በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | ትዳር

በትዳር ደስታ ማጣት

በትዳር ደስታ ማጣት

ተፈታታኙ ነገር

ከመጋባታችሁ በፊት ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በጣም እንደምትጣጣሙና ብዙ የሚያመሳስሏችሁ ነገሮች እንዳሉ ሆኖ ይሰማችሁ ነበር። አሁን ግን ሁኔታው እንደጠበቃችሁት ሆኖ ስላላገኛችሁት ሆድና ጀርባ ሆናችኋል፤ በሞቀ ትዳር ውስጥ ሳይሆን እስር ቤት ውስጥ እንዳላችሁ ይሰማችኋል።

ግን አይዟችሁ፤ ግንኙነታችሁን ማሻሻል ትችላላችሁ። በመጀመሪያ ግን ሁኔታው እንደጠበቃችሁት ሳይሆን የቀረው ለምን ሊሆን እንደሚችል እንመልከት።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

እውነታውን መጋፈጣችሁ። ሥራ፣ ልጆችን ማሳደግ፣ ከአማቶች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሁም ሌሎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ትዳር እንደመሠረታችሁ የነበራችሁ ደስታ ቀስ በቀስ እየቀዘቀዘ እንዲሄድ ሊያደርጉ ይችላሉ። በተጨማሪም ያልተጠበቁ ችግሮች ለምሳሌ ያህል የገንዘብ ችግር ወይም በማይድን በሽታ የተያዘን የቤተሰብ አባል ማስታመም በትዳር ውስጥ ውጥረት ሊፈጥር ይችላል።

ልዩነቶችን ማስታረቅ ፈጽሞ የማይቻል እንደሆነ አድርጋችሁ ማሰባችሁ። ባለትዳሮች ይጠናኑ በነበረበት ወቅት ልዩነቶቻቸውን ችላ ብለው ማለፍ አይከብዳቸውም ነበር። ከተጋቡ በኋላ ግን ከሚነጋገሩበት መንገድ፣ ከገንዘብ አያያዝ፣ ከችግር አፈታትና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር በተያያዘ ምን ያህል የተለያዩ እንደሆኑ ይገነዘባሉ። ከዚያ በፊት ያን ያህል የማያስከፉ የነበሩት ልዩነቶች አሁን ችሎ ለማለፍ የሚከብዱ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ።

በስሜት እየተራራቃችሁ መምጣታችሁ። ደግነት የጎደላቸው አነጋገሮችና ድርጊቶች እንዲሁም ሳይፈቱ የቀሩ አለመግባባቶች ውለው ሲያድሩ ይከማቹና ባልና ሚስቱ በስሜት እንዲራራቁ ያደርጋሉ፤ ይባስ ብሎም ከሌላ ሰው ጋር ስሜታዊ ቅርርብ ሊጀምሩ ይችላሉ።

የጠበቃችሁት ነገር ከእውነታው የራቀ መሆኑ። አንዳንድ ሰዎች ትዳር ውስጥ የሚገቡት ለእነሱ እንደተፈጠረ የሚሰማቸውን ሰው እንዳገኙ እርግጠኛ ሆነው ነው። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ለግለሰቡ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ቢመስልም አደገኛ ሊሆን ይችላል። በትዳራቸው ውስጥ ችግር ሲከሰት “ፍጹም የትዳር ጓደኛ” ያሉት ሰው ጨርሶ ከጠበቁት ሌላ እንደሆነባቸው ይሰማቸዋል፤ በዚህ ጊዜ ሁለቱም ምርጫቸው የተሳሳተ እንደነበረ ማሰብ ይጀምራሉ።

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

በትዳር ጓደኛችሁ ጥሩ ባሕርያት ላይ አተኩሩ። እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኛችሁን ሦስት ጥሩ ባሕርያት ጻፉ። ይህን የጻፋችሁትን ዝርዝር ምንጊዜም ያዙት፤ ምናልባትም በጋብቻ ፎቶግራፋችሁ ጀርባ ወይም በሞባይል ስልካችሁ ላይ መጻፍ ትችሉ ይሆናል። የትዳር ጓደኛችሁን ያገባችሁበትን ምክንያት ለማስታወስ አዘውትራችሁ ይህን ዝርዝር እዩት። በትዳር ጓደኛችሁ ጥሩ ባሕርያት ላይ ማተኮራችሁ ሰላም እንዲሰፍን ከመርዳቱም በላይ ልዩነቶቻችሁን አቻችላችሁ እንድትኖሩ ይረዳችኋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሮም 14:19

አብራችሁ የምታሳልፉት ልዩ ጊዜ መድቡ። ከመጋባታችሁ በፊት አንዳንድ ነገሮችን አብራችሁ ለማከናወን ጊዜ ትመድቡ እንደነበረ የታወቀ ነው። ተገናኝቶ መጨዋወት ብርቅና አስደሳች በነበረበት በዚያን ጊዜም እንኳ አስባችሁበት ፕሮግራም መያዝ አስፈልጓችኋል። ታዲያ አሁንስ ለምን ተመሳሳይ ነገር አታደርጉም? እየተጠናናችሁ እንዳለ አድርጋችሁ በመቁጠር ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር አብራችሁ የምታሳልፉት ልዩ ጊዜ እንዲኖራችሁ አድርጉ። እንዲህ ማድረጋችሁ እርስ በርስ እንድትቀራረቡና በሕይወታችሁ ውስጥ የሚያጋጥሟችሁን ድንገተኛ ችግሮች በተሻለ መንገድ ለመወጣት ይረዳችኋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 5:18

የተሰማችሁን ነገር ተወያዩበት። የትዳር ጓደኛችሁ በአነጋገር ወይም በድርጊት ጎድቷችሁ ከነበረ ጉዳዩን ችላ ብላችሁ ልታልፉት ትችላላችሁ? ከሆነ ጥሩ ነው። ካልቻላችሁ ግን በማኩረፍ መፍትሔ ለማግኘት አትሞክሩ፤ ይህ ብስለት እንደጎደላችሁ የሚያሳይ ነው። በተቻለ ፍጥነት፣ ቢቻል በዚያው ቀን በረጋ መንፈስ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተወያዩበት።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ኤፌሶን 4:26

የትዳር ጓደኛችሁ በአነጋገር ወይም በድርጊት ጎድቷችሁ ከነበረ ጉዳዩን ችላ ብላችሁ ልታልፉት ትችላላችሁ?

የትዳር ጓደኛችሁ አንድን ነገር እንዲናገር ወይም እንዲያደርግ ያነሳሳውን ምክንያት ለማስተዋል ሞክሩ። አንዳችሁ ሌላውን ሆን ብላችሁ የመጉዳት ሐሳብ እንደማይኖራችሁ የታወቀ ነው። ይህን ለትዳር ጓደኛችሁ ማረጋገጥ የምትችሉበት አንዱ መንገድ የትዳር ጓደኛችሁን ስሜት የሚጎዳ ነገር በምታደርጉበት ጊዜ ከልባችሁ ይቅርታ መጠየቅ ነው። ከዚያም ሁለታችሁም፣ ሳይታወቃችሁ ሌላውን ከመጉዳት ለመራቅ ምን እርምጃዎችን መውሰድ እንደምትችሉ በግልጽ ተወያዩ። የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተሉ፦ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ . . . እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።”—ኤፌሶን 4:32

ከትዳር በምትጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ “መከራ ይደርስባቸዋል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) እንዲህ ያለ መከራ ሲደርስባችሁ ቸኩላችሁ ያደረጋችሁት ምርጫ ስህተት እንደነበር አትደምድሙ። ከዚህ ይልቅ ልዩነቶቻችሁን ለመፍታት ሁለታችሁም ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 3:13