በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ዩናይትድ ስቴትስ

“አንድ ሲጋራ አጫሽ ሠራተኛ፣ ከማያጨስ ሠራተኛ ጋር ሲወዳደር አሠሪውን በዓመት 5,816 የአሜሪካ ዶላር ተጨማሪ ወጪ ያስወጣዋል” በማለት ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። በኦሃዮ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጥናቱን ያካሄዱት ተመራማሪዎች እንደገለጹት ይህን ተጨማሪ ወጪ ከሚያስወጡት ነገሮች መካከል ለማጨስ ብሎ ሥራን ማቋረጥ፣ ለሕክምና የሚወጣ ከፍተኛ ወጪ እና ከሥራ ገበታ መቅረት ይገኙበታል። ሌላው ምክንያት ደግሞ የሚያጨሰው ሰው የኒኮቲን ሱሰኛ በመሆኑ ሲጋራ ካላጨሰ ሥራውን በሚገባ መሥራት አለመቻሉ ነው።

ጣሊያን

“ቀሳውስትና ምዕመናን በሚናገሩት እና በሚያደርጉት፣ ማለትም በአንደበታቸውና በአኗኗራቸው መካከል ከፍተኛ መጣረስ መኖሩ የቤተ ክርስቲያንን ተአማኒነት በጣም እየሸረሸረው ነው።”—ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ

ማሌዥያ

የማሌዥያ ባለሥልጣኖች በሁለት የጣውላ ጭነቶች ውስጥ 240 ኩንታል የሚመዝኑ ከ1,000 የሚበልጡ የዝሆን ጥርሶች ተደብቀው አግኝተዋል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ይህን ያህል መጠን ያለው የዝሆን ጥርስ ከአሁን በፊት ተይዞ እንደማያውቅ ተናግረዋል። የጭነቱ መነሻ ቦታ ቶጎ ሲሆን መድረሻው ደግሞ ቻይና ነበር።

አፍሪካ

በዓለም የጤና ድርጅት የ2012 ሪፖርት መሠረት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከሞቱት ሰዎች መካከል 63 በመቶ የሚሆኑት የሞቱት በተላላፊ በሽታዎች ምክንያት ነው፤ ከእነዚህ መካከል ኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ ተቅማጥ፣ ወባ፣ ሳንባ ነቀርሳ እና የሕፃናት በሽታዎች ይገኙበታል።

አውስትራሊያ

በስማርት ፎኖች እና በሌሎች መሣሪያዎች ላይ የሚጫኑ የቁማር መጫወቻ ፕሮግራሞች በልጆች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፈዋል። አንዳንዶቹ ጨዋታዎች እውነተኛውን የቁማር ጨዋታ የሚመስሉ ሲሆኑ ለማሸነፍም ቀላል ናቸው። መንግሥት ያወጣው አንድ ዘገባ ላይ የሚገኝ ማሳሰቢያ እንደሚገልጸው እንዲህ ያሉት ጨዋታዎች ልጆች ቁማርን ተቀባይነት እንዳለው ነገር እንዲመለከቱትና “ወደፊት የቁማር ሱሰኞች እንዲሆኑ” ሊያደርግ ይችላል።