በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?​—ክፍል 2

ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?​—ክፍል 2

የወጣቶች ጥያቄ

ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?​—ክፍል 2

ከታች ካሉት ነጥቦች በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ለየትኛው ነው? በቅደም ተከተል አስቀምጣቸው።

․․․․․ የግል ሚስጥሬ

․․․․․ ጊዜዬ

․․․․․ በሌሎች ዘንድ ያለኝ ስም

․․․․․ ከሌሎች ጋር ያለኝ ጓደኝነት

ከላይ ካሉት ነጥቦች መካከል የመጀመሪያውን ቦታ የሰጠኸው ለየትኛው ነው? ማኅበራዊ ድረ ገጾችን የምትጠቀም ከሆነ የመጀመሪያውን ቦታ የሰጠኸው ነጥብም ሆነ የቀሩት ሦስቱ ለአደጋ የተጋለጡ ይሆናሉ።

ታዲያ አንተ የማኅበራዊ ድረ ገጽ አካውንት ሊኖርህ ይገባል? የምትኖረው ከወላጆችህ ጋር ከሆነ ይህን የሚወስኑት እነሱ ናቸው። * (ምሳሌ 6:20) እንደማንኛውም የኢንተርኔት አገልግሎት ሁሉ ማኅበራዊ ድረ ገጽም የራሱ የሆነ ጥቅምና ጉዳት ሊኖረው ይችላል። ወላጆችህ እንዲህ ባለው ድረ ገጽ ላይ አካውንት እንድትከፍት የማይፈልጉ ከሆነ ውሳኔያቸውን ማክበር ይኖርብሃል።​—ኤፌሶን 6:1

በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆችህ በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንድትጠቀም ከፈቀዱልህ ከአደጋዎቹ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው ዓምድ ሥር በሐምሌ 2011 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣው ርዕስ በቁም ነገር ሊታሰብባቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮችን ጠቅሷል፤ እነሱም የግል ሚስጥርህና ጊዜህ ናቸው። በዚህ እትም ላይ ደግሞ በሌሎች ዘንድ ያለህን ስምና ከሌሎች ጋር ያለህን ጓደኝነት በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳቦችን እንመለከታለን።

በሌሎች ዘንድ ያለህ ስም

በሌሎች ዘንድ ያለህን ስም መጠበቅ ሲባል ሌሎች ስለ አንተ መጥፎ ነገር እንዲያስቡ የሚያደርግ ምንም ነገር እንዳይኖር መጠንቀቅ ማለት ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ምንም ጭረት የሌለው አዲስ መኪና አለህ እንበል። መኪናህ በዚሁ ይዞታው ቢቆይልህ ደስ አይልህም? በራስህ ግዴለሽነት የተነሳ መኪናህ ተጋጭቶ ጉዳት ቢደርስበት ምን ይሰማሃል?

ማኅበራዊ ድረ ገጽ የምትጠቀምም ከሆነ በሌሎች ዘንድ ያለህ ስም ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥመው ይችላል። ካራ የተባለች ወጣት “በድረ ገጹ ላይ እንደ ቀልድ ባስቀመጥከው ፎቶ ወይም በጻፍከው አስተያየት የተነሳ ስምህ ሊጠፋ ይችላል” ስትል ተናግራለች። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት ነገሮች እንዴት ስምህን ሊያጠፉት እንደሚችሉ አስብ፦

ፎቶዎችህ። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሌሎች ምንጊዜም መልካም ነገር ስታደርጉ ይመልከቷችሁ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:12 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ያሉ ፎቶዎችን አይተህ ከሆነ ምን አስተውለሃል?

“በጣም የማከበረው ሰው እንኳ አንዳንድ ጊዜ እንደሰከረ የሚያሳዩ ፎቶዎችን ያስቀምጣል።”​የ19 ዓመቷ አና

“ሰውነታቸው እንዲታይላቸው የሚያደርግ ፎቶ ተነስተው የሚያስቀምጡ ወጣቶችን አውቃለሁ። በድረ ገጻቸው ላይ ሲታዩ በእውን ከምናውቃቸው ፈጽሞ የተለዩ ናቸው።”​የ19 ዓመቷ ካራ

በማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ (1) የጾታ ስሜት የሚቀሰቅስ አለባበስ ለብሶ የሚያሳይ ወይም (2) እንደሰከረ የሚያሳይ ፎቶ የሚያስቀምጥ ሰው ምን ዓይነት ባሕርይ አለው ብለህ ታስባለህ?

1

2

የምትጽፈው አስተያየት። ኤፌሶን 4:29 “የበሰበሰ ቃል [“ጸያፍ ንግግር፣” ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ቨርሽን] ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ” ይላል። አሳፋሪ ንግግሮች፣ ሐሜት ወይም ሥነ ምግባር የጎደላቸው ርዕሶች በማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት በሚደረጉ ውይይቶች ውስጥ ቀስ በቀስ ሰርገው እንደሚገቡ አንዳንዶች አስተውለዋል።

“ሰዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የፈለጉትን መጻፍ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ስትናገረው በጣም የሚቀፍህ ነገር ስትጽፈው ያን ያህል ላይቀፍህ ይችላል። የምትጽፈው ነገር ስድብ ባይሆንም እንኳ የምትጠቀምባቸው ቃላት የሚያሽኮረምሙ፣ ዓይን ያወጡ ወይም ጸያፍ ሊሆኑ ይችላሉ።”​የ19 ዓመቷ ዳንዬል

ሰዎች ኮምፒውተር ላይ ሲሆን የፈለጉትን መጻፍ እንደሚችሉ የሚሰማቸው ለምን ይመስልሃል?

․․․․․

ድረ ገጹ ላይ የምታስቀምጣቸው ፎቶዎችና የምትጽፋቸው አስተያየቶች የሚፈጥሩት ችግር ይኖራል? እንዴታ! በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው ጄን “ይህ ጉዳይ በትምህርት ቤት ትልቅ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር” ብላለች። “ሥራ ቀጣሪዎች የአመልካቹን ማንነት ለመገምገም የእሱን ድረ ገጽ እንደሚመለከቱ ስንወያይ ነበር” በማለት ተናግራለች።

ዶክተር ቢ. ጄ. ፎግ ሠራተኞችን መቅጠር ሲፈልጉ የአመልካቾቹን ድረ ገጽ እንደሚመለከቱ ፌስቡክ ፎር ፓረንትስ በተባለው መጽሐፍ ላይ ገልጸዋል። “ይህን ማድረግ እንደሚጠበቅብኝ ይሰማኛል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “የአመልካቹ ድረ ገጽ ውስጥ መግባት ከቻልኩና የማይረቡ ነገሮችን ካየሁ ያን ሰው አልፈልገውም። ስለዚህ አልቀጥረውም። ለምን? ምክንያቱም አብረውኝ የሚሠሩ ሰዎች ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው እንዲሆኑ እፈልጋለሁ።”

ክርስቲያን ከሆንክ ደግሞ ከዚህ ይበልጥ ሊያሳስብህ የሚገባ ነገር አለ፤ በድረ ገጹ ላይ የምታስቀምጣቸው ነገሮች በእምነት አጋሮችህም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በምንም መንገድ ማሰናከያ የሚሆን ነገር እንዲኖር አናደርግም” ሲል ጽፏል።​—2 ቆሮንቶስ 6:3፤ 1 ጴጥሮስ 3:16

ምን ልታደርግ ትችላለህ?

ወላጆችህ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን እንድትጠቀም ከፈቀዱልህ በድረ ገጹ ላይ ያስቀመጥካቸውን ፎቶዎች ተመልከትና እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ፦ ‘እነዚህ ፎቶዎች ስለ እኔ ምን መልእክት ያስተላልፋሉ? በእርግጥ ሰዎች እኔን እንዲያውቁኝ የምፈልገው በዚህ ሁኔታ ነው? ወላጆቼ፣ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ወይም ሥራ ሊቀጥረኝ የሚፈልግ ሰው እነዚህን ፎቶዎች ቢመለከቷቸው አፍራለሁ?’ ለመጨረሻው ጥያቄ የምትሰጠው መልስ አዎ የሚል ከሆነ ማስተካከያ አድርግ። የ21 ዓመቷ ኬት ያደረገችው ይህንን ነው። “አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ በድረ ገጼ ላይ ያደረግኩትን ፎቶ አይቶ አነጋገረኝ” ብላለች። አክላም “እንዲህ በማድረጉም አመስጋኝ ነኝ። ይህን ያደረገው ስሜ እንዳይጠፋ ብሎ እንደሆነ አውቃለሁ” ስትል ተናግራለች።

በተጨማሪም በድረ ገጽህ ላይ ያሰፈርካቸውን አስተያየቶችም ሆነ ሌሎች የጻፏቸውን ነገሮች በጥንቃቄ መርምር። “የማይረባ ንግግርም ሆነ ጸያፍ ቀልድ” ካየህ ዝም አትበል። (ኤፌሶን 5:3, 4) የ19 ዓመቷ ጄን “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚጽፏቸው አስተያየቶች መጥፎ ቃላትን የያዙ ወይም ሁለት ዓይነት ትርጉም ያላቸው ናቸው” ስትል ተናግራለች። “እርግጥ ነው፣ ያንን የጻፍከው አንተ ባትሆንም እንኳ በአንተ ድረ ገጽ ላይ እስከተቀመጠ ድረስ ስለ አንተ መጥፎ ነገር ማስተላለፉ አይቀርም።”

ስምህ እንዳይጠፋ የምትፈልግ ከሆነ ስለምታስቀምጣቸው ፎቶዎችና ስለምትጽፋቸው አስተያየቶች ምን ዓይነት ገደብ ማበጀት ይኖርብሃል?

․․․․․

ከሌሎች ጋር ያለህ ጓደኝነት

አዲስ መኪና ቢኖርህ ዝም ብለህ ማንንም ሰው ታሳፍራለህ? ወላጆችህ የማኅበራዊ ድረ ገጽ አካውንት እንድትከፍት የሚፈቅዱልህ ከሆነ ጓደኞችህ እንዲሆኑ የምትጋብዛቸውን ወይም ጓደኛ አድርገህ የምትቀበላቸውን ሰዎች በተመለከተም ተመሳሳይ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅብሃል። በዚህ ረገድ ምን ያህል መራጭ መሆን ይኖርብሃል?

“አንዳንድ ሰዎች ዓላማቸው በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን ጓደኛ ማድረግ ብቻ ነው። በደንብ የማያውቋቸውን ሰዎች እንኳ ጓደኛ አድርገው ይቀበላሉ።”​የ16 ዓመቷ ናዪሻ

“ማኅበራዊ ድረ ገጾች ድሮ ታውቋቸው የነበሩ ሰዎችን ያገናኟችኋል። አንዳንድ ጊዜ ግን ከእነዚህ ሰዎች ጋር እንደገና አለመገናኘቱ የተሻለ ይሆናል።”​የ25 ዓመቷ ኤለን

ምን ልታደርግ ትችላለህ?

የመፍትሔ ሐሳብ፦ መቃኘትና ማስተካከያ ማድረግ። የጓደኞችህን ዝርዝር ከቃኘህ በኋላ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘኸው ማስተካከያ አድርግ። ይህን ባደረግክ ቁጥር እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦

1. ‘ግለሰቡን በኢንተርኔት ከማውቀው ውጭ ምን ያህል አውቀዋለሁ?’

2. ‘ይህ ሰው የሚያስቀምጣቸው ፎቶዎችና የሚጽፋቸው አስተያየቶች ምን ዓይነት ናቸው?’

3. ‘ይህ ሰው በሕይወቴ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?’

“አብዛኛውን ጊዜ በየወሩ ‘የጓደኞቼን ዝርዝር’ እቃኛለሁ። ዝርዝሩ ላይ ብዙም የማይጥመኝ ወይም በደንብ የማላውቀው ሰው ካለ ከዝርዝሩ ውስጥ አጠፋዋለሁ።”​የ17 ዓመቷ ኢቫና

የመፍትሔ ሐሳብ፦ ‘ጓደኛ የምትመርጥበትን መስፈርት’ ማውጣት። ሌላ ጊዜ በጓደኛ ምርጫህ ረገድ እንደምታደርገው ሁሉ በማኅበራዊ ድረ ገጽም ላይ ጓደኞችህ እንዲሆኑ የምትጋብዛቸውንም ሆነ ጓደኛ አድርገህ የምትቀበላቸውን ሰዎች በተመለከተ ተመሳሳይ ገደቦችን ማበጀት ይኖርብሃል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ለምሳሌ ያህል ሊን የተባለች ወጣት “የእኔ መስፈርት ይህ ነው፦ የማላውቅህ ከሆነ ጓደኛ እንድሆንህ የምታቀርብልኝን ግብዣ አልቀበልም። በድረ ገጽህ ላይ ደስ የማይለኝ ነገር ካየሁ ‘ከጓደኞቼ ዝርዝር’ ውስጥ እሰርዝሃለሁ፤ ከዚያ በኋላ የምታቀርብልኝን ግብዣም አልቀበልም” ስትል ተናግራለች። ሌሎችም ተመሳሳይ ገደቦችን አበጅተዋል።

“ዝም ብዬ ማንንም ሰው ‘ጓደኛ’ አላደርግም። እንዲህ ማድረግ አደገኛ ሊሆን ይችላል።”​የ21 ዓመቷ ኤሪን

“ድሮ አብሬያቸው እማር የነበሩ ልጆች በማኅበራዊ ድረ ገጽ አማካኝነት ጓደኛቸው እንድሆን ጋብዘውኝ ነበር። ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ ከእነዚህ ልጆች ጋር ላለመግጠም ከፍተኛ ጥረት አደርግ ነበር፤ ታዲያ አሁን ጓደኛቸው የምሆንበት ምን ምክንያት አለኝ?”​የ21 ዓመቱ አሌክስ

ከዚህ በታች አንተ ‘ጓደኛ የምትመርጥበት መስፈርት’ ምን እንደሆነ ጻፍ።

․․․․․

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 ንቁ! መጽሔት የትኛውንም ዓይነት ማኅበራዊ ድረ ገጽ ለይቶ በመጥቀስ አይደግፍም አሊያም አያወግዝም። ክርስቲያኖች የኢንተርኔት አጠቃቀማቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር እንደማይቃረን ማረጋገጥ አለባቸው።​—1 ጢሞቴዎስ 1:5, 19

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ከመልካም ስምና ከብልጽግና አንዱን መምረጥ ካለብህ መልካም ስምን ምረጥ” ይላል።​—ምሳሌ 22:1 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለምን ወላጆችህን አትጠይቃቸውም?

በዚህ ርዕስና በሐምሌ 2011 ንቁ! መጽሔት ላይ በወጣው “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው ዓምድ ሥር ያሉትን ነጥቦች ከወላጆችህ ጋር ተወያይባቸው። የኢንተርኔት አጠቃቀምህ (1) የግል ሚስጥርህን፣ (2) ጊዜህን፣ (3) በሌሎች ዘንድ ያለህን ስም እንዲሁም (4) ከሌሎች ጋር ያለህን ጓደኝነት እንዴት ሊነካብህ እንደሚችል ተወያዩ።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

ልጆቻችሁ ስለ ኢንተርኔት አጠቃቀም ከእናንተ የተሻለ ያውቁ ይሆናል። ሆኖም የእናንተን ያህል የማመዛዝን ችሎታ የላቸውም። (ምሳሌ 1:4፤ 2:1-6) ኢንተርኔት የሚያስከትለውን አደጋ መከላከል ስለሚቻልበት መንገድ የሚያጠኑ ፔሪ አፍታብ የተባሉ ባለሙያ “ልጆች ስለ ቴክኖሎጂ የተሻለ እውቀት አላቸው። ወላጆች ደግሞ ስለ ሕይወት የተሻለ እውቀት አላቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በጣም ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል። ልጃችሁ በእነዚህ ድረ ገጾች ለመጠቀም የሚያስችል ብስለት አለው? ይህን የምትወስኑት እናንተ ናችሁ። መኪና ማሽከርከር፣ የባንክ ሒሳብ መክፈት ወይም ክሬዲት ካርድ መጠቀም የራሱ የሆነ አደጋ እንዳለው ሁሉ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መጠቀምም የራሱ የሆኑ አደጋዎች አሉት። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

የግል ሚስጥር። ብዙ ወጣቶች ዝርዝር መረጃዎችን በድረ ገጽ ላይ ማስቀመጥ ምን ሊያስከትል እንደሚችል አይገነዘቡም። የት እንደሚኖሩ፣ የት እንደሚማሩ ወይም በምን ሰዓት ቤት እንደሚገኙና እንደማይገኙ መግለጻቸው የቤተሰባችሁን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።

ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ልጆቻችሁ ትንንሽ በነበሩበት ጊዜ መንገድ ሲያቋርጡ በሁለቱም አቅጣጫ አይተው እንዲሻገሩ ትመክሯቸው ነበር። ከፍ ካሉ በኋላ ደግሞ ኢንተርኔት በሚጠቀሙበት ጊዜ ምን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ማስተማር ይኖርባችኋል። “የወጣቶች ጥያቄ” በሚለው ዓምድ ሥር ባለፈው ወር በወጣው ርዕስ ላይ የሚገኘውን ስለ ግል ሚስጥር የሚናገረውን ሐሳብ አንብቡት። በተጨማሪም የጥቅምት 2008 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 3-9⁠ን ተመልከቱ። ከዚያም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኝ ልጃችሁ ጋር ተወያዩበት። በኢንተርኔት አጠቃቀም ረገድ ጥንቃቄ ማድረግን በተመለከተ በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ “ትክክለኛ ፍርድንና አስተውሎ መለየትን” ለመቅረጽ ጥረት አድርጉ።​—ምሳሌ 3:21

ጊዜ። ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መጠቀም ሱስ ሊሆን ይችላል። ሪክ የተባለው የ23 ዓመት ወጣት “አካውንት ከከፈትኩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከዚያ ላይ መነሳት አልቻልኩም” ሲል ተናግሯል። “ፎቶዎችንና ሌሎች የጻፏቸውን አስተያየቶች በመመልከት ብዙ ሰዓት አጠፋለሁ።”

ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? በጥር 2011 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መጠቀም ሱስ ሆኖብኛል?” የሚለውን ርዕስ ከልጆቻችሁ ጋር አንብባችሁ ተወያዩበት። በተለይ ደግሞ በገጽ 26 ላይ ለሚገኘው “ማኅበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትበት ድረ ገጽ ሱሰኛ ነበርኩ” ለሚለው ሣጥን ልዩ ትኩረት ስጡ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ልጃችሁ “በልማዶቹ ልከኛ” እንዲሆንና በኢንተርኔት አጠቃቀሙ ረገድም የጊዜ ገደብ እንዲያበጅ እርዱት። (1 ጢሞቴዎስ 3:2) ከኢንተርኔት ውጭም ከሌሎች ጋር ግንኙነት መመሥረት የሚቻልበት መንገድ እንዳለ አሳስቡት!

በሌሎች ዘንድ የሚኖራቸው ስም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ልጆች የሚያደርጉት ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ማንነታቸውን ያሳያል” ይላል። (ምሳሌ 20:11 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ይህ አባባል በኢንተርኔት አጠቃቀምም ረገድ በሚገባ ይሠራል! ከዚህም በላይ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ለብዙ ሰዎች እይታ የተጋለጡ ስለሆኑ ልጃችሁ እዚያ ላይ የሚያስቀምጠው ነገር የእሱን ስም ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡንም ስም ሊያጠፋ ይችላል።

ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ወጣቶች በድረ ገጻቸው ላይ የሚያስቀምጡት ነገር የእነሱን ማንነት እንደሚያንጸባርቅ ማወቅ አለባቸው። በተጨማሪም አንድ ጊዜ ኢንተርኔት ላይ የተቀመጠ ነገር ሊጠፋ እንደማይችል ሊገነዘቡ ይገባል። ዶክተር ግዌን ሹርገን ኦኪፍ ሳይበርሴፍ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ “በኢንተርኔት ላይ የተቀመጡ ነገሮች በቋሚነት እዚያው እንደሚቀሩ ልጆች በቀላሉ ላይረዱ ይችላሉ፤ ሆኖም ስለዚህ ጉዳይ መማራቸው ወሳኝ ነገር ነው” በማለት ገልጸዋል። “ልጆች በኢንተርኔት አጠቃቀም ረገድ ሊኖራቸው የሚገባውን ምግባር በተመለከተ ማስረዳት የሚቻልበት አንዱ መንገድ አንድን ሰው በአካል ቢያገኙት ሊሉት የማይችሉትን ነገር በኢንተርኔትም ማለት እንደሌለባቸው ማስገንዘብ ነው።”

ከሌሎች ጋር ያላቸው ጓደኝነት። የ23 ዓመቷ ታንያ “ብዙ ወጣቶች በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ መሆን ይፈልጋሉ፤ ስለሆነም የማያውቋቸውን ወይም ጥሩ ሥነ ምግባር የሌላቸውን ሰዎች ‘ጓደኛ’ አድርገው ለመቀበል ፈቃደኞች ይሆናሉ” በማለት ተናግራለች።

ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ልጃችሁ ‘ጓደኛ የሚመርጥበትን መስፈርት’ እንዲያወጣ እርዱት። ለምሳሌ ያህል የ22 ዓመቷ አሊሲያ አንድ ሰው እንዲሁ የጓደኞቿ ጓደኛ ስለሆነ ብቻ ጓደኛ አድርጋ አትቀበለውም። “ማንነትህን ካላወቅኩ ወይም በአካል አግኝቼህ የማላውቅ ከሆነ የጓደኛዬ ጓደኛ ስለሆንክ ብቻ ጓደኛ አድርጌ አልቀበልህም” ስትል ተናግራለች።

ቲም እና ጁሊያ የተባሉ ባልና ሚስት የልጃቸውን ጓደኞችና ድረ ገጿ ላይ የምታስቀምጣቸውን ነገሮች ለመቆጣጠር ሲሉ በማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ አካውንት ከፍተዋል። ጁሊያ “ልጃችን የጓደኞቿ ዝርዝር ውስጥ እንድታስገባን ጠየቅናት” በማለት ተናግራለች። “በኢንተርኔት የምታገኛቸው ሰዎች ቤታችን የተጋበዙ ያህል ነው። ማንነታቸውን ማወቅ እንፈልጋለን።”

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ መኪና በግዴለሽነት ከተነዳ ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል ሁሉ በድረ ገጽህ ላይ ጨዋነት የጎደላቸውን ፎቶዎችና አስተያየቶችን የምታስቀምጥ ከሆነም ስምህ ሊጠፋ ይችላል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የማታውቀው ሰው እንድትሸኘው ስለጠየቀህ ብቻ መኪናህ ላይ ታሳፍረዋለህ? ታዲያ አንድን የማታውቀውን ሰው በኢንተርኔት አማካኝነት ጓደኛ አድርገህ እንዴት ትቀበለዋለህ?