያናዊ መርከበኛና አሳሽ ከእንግሊዝ ተነስቶ አትላንቲክ ውቅያኖስን ሲያቋርጥ በካናዳ የባሕር ዳርቻ አካባቢ ዓሣ በብዛት የሚገኝበትን ግራንድ ባንክስ የሚባል ብዙም ጥልቀት የሌለው ቦታ አገኘ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ወርቅ ሲገኝ እንደሚያደርገው ሁሉ ወደዚህ ቦታ መጉረፍ ጀመረ። ይህ የሆነው ክሪስቶፈር ኮሎምበስ በ1492 ታሪካዊ የባሕር ጉዞ ካደረገ ከአምስት ዓመት በኋላ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በመቶ የሚቆጠሩ ዓሣ አጥማጆች በግራንድ ባንክስ ዓሣ ለማጥመድ አትላንቲክን ማቋረጥ ጀመሩ። ከዚያ በፊት ማንም አውሮፓዊ ኮድ በተባለው ዓሣ የተሞላ እንዲህ ያለ ቦታ አይቶ አያውቅም ነበር።

ኮድ የሚባለው ዓሣ የወርቅ ያህል ይወደድ ነበር። ነጭና ከስብ ነፃ ከመሆኑ የተነሳ ተወዳጅ የነበረው የኮድ ሥጋ አሁንም ድረስ በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊነቱ አልቀነሰም። የአትላንቲኩ ኮድ አብዛኛውን ጊዜ ከ1.4 እስከ 9 ኪሎ ግራም ይመዝናል፤ በግራንድ ባንክስ ያሉት አንዳንድ የኮድ ዝርያዎች ግን መጠናቸው ሰው ያህላል። ባለፉት ተከታታይ መቶ ዘመናት ዓሣ አጥማጆች ትላልቅ ተጎታች መረቦችንና በሺህ የሚቆጠሩ መንጠቆዎች የታሰሩባቸው ረዣዥም ገመዶችን መጠቀም ከጀመሩ በኋላ የሚይዙት ዓሣ ቁጥር እየጨመረ መጣ።

የዓሣ ማጥመድ ኢንዱስትሪ ያስከተለው ችግር

በ19ኛው መቶ ዘመን አንዳንድ አውሮፓውያን የዓሣ መጠን በተለይም ሄሪንግ የሚባለው ዓሣ እየተመናመነ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው መግለጽ ጀመሩ። ይሁን እንጂ የብሪቲሽ ሮያል ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ቶማስ ሃክስሊ በ1883 በለንደን በተደረገው ዓለም አቀፍ የዓሣ ማጥመጃ ቦታዎች ኤግዚቢሽን ላይ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥተው ነበር፦ “የእነዚህ ዓሦች ብዛት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ እኛ የምናጠምደው እጅግ አነስተኛ ነው። . . . በዚህም ምክንያት ኮድ የሚጠመድበት ቦታ . . . ምናልባትም ሁሉም ታላላቅ የዓሣ ማጥመጃ ሥፍራዎች ፈጽሞ ሊሟጠጡ እንደማይችሉ አምናለሁ።”

የዓሣ ማጥመድ ኢንዱስትሪው በግራንድ ባንክስ ላይ በእንፋሎት ኃይል የሚሠሩ ጀልባዎችን መጠቀም ከጀመረ በኋላም እንኳ የሃክስሊን አመለካከት የተጠራጠሩት ሰዎች በጣም ጥቂት ነበሩ። በተለይ ደግሞ በማሳቹሴትስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይኖር የነበረው ክላረንስ በርድስአይ በ1925 ፈጣን የዓሣ ማቀዝቀዣ ዘዴ ከፈለሰፈ በኋላ የኮድ ዓሣ ተፈላጊነት ጨመረ። ዓሣ አጥማጆች ሰፋፊ መረቦችን የሚጎትቱ በናፍጣ የሚሠሩ ትልልቅ ጀልባዎችን መጠቀም ሲጀምሩ ደግሞ የበለጠ ብዛት ያለው ዓሣ መያዝ ቻሉ። ይሁን እንጂ ሁኔታው በዚህ ብቻ የሚያበቃ አልነበረም።

በ1951 አንድ ለየት ያለ መርከብ ዓሣ ለማጥመድ ከብሪታንያ ወደ ግራንድ ባንክስ መጣ። የዚህ መርከብ ርዝመት 85 ሜትር ሲሆን 2,600 ቶን ጭነት የመያዝ አቅም ነበረው። ይህ፣ ዓሦቹ ተጠምደው እንደወጡ አቀዝቅዞ የሚያሽግ በዓለም የመጀመሪያው መርከብ ነው። መርከቡ ከኋላው በኩል ሰፊውን መረብ የሚጠቀልል ማሽን ያለው ሲሆን በታችኛው ወለል ላይ ደግሞ ብልት እያወጡ የሚያቀዘቅዙ ፈጣን ማሽኖች ተደርድረዋል። መርከቡ ዓሣ ያለበትን ቦታ የሚጠቁሙ እንደ ራዳር ያሉ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ተጠቅሞ ዓሦች እጅብ ብለው የሚገኙበትን ቦታ በማግኘት ሳምንቱን ሙሉ ሌት ተቀን ዓሣ ይሰበስባል።

ሌሎች አገሮችም የዓሣ ንግዱ ትርፋማ እንደሆነ ስለተገነዘቡ ወዲያውኑ ከብሪታንያ መርከብ ጋር የሚመሳሰሉ መርከቦችን ባሕሩ ላይ በማሰማራት በሰዓት እስከ 200 ቶን የሚደርስ ዓሣ ይሰበስቡ ጀመር። አንዳንዶቹ መርከቦች 8,000 ቶን ጭነት የመያዝ አቅም የነበራቸው ሲሆን 400 ሰዎችን የሚይዝ ትልቅ አውሮፕላን መዋጥ የሚችሉ ትልልቅ መረቦች ነበሯቸው።

ዳግም እንዳያንሰራራ ሆኖ ተሟጠጠ

“በ1970ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይም እንኳ አብዛኞቹ ሰዎች በውቅያኖስ ውስጥ ያለው ሀብት ፈጽሞ አያልቅም የሚለውን የተሳሳተ ሐሳብ እንደያዙ ነበር” በማለት ኦሽንስ ኢንድ የተሰኘው መጽሐፍ ተናግሯል። በ1980ዎቹ ዓመታት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ግዙፍ መርከቦች በግራንድ ባንክስ ላይ ዓሣ ሲያጠምዱ ቆይተዋል። በዚህ ወቅት የሳይንስ ሊቃውንት ኮድ ዓሣ ሊያልቅ መቃረቡን አስጠነቀቁ። ይሁን እንጂ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚተዳደሩት ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ፖለቲከኞች ጠንከር ያለ ውሳኔ ለማሳለፍ ወኔው አልነበራቸውም። በመጨረሻም በ1992 የሳይንስ ሊቃውንት ኮድ ዓሣ በ30 ዓመታት ውስጥ 98.9 በመቶ እንደሚቀንስ አመለከቱ፤ ይህ በእርግጥ አስደንጋጭ ነበር! በመሆኑም በግራንድ ባንክስ ላይ ኮድ ዓሣ ማጥመድ ታገደ። ይሁን እንጂ ውሳኔው ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ነበር። በዓለም ላይ ዓሣ በብዛት ይገኝባቸው ከነበሩት ቦታዎች አንዱ የሆነው ግራንድ ባንክስ በአሰሳ ከተገኘ ከአምስት መቶ ዓመት በኋላ በውስጡ ያሉት ዓሦች ተሟጠጡ።

ዓሣ አጥማጆች ኮድ ዓሣ በፍጥነት ይራባል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። ይሁን እንጂ ኮድ የሚኖረው ከ20 ዓመታት በላይ ሲሆን የመጨረሻው የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ረጅም ጊዜ ይወስድበታል። ከ1992 ወዲህ ባሉት ዓመታት ተስፋ የተደረገው ነገር አልተፈጸመም።

በዓሣ ማጥመድ መስክ የተከሰተ ዓለም አቀፍ ቀውስ

በግራንድ ባንክስ የደረሰው አስደንጋጭ ሁኔታ የዓሣ ማጥመድ ኢንዱስትሪው ለገጠመው ዓለም አቀፍ ችግር ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። በ2002 የብሪታንያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንደተናገሩት “ከዓለም የዓሣ ሀብት ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ተሟጥጦ ሊያልቅ የቀረው በጣም ጥቂት ነው።” የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ብዙ የዓሣ ዝርያዎች መካከል ቱና የሚባሉት ትንንሽ ዓሣዎች፣ ስዎርድፊሽ፣ ሻርክና ሮክፊሽ ይገኙበታል።

ብዙ ባለጠጋ አገሮች የራሳቸውን ዓሣ ማጥመጃ ሥፍራ ካሟጠጡ በኋላ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ዓሣ ማጥመጃ ቦታ እየፈለጉ ነው። ለምሳሌ ያህል በጣም ብዙ ዓሣ ከሚገኝባቸው የዓለም አካባቢዎች ውስጥ አንዳንዶቹ የሚገኙት በአፍሪካ የባሕር ዳርቻዎች ነው። ብዙ የአፍሪካ መሪዎች የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበት ምንጭ ስለሚፈልጉ ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ፈቃድ ለመከልከል ድፍረት የላቸውም። የአገሬው ሰዎች የዓሣ ሀብታቸው በመሟጠጡ ምክንያት ቢናደዱ ምንም አያስገርምም። 

ከልክ በላይ ዓሣ ማጥመድ የማይቆመው ለምንድን ነው?

ከውጭ ሆኖ ለሚያየው ሰው መፍትሔው ቀላል ሊመስለው ስለሚችል ‘ከልክ በላይ እንዳያጠምዱ ለምን አይከለክሏቸውም’ ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም። ዓሣ የማጥመዱን ሥራ ለማከናወን የሚያስፈልጉትን ዕቃዎች ለማሟላት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። በመሆኑም እያንዳንዱ ዓሣ አጥማጅ እሱ ሥራውን መቀጠል እንዲችል ሌሎች እንዲያቆሙ ይጠብቃል። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ማናቸውም አያቆሙም። ከዚህም በላይ መንግሥታት ብዙውን ጊዜ ዓሣ በማጥመዱ ሥራ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ፈሰስ ስለሚያደርጉ ለችግሩ በመንስኤነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው። ኢሹስ ኢን ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ የተሰኘ መጽሔት እንዲህ ይላል፦ “ብዙውን ጊዜ አገሮች [የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት] ለዓሣ ሀብት ጥበቃ ያወጣቸውን ግቦች የሚመለከቷቸው በሌሎች አገሮች ላይ እንጂ በእነሱ ላይ እንደሚሠሩ ደንቦች አድርገው አይደለም።”

ለመዝናኛ ሲሉ ዓሣ የሚያጠምዱ ሰዎችም ከተጠያቂነት አያመልጡም። ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔት በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገን አንድ ጥናት ጠቅሶ እንደዘገበው “ለመዝናኛ ሲሉ ዓሣ የሚያጠምዱ ሰዎች፣ በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ዙሪያ ከመጠን በላይ እንደተጠመዱ ከተነገረላቸው የዓሣ ዝርያዎች ውስጥ 64 በመቶ ለሚሆኑት ተጠያቂዎች ናቸው።” ለመዝናኛም ይሁን ለንግድ ሲሉ ዓሣ የሚያጠምዱ ሰዎች ከፍተኛ ተሰሚነት ስላላቸው ፖለቲከኞች ተወዳጅነት የሚያስገኝላቸውን እንጂ ለዓሣ ሀብት ጥበቃ የሚበጀውን ነገር አያደርጉም።

ታዲያ በመላው ዓለም የሚገኙት የዓሣ ማጥመጃ ቦታዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይችል ይሆን? ቦይስ ቶርን ሚለር ዘ ሊቪንግ ኦሽን በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “ሰዎች በአስተሳሰባቸው ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ካላደረጉ በስተቀር በውቅያኖስ ውስጥ ያሉትን የዓሣ ዝርያዎች የሚታደግ ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ምንም ነገር የለም” ብለዋል። ደስ የሚለው ነገር፣ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ወደፊት የመላዋን ምድር ደህንነት የሚያረጋግጥ መንግሥት አቋቁሟል።—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ጆን ካቦት የተወለደው በጣሊያን ሲሆን እዚያም ጆቫኒ ካቦቶ ተብሎ ይጠራ ነበር። በ1480ዎቹ ዓመታት ወደ ብሪስቶል፣ እንግሊዝ የሄደ ሲሆን በ1497 ያደረገውን የባሕር ጉዞ የጀመረው ከብሪስቶል ነው።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ተቀነጨበ ሐሳብ]

በቡልዶዘር እንደተመነጠሩ ደኖች ሁሉ ከመጠን በላይ ዓሣ የተጠመደባቸው ባሕሮችም ውድመት ደርሶባቸዋል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ዓሣ ከሚጠመድባቸው ቦታዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ወይም ከመጠን በላይ ጥቅም ላይ ውለዋል አሊያም ተሟጥጠዋል።’—የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ አምስተኛ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ከእንስሳት የሚገኘውን ፕሮቲን በዋነኝነት የሚያገኘው ከዓሣ ነው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካምቦዲያ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለንግድ ሲባል የተጠመዱ ዓሦች፣ አላስካ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Janis Miglavs/DanitaDelimont.com

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ከላይ፦ © Mikkel Ostergaard/Panos Pictures; መሃል፦ © Steven Kazlowski/SeaPics.com; ከታች፦ © Tim Dirven/Panos Pictures