በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቲንጋቲንጋ—ፈገግ የሚያሰኝ የሥዕል ጥበብ

ቲንጋቲንጋ—ፈገግ የሚያሰኝ የሥዕል ጥበብ

ቲንጋቲንጋ—ፈገግ የሚያሰኝ የሥዕል ጥበብ

“ቲንጋቲንጋ አካባቢያችንን በልጅ ዓይን እንድናይ የሚያስችል የሥዕል ጥበብ ነው።” ይህን የተናገሩት የቲንጋቲንጋ ሥነ ጥበብ የኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዳንኤል ኦጋስታ ናቸው። አክለውም “አስቂኝ፣ አስደሳችና በቀለማት ያሸበረቀ” ሲሉ ገልጸውታል። ቲንጋቲንጋ የአፍሪካን በተለይም የዚህ ጥበብ መገኛ የሆነችውን የታንዛኒያን የዱር እንስሳትና ባሕል የሚያሳይ የሥዕል ጥበብ ነው።

ቲንጋቲንጋ የሚባለው የአሳሳል ስልት ስያሜውን ያገኘው ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ጥበብ ካስተዋወቀው ከኤድዋርድ ሰይድ ቲንጋቲንጋ ሲሆን ይህ ሰው የተወለደው በ1932 ነው። ኤድዋርድ እያደገ ሲሄድ እሱ በሚኖርበት በደቡባዊ ታንዛኒያ ያሉት ገጠራማ አካባቢዎችና የዱር እንስሳት ልዩ ስሜት ሳይፈጥሩበት አልቀረም። በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ሳለ ሥራና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ቀዬውን ትቶ ሄደ። በኋላም የታንዛኒያ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ዳሬ ሰላም በመሄድ በአትክልተኝነት ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ። ኤድዋርድ በውስጡ የተቀበረውን የጥበብ ተሰጥኦ ማታ ማታ በሙዚቃና በዳንስ ይገልጽ ነበር፤ እንዲያውም ከጊዜ በኋላ በዚህ ሙያው ታዋቂ መሆን ችሎ ነበር።

በ1968 በኤድዋርድ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነገር ተከሰተ። በዳሬ ሰላም፣ ሙሂምቤሌ በሚባል የሕዝብ ሆስፒታል ውስጥ የመንግሥት ሥራ አገኘ። እዚያ እያለም በቂ ጊዜ በማግኘቱ የልጅነት ትዝታዎቹንና ልዩ ስሜት የሚፈጥሩበትን ነገሮች በራሱ የአሳሳል ስልት መግለጽ ጀመረ። ቲንጋቲንጋ የተባለው የአሳሳል ስልት የተፈጠረው በዚህ ጊዜ ነበር። ኤድዋርድ ለሥዕል መሥሪያ ተብለው የሚዘጋጁ ብሩሾችን፣ ቀለሞችንና ሌሎች ነገሮችን የማግኘት አጋጣሚ አልነበረውም። ስለዚህ ከአካባቢው የሕንፃ መሣሪያ መደብር ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ተራ ነገሮች ተጠቅሞ መሳል ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ ሥዕሉን ለመሥራት የሚጠቀመው የብረት ቀለም ሲሆን “ሸራው” ደግሞ ፋይዚት ነበር፤ ፋይዚቱ በአንዱ ገጽ ልሙጥ ስለሆነ የሚያብረቀርቁ ሥዕሎችን ለመሥራት ያመቻል።

የኤድዋርድ ሥዕሎች የተወሳሰቡ አልነበሩም። መደቡን አንድ ወይም ሁለት ዓይነት ቀለሞችን ከቀባ በኋላ በላዩ ላይ አንድ ነገር ብቻ ማለትም በአፍሪካ የሚገኝን የአንድ እንስሳ ምስል ይስል ነበር፤ ምስሉን የሚሠራው ደማቅ ቀለሞችን በመጠቀምና የእንስሳውን የተለየ ገጽታ አጋንኖ በሚገልጽ መንገድ ነበር። በሥዕሉ ላይ መልክአ ምድሮችን ወይም ሌሎች ዝርዝር ነገሮችን አይጨምርም ነበር።

ኤድዋርድ ሥዕሉን በሚሠራበት ጊዜ ዘመዶቹና በጣም የሚቀርባቸው ጥቂት ሰዎች እንዲመለከቱ ይፈቅድላቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የእሱ “ደቀ መዝሙር” ሆኑ፤ እንዲሁም የኤድዋርድ የአሳሳል ስልት ታዋቂነት እያገኘ ሄደ።

ከመጀመሪያው አንስቶ የቲንጋቲንጋ ሥዕሎች የሚሳሉት ደማቅ ቀለማትን በመጠቀም ሲሆን ምስሎቹም የሚሠሩት ቀለል ባለና ልዩ የሚያደርጋቸውን ገጽታ አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ ነው። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በዚህ የአሳሳል ስልት ለውጥ በማድረግ በአንድ ሥዕል ውስጥ በርካታ ዝርዝር ነገሮችን ማካተት ተጀመረ። እንዲያውም አንዳንድ ሠዓሊዎች ሰዎችን፣ የተለያዩ እንስሳትንና ሌሎች ነገሮችን የያዙ ሥዕሎችን መሥራት ጀመሩ።

መነሻ ሐሳብ

በአፍሪካ ውስጥ ያሉ የተለያዩ እንስሳትንና ዕፅዋትን በመመልከት የቲንጋቲንጋ ሥዕልን ለመሥራት የሚያስችሉ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የመነሻ ሐሳቦችን ማግኘት ይቻላል፤ ከእነዚህ መካከል አጋዘን፣ ጎሽ፣ ዝሆን፣ ቀጭኔ፣ ጉማሬ፣ አንበሳ፣ ጦጣ፣ የሜዳ አህያና ሌሎች እንስሳት አልፎ ተርፎም ደማቅ ቀለም ያላቸው አበቦች፣ ዛፎች፣ ወፎችና ዓሦች ይጠቀሳሉ። ከአብዛኞቹ ሥዕሎች በስተጀርባ በሰሜን ምሥራቅ ታንዛኒያ የሚገኘውንና የአፍሪካ ረጅሙ ተራራ የሆነውን ኪሊማንጃሮን ማየት የተለመደ ነው።

በዛሬው ጊዜ ያሉ የቲንጋቲንጋ ሥዕሎች የአፍሪካን ሕዝብና ባሕል ለማሳየትም ይሞክራሉ። ሥዕሎቹ ግርግር የበዛበትን የገበያ ስፍራ፣ ሰዎች በሆስፒታል ውስጥ ሕመምተኞችን ሲጠይቁ ወይም የገጠር ሕይወትን የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ።

የቲንጋቲንጋ የሥዕል ጥበብ፣ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሥነ ጥበብ ተሰጥኦ ያላቸው አፍሪካውያን የውስጥ ስሜታቸውን ለመግለጽ መንገድ ከፍቶላቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኖላቸዋል። ከዚህም በላይ የቲንጋቲንጋ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ መቀመጫውን ዳሬ ሰላም ያደረገ የሠዓሊዎች ማኅበር እስከማቋቋም ደርሰዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ የድሮውን ዘዴ በመከተል ሥዕሎቹን በብረት ቀለም ተጠቅመው ይሠራሉ። ኤድዋርድ ቲንጋቲንጋ፣ ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ (የሞተው በ1972 ነው) እሱ የጀመረው የአሳሳል ስልት ይህን ያህል ተወዳጅ እንደሆነ ሲመለከት በጣም እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም።