በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታሪክ መስኮት | ፕላቶ

ፕላቶ

ፕላቶ

ፕላቶ (ከ427-347 ዓ.ዓ. ገደማ) አረማዊ የግሪክ ፈላስፋ ነበር። የተወለደው አቴና ውስጥ ከአንድ የባላባት ቤተሰብ ሲሆን የከበርቴ ልጆች የሚማሩትን ትምህርት ተከታትሏል። በዘመኑ ታዋቂ የነበረው ሶቅራጥስ የተባለው ፈላስፋ እንዲሁም የፍልስፍናና የሒሳብ ሊቅ የሆነው የፓይታጎረስ ተከታዮች በፕላቶ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ፕላቶ በሜድትራንያን አካባቢ ከተዘዋወረና ሲሲሊ በተባለች የግሪክ ከተማ ውስጥ በምትገኘው በስራኩስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ሲሳተፍ ከቆየ በኋላ ወደ አቴና ተመልሶ አካዳሚ በመባል የሚታወቀውን የፍልስፍናና የሳይንስ ትምህርት ቤት አቋቋመ። የመጀመሪያው የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ትምህርት ቤት የሒሳብና የፍልስፍና ምርምር ማዕከል በመሆን አገልግሏል።

ስለ ፕላቶ ማወቅ ለምን አስፈለገ?

የፕላቶ ትምህርት ክርስቲያን ነን የሚሉትን ጨምሮ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሃይማኖታዊ እምነት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ እንዲያውም ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የፕላቶ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ከፕላቶ ትምህርቶች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ‘ሰው ሲሞት ከእሱ ተነጥላ የምትሄድ የማትሞት ነፍስ አለች’ የሚለው ነው።

“ፕላቶ እጅግ ይወዳቸው ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የነፍስ ያለመሞት ባሕርይ ነው።”​—ቦዲ ኤንድ ሶል ኢን ኤንሸንት ፊሎሰፊ

ፕላቶ ከሞት በኋላ አለ ስለሚባለው ሕይወት የማወቅ ጥልቅ ፍላጎት ነበረው። ቦዲ ኤንድ ሶል ኢን ኤንሸንት ፊሎሰፊ (ሥጋና ነፍስ በጥንታዊው ፍልስፍና) የተባለው መጽሐፍ “ፕላቶ እጅግ ይወዳቸው ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የነፍስ ያለመሞት ባሕርይ ነው” ይላል። ፕላቶ አንድ ሰው ሲሞት፣ ምድር ላይ ሳለ በነበረው አኗኗር መሠረት “ከሥጋው ተለይታ የምትሄደው ነፍስ ቅጣት ወይም ሽልማት” እንደምትቀበል በጥብቅ ያምን ነበር። *

የፕላቶ ትምህርት የተስፋፋው እንዴት ነው?

አካዳሚ የሚባለው የፕላቶ ትምህርት ቤት ሥራ ላይ በቆየባቸው ዘጠኝ መቶ ዓመታት ማለትም ከ387 ዓ.ዓ. እስከ 529 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት የፕላቶ ትምህርት በሰው ልጆች አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚህ ወቅት የፕላቶ ፍልስፍና በግሪክና በሮም ግዛቶች ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። አይሁዳዊ ፈላስፋ የነበረው የእስክንድርያው ፋይሎም ሆነ በርካታ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች የፕላቶን ፍልስፍና ተቀብለዋል። በዚህ ምክንያት ነፍስ አትሞትም የሚለውን ጨምሮ የአረማውያን የፍልስፍና ትምህርቶች ወደ አይሁድና ወደ ክርስትና እምነት ውስጥ ሰርገው ገቡ።

ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም የክርስትና ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በተወሰነ መጠንም ቢሆን በግሪክ ፍልስፍና፣ በዋነኛነት ደግሞ በፕላቶ ትምህርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። አንዳንድ የክርስትና ፈላስፎች ግን . . . ራሳቸውን ክርስቲያን አድርገው የሚቆጥሩ የፕላቶ ተከታዮች ናቸው።” እስቲ የሚከተሉትን የመረጃ ምንጮች አወዳድር።

ፕላቶ ምን ብሏል? “[አንድ ሰው ሲሞት] የማትሞት ነፍስ ብለን የምንጠራት የእያንዳንዳችን እውነተኛ ማንነት፣ አማልክት ወደሚገኙበት በመሄድ . . . በዚያ ለፍርድ ትቆማለች፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ሰዎች በመተማመን፣ ክፉ ሰዎች ደግሞ በከፍተኛ ፍርሃት የሚጠብቁት ነገር ነው።”—ፕላቶ፣ ሎውስ (12ኛ ጥራዝ)

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ነፍስ፣ አንድን ግለሰብ ወይም ሕይወቱን ታመለክታለች። እንስሳት ሳይቀሩ ነፍሳት ናቸው። በሞት ጊዜ ነፍስ ከሕልውና ውጭ ትሆናለች። * የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ልብ በል፦

  • “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ።”1 ቆሮንቶስ 15:45

  • “ሁለተኛውም በሳህኑ ውስጥ ያለውን ወደ ባሕር አፈሰሰው። ባሕሩም እንደሞተ ሰው ደም ሆነ፤ ሕያው ነፍስ ሁሉ፣ አዎ፣ በባሕር ውስጥ ያለ ነገር ሁሉ ሞተ።”—ራእይ 16:3

  • “ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል።”—ኢሳይያስ 53:12 የ1954 ትርጉም

  • “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።”—ሕዝቅኤል 18:4

ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ ከሥጋ ተለይታ በሕይወት እንደምትኖር አያስተምርም። ስለዚህ ‘እምነቴ የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው ወይስ በፕላቶ ፍልስፍና?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

^ አን.7 ነፍስ አትሞትም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ያስፋፋው ፕላቶ ቢሆንም ጽንሰ ሐሳቡን ለመቀበል የመጀመሪያው ሰው አልነበረም። ይህ ጽንሰ ሐሳብ በተለያየ መልክ ይገለጽ እንጂ የግብፃውያንንና የባቢሎናውያንን ሃይማኖቶች ጨምሮ በተለያዩ አረማዊ ሃይማኖቶች ውስጥ ሲታመንበት በርካታ ዘመናት አልፈዋል።

^ አን.12 መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ያሉበት ሁኔታ ከእንቅልፍ ጋር እንደሚመሳሰልና በትንሣኤ የሚነቁበትን ጊዜ እንደሚጠባበቁ ይናገራል። (መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 11:11-14፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) ከዚህ በተቃራኒ ግን ነፍስ ዘላለማዊ ብትሆን ኖሮ ስለማትሞት ትንሣኤ አያስፈልጋትም ነበር ማለት ነው።