በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ​—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 1

መጽሐፍ ቅዱስ​—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 1

መጽሐፍ ቅዱስ​—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 1

“ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ”

ከዚህ እትም ጀምሮ በሚወጡ ስምንት ተከታታይ “የንቁ!” እትሞች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ማለትም በውስጡ ስለያዛቸው ትንቢቶች እንመረምራለን። ይህ ተከታታይ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች ናቸው? ወይስ እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፋቸውን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ? እስቲ ማስረጃዎቹን አብረን እንመርምር።

በዘመናችን በስፋት ከሚታዩ ባሕርያት መካከል አንዱ ጥርጣሬ ነው፤ በመሆኑም አንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸው ጥርጣሬ በመጽሐፉ ላይ እምነት እንዳይጥሉ አድርጓቸዋል። የሚያሳዝነው ብዙዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ጊዜ ወስደው መጽሐፉን በሐቀኝነት መርምረው አይደለም። ከዚህ ይልቅ አስተያየት የሚሰጡት፣ ሌሎች ሰዎች በተናገሩት ሐሳብ ላይ ተመሥርተው ነው። አንተ ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት እንደሚኖርህ ተስፋ እናደርጋለን። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኝነት የሚያረጋግጡ አንዳንድ ማስረጃዎችን ወደኋላ መለስ ብለን ለምን አንቃኝም?

ዛሬም ድረስ በክርስቲያኖች፣ በአይሁዶችና በሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ በሚሰጠው በአንድ ሰው ታሪክ ቅኝታችንን እንጀምራለን። ይህ ሰው ዕብራዊ ሲሆን የኖረው ከ2018 እስከ 1843 ዓ.ዓ. ነው። ስሙም አብርሃም ይባላል። *

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት የመጀመሪያዎቹ ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹ በአብርሃም ላይ ያተኮሩ ሲሆን እነዚህ ትንቢቶች እኛንም ጭምር የሚመለከቱ ናቸው። ( “‘ለምድር ሕዝቦች ሁሉ’ የሚሆን በረከት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ እንደሚገልጸው እነዚህ ትንቢቶች የሚከተሉትን ነገሮች ያካትታሉ፦ (1) የአብርሃም ዘሮች ታላቅ ሕዝብ ይሆናሉ። (2) በዚህ ሂደት ውስጥ በባዕድ አገር በባርነት ይኖራሉ። (3) ከዚያም ከባርነት ነፃ ይወጣሉ፤ እንዲሁም የከነዓንን ምድር ይወርሳሉ። እስቲ እነዚህን ነጥቦች በዝርዝር እንመልከት።

ሦስት ጎላ ያሉ ትንቢቶች

ትንቢት 1፦ “ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”​ዘፍጥረት 12:2

ፍጻሜ፦ የአብርሃም ዝርያ የሆኑት የይስሐቅና የያዕቆብ (እስራኤልም ተብሎ ይጠራል) ልጆች የራሱ ነገሥታት ያሉትን የጥንቱን የእስራኤል ብሔር መሥርተዋል።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

● የይስሐቅን፣ የያዕቆብንና የያዕቆብ 12 ልጆችን ጨምሮ የአብርሃም የዘር ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዝርዝር ሰፍሯል። በእስራኤል ወይም በይሁዳ የነገሡ በርካታ ነገሥታትም በዚህ የዘር ሐረግ ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ። ከእነዚህ ነገሥታት መካከል 17ቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በሆኑ የታሪክ ዘገባዎች ላይም ተጠቅሰዋል፤ ይህም የአብርሃም ዝርያዎች በይስሐቅና በያዕቆብ በኩል እንዴት ትልቅ ብሔር እንደሆኑ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር ይስማማል። *

ትንቢት 2፦ “ዘርህ [የአብርሃም] በባዕድ አገር ስደተኛ እንደሚሆን በእርግጥ ዕወቅ፤ . . . በባርነት ተረግጦ ይገዛል። በአራተኛውም ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል።”​ዘፍጥረት 15:13, 16

ፍጻሜ፦ በከነዓን ምድር በተከሰተው ረሃብ ምክንያት ወደ ግብፅ የተሰደዱት የአብርሃም ዝርያዎች መጀመሪያ በመጻተኝነት በኋላ ደግሞ ከጭቃና ከጭድ ጡብ እየሠሩ በባርነት እስከ አራት ትውልድ ድረስ በግብፅ አገር ኖሩ። ከዚህ ትውልድ ውስጥ የአንዱን ቤተሰብ ማለትም የአብርሃም የልጅ ልጅ፣ ልጅ የሆነውን የሌዊን የዘር ሐረግ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በዕድሜ ከገፋው አባቱ ጋር ወደ ግብፅ ከሄደው ከሌዊ ተነስተን አራት ትውልድ ስንቆጥር (1) ሌዊን (2) ልጁ ቀዓትን (3) የልጅ ልጁ እንበረምንና (4) የልጅ ልጁ፣ ልጅ የሆነውን ሙሴን እናገኛለን። (ዘፀአት 6:16, 18, 20) በ1513 ዓ.ዓ. እስራኤላውያንን እየመራ ከግብፅ ያወጣቸው ደግሞ ሙሴ ነው።​— የዘመን ቅደም ተከተሉንና  “ዝንፍ የማይል የጊዜ አጠባበቅ” የሚለውን ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

● ሴማውያን (እንደ ጥንቶቹ ዕብራውያን ያሉ ዘሮች) ረሃብ በሚከሰትበት ጊዜ ከነመንጎቻቸው ወደ ግብፅ እንዲገቡ ይፈቀድላቸው እንደነበረ የሚያረጋግጡ ጥንታዊ የግብፃውያን ጽሑፎችና የአርኪኦሎጂ መረጃዎች እንዳሉ የብሉይ ኪዳንና የቅርብ ምሥራቅ አርኪኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄምስ ሆፍሚየር ገልጸዋል። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ጡብ የሚሠሩ ባሪያዎች እንደነበሩ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለ?

● እስራኤላውያንን በቀጥታ የሚጠቅሱ የግብፃውያን መዛግብት ባይኖሩም ግብፃውያን የባዕድ አገር ሰዎችን ከጭቃና ከጭድ ጡብ ያሠሩ እንደነበር የመቃብር ላይ ሥዕሎቻቸውና የመጽሐፍ ጥቅልሎቻቸው ያረጋግጣሉ። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ተቆጣጣሪዎች፣ ምን ያህል ጡብ መመረት እንዳለበት ኮታ እንደሚያወጡ እንዲሁም ይህንን በጽሑፍ እንደሚያሰፍሩ የግብፃውያን መዛግብት ይገልጻሉ። (ዘፀአት 5:14, 19) ሆፍሚየር አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “እስራኤላውያን በባርነት ቀንበር ይማቅቁ በነበረበት ዘመን ግብፃውያን የባዕድ አገር ሰዎችን የግዳጅ ሥራ ያሠሯቸው እንደነበረ የግብፃውያን የመረጃ ምንጮች ያረጋግጣሉ። በጥቅሉ ሲታይ የጥንቶቹ ዕብራውያን በረሃቡ ዘመን . . . ወደ ግብፅ እንደገቡና ከዚያም በባርነት እንደኖሩ የሚገልጸው ዘገባ እውነተኛ ይመስላል።”

ትንቢት 3፦ “የከነዓንን ምድር በሙሉ . . . ለዘርህ . . . እሰጣለሁ።”​ዘፍጥረት 17:8

ፍጻሜ፦ አዲስ የተቋቋመውን የእስራኤል ብሔር ከግብፅ ያወጣው ሙሴ ቢሆንም በ1473 ዓ.ዓ. የነዌ ልጅ ኢያሱ ሕዝቡን ወደ ከነዓን ምድር አስገብቷል።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

● በጥንታዊቷ ግብፅ ሥልጣኔ ላይ ጥናት አካሂደው የነበሩት ኬነዝ አንደርሰን ኪችን የተባሉ ፕሮፌሰር፣ ጊዜውን በተመለከተ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የተለያየ ሐሳብ ቢኖራቸውም “እስራኤላውያን ወደ ከነዓን መግባታቸውንና በዚያም መስፈራቸውን አምነን ለመቀበል እንገደዳለን” በማለት ተናግረዋል።

● መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢያሱ የከነዓናውያን ከተማ የነበረችውን “አጾርን በእሳት [እንዳቃጠላት]” ይናገራል። (ኢያሱ 11:10, 11) የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ደግሞ የከተማዋን ፍርስራሽ ሲቆፍሩ ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሦስት የከነዓናውያን ቤተ መቅደሶችን አግኝተዋል። በተጨማሪም ከተማይቱ በ1400ዎቹ ዓ.ዓ. እንደተቃጠለች የሚያረጋግጥ ማስረጃ አግኝተዋል። እነዚህ መረጃዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ።

● ከኢየሩሳሌም 9.6 ኪሎ ሜትር ርቃ ስለምትገኘው ገባዖን ስለተባለችው የከነዓናውያን ከተማ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ያገኙት መረጃም ትኩረት የሚስብ ነው። የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የከተማይቱ ስም የተቀረጸባቸው 30 የሚያህሉ የማሰሮ እጀታዎች በማግኘታቸው የከተማይቱን ማንነት መለየት ችለዋል። ከአጾር ነዋሪዎች በተለየ የጥንቶቹ ገባዖናውያን ከኢያሱ ጋር ሰላም መሥርተዋል። እሱም ከዚያ በኋላ “ውሃ ቀጂ” አድርጓቸዋል። (ኢያሱ 9:3-7, 23) እንዲህ ያለ ሥራ የሰጣቸው ለምን ነበር? በ2 ሳሙኤል 2:13 እና በኤርምያስ 41:12 ላይ የሚገኙ ዘገባዎች ገባዖን የተትረፈረፈ የውኃ ሀብት እንደነበራት ይጠቁማሉ። ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር በሚስማማ መልኩ ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን አርኪኦሎጂካል ስተዲ ባይብል እንዲህ ይላል፦ “ገባዖንን ለየት የሚያደርጋት ዋነኛው ነገር የነበራት የተትረፈረፈ የውኃ ሀብት ሲሆን አንድ ትልቅና ሰባት ትናንሽ ምንጮች ነበሯት።”

● በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው የሚገኝ በርካታ ግለሰቦች በሌሎች የታሪክ መዛግብት ላይም ተጠቅሰዋል። ከእነዚህ መካከል ቀደም ሲል ያየናቸው በእስራኤል ወይም በይሁዳ ይገዙ የነበሩና ከአብርሃም ዘር የመጡ 17 ነገሥታት ይገኙበታል። አክዓብ፣ አካዝ፣ ዳዊት፣ ሕዝቅያስ፣ ምናሴና ዖዝያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ በሆኑ በእነዚህ መዛግብት ውስጥ ስማቸው ይገኛል። ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው፣ ይህ ንጉሣዊ ሥርወ መንግሥት መኖሩ እስራኤል የሚባል ብሔር ወደ ከነዓን ምድር እንደገባና ይህን ምድር እንደወረሰ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው።

● በ1896 ተመራማሪዎች በቴብስ፣ ግብፅ የሜርኔፕታን ሐውልት አገኙ። ሐውልቱ ፈርዖን ሜርኔፕታ በ1210 ዓ.ዓ. በከነዓን ምድር ላይ ስላካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ይናገራል። ይህ ሐውልት፣ እስራኤል የሚባል ሕዝብ እንደነበረ በቀጥታ የሚጠቅስ የመጀመሪያው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሚገኝ ማስረጃ ነው።

ዝርዝር መረጃዎች ያላቸው ጠቀሜታ

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰዎች፣ ስለ ቦታዎችና ስለተፈጸሙ ክንውኖች የሚገልጹ በርካታ ዝርዝር መረጃዎችን ይዟል። እነዚህ ዝርዝር መረጃዎች የአምላክ ቃልን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ከሆኑ የታሪክ መረጃዎች ጋር ለማመሳከርና ትንቢቶቹ በትክክል መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ ያስችሉናል። አምላክ፣ ከአብርሃምና ከዘሩ ጋር በተያያዘ የተናገራቸው ነገሮች ማለትም የአብርሃም ዘሮች ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆኑ፣ በግብፅ በባርነት እንደሚኖሩና በኋላም የከነዓንን ምድር እንደሚወርሱ የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ ነገሮች በሙሉ፣ ጴጥሮስ የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ” በማለት በትሕትና የጻፈውን ሐሳብ ያስታውሱናል።​—2 ጴጥሮስ 1:21

የእስራኤል ሕዝብ በከነዓን ምድር ከሰፈረ በኋላ በነበሩት ዘመናት ብሔሩ አሳዛኝ መዘዝ የሚያስከትል ጎዳና መከተል ጀመረ። ይህ ሁኔታ በብሔሩ ላይ የሚያስከትለውን ከባድ መዘዝ በተመለከተም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አስቀድመው ትንቢት ተናግረው ነበር፤ እነዚህን ትንቢቶች በሚቀጥለው እትም ላይ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 የአብርሃም የቀድሞ ስሙ አብራም ነበር።

^ አን.11 አንደኛ ዜና መዋዕል 1:27-34ን፤ 2:1-15ን እና 3:1-24ን ተመልከት። የንጉሥ ሰለሞን ልጅ በነበረው በሮብዓም ዘመነ መንግሥት የእስራኤል ብሔር ለሁለት በመከፈሉ ሰሜናዊውና ደቡባዊው የሚባሉ ሁለት ግዛቶች ተፈጠሩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በእስራኤል ሁለት ነገሥታት በአንድ ጊዜ መግዛት ጀመሩ።​—1 ነገሥት 12:1-24

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ለምድር ሕዝቦች ሁሉ’ የሚሆን በረከት

  አምላክ፣ በአብርሃም ዘር አማካኝነት “የምድር ሕዝቦች ሁሉ” እንደሚባረኩ ቃል ገብቶ ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) አምላክ የአብርሃምን ዝርያዎች አንድ ሕዝብ እንዲሆኑ አድርጎ ያዋቀረበት ዋነኛው ምክንያት ሕይወቱን ለመላው የሰው ዘር አሳልፎ የሚሰጠውን መሲሕ ለማስገኘት ነበር። * በመሆኑም አምላክ ለአብርሃም የገባው ቃል ኪዳን አንተንም ይመለከታል! ዮሐንስ 3:16 እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.33 ከመሲሑ ማንነት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ትንቢቶች በዚህ ተከታታይ ርዕስ ክፍል 3 እና ክፍል 4 ላይ ይብራራሉ።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዝንፍ የማይል የጊዜ አጠባበቅ

  ንጉሥ ሰለሞን በኢየሩሳሌም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደጀመረ የሚገልጸው በ1 ነገሥት 6:1 ላይ የሚገኘው ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ነገሮች፣ ከተባለው ጊዜ ዝንፍ ሳይሉ በትክክል እንደሚፈጸሙ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በአራት መቶ ሰማንያ ዓመት፣ [479 ሙሉ ዓመታት] ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ዚፍ በተባለው በሁለተኛው ወር ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ።”

በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር መሠረት የሰለሞን አራተኛ ዘመነ መንግሥት የዋለው በ1034 ዓ.ዓ. ነው። ከዚህ ዓመት ጀምረን 479 ሙሉ ዓመታት ወደኋላ ስንቆጥር እስራኤላውያን ከግብፅ ወደ ወጡበት ዓመት ማለትም ወደ 1513 ዓ.ዓ. ያደርሰናል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አብርሃም​በታሪክ የሚታወቅ ሰው

● በሁለተኛው ሺህ ዓ.ዓ. መጀመሪያ አካባቢ እንደነበሩ በሚገመቱ የሸክላ ጽላቶች ላይ ከአብርሃም ዘመዶች ስም ጋር አንድ ዓይነት የሆነ መጠሪያ ያላቸው ከተሞች ስም ዝርዝር ተገኝቷል። ከእነዚህ ከተሞች መካከል ፋሌቅ፣ ሴሮሕ፣ ናኮር፣ ታራና ሐራን ይገኙበታል።​—ዘፍጥረት 11:17-32

ዘፍጥረት 11:31 አብርሃምና ቤተሰቡ “በከለዳውያን ምድር ከምትገኘው ከዑር” እንደወጡ ይናገራል። የዚህች ከተማ ፍርስራሽ፣ በደቡብ ምሥራቅ ኢራቅ ተገኝቷል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የአብርሃም አባት ታራ በካራን (በዛሬይቱ ቱርክ ይገኝ እንደነበረ ይገመታል) እንደሞተ እንዲሁም የአብርሃም ሚስት ሣራ በኬብሮን (እስከ ዛሬ ድረስ ሰዎች ከሚኖሩባቸው እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት የመካከለኛው ምሥራቅ ከተሞች አንዷ ናት) እንደሞተች ይገልጻል።​—ዘፍጥረት 11:32፤ 23:2

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ከአብርሃም ዘርና ከእስራኤላውያን ነፃ መውጣት ጋር የተያያዙ ዓመታት

 የአብርሃም ዘር አራት ትውልዶች

ሌዊ

ቀዓት

እንበረም

ሙሴ

(ዓ.ዓ.)

1843 አብርሃም ሞተ

1728 ያዕቆብ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ግብጽ ሄደ

1711 ያዕቆብ ሞተ

1657 ዮሴፍ ሞተ

1593 ሙሴ ተወለደ

1513 ሙሴ እስራኤልን ከግብጽ ነፃ አወጣ

1473 ሙሴ ሞተ። ኢያሱ፣ እስራኤላውያንን ወደ ከነዓን ምድር ይዞ ገባ

የመሳፍንት ዘመን

1117 ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ሳሙኤል ቀባው

1107 ዳዊት ተወለደ

1070 ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ሆነ

1034 ሰለሞን ቤተ መቅደሱን መገንባት ጀመረ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የዳዊት ቤት” የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ይህ ድንጋይ በእስራኤል ወይም በይሁዳ ይገዙ የነበሩት የአብርሃም ዝርያ የሆኑ ነገሥታትን ስም ከሚጠቅሱት የታሪክ መረጃዎች አንዱ ነው

[የሥዕሉ ምንጭ]

© Israel Museum, Jerusalem/The Bridgeman Art Library International