በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

መጽሐፍ ቅዱስ ደም ምን መደረግ እንዳለበት ከሚሰጠው መመሪያ አንጻር የይሖዋ ምሥክሮች የራስን ደም በመጠቀም ለሚከናወኑ የሕክምና አሠራሮች ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

በግል ምርጫ ወይም በአንዳንድ የሕክምና መመሪያዎች ላይ ብቻ ተመሥርቶ ከመወሰን ይልቅ እያንዳንዱ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር በጥሞና መመርመር አለበት። ይህ በግለሰቡና በይሖዋ መካከል ያለ ጉዳይ ነው።

የሕይወታችን ባለቤት የሆነው ይሖዋ ደም መበላት እንደሌለበት ደንግጓል። (ዘፍጥረት 9:​3, 4) ደም ሕይወትን ስለሚወክል አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ በሰጠው ሕግ በደም አጠቃቀም ላይ ገደብ አውጥቷል። “የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ . . . በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት” ሲል ደንግጓል። አንድ ሰው ለምግብነት ብሎ እንስሳ ቢያርድስ? አምላክ “ደሙን ያፈስሳል በአፈርም ይከድነዋል” ብሏል። a (ዘሌዋውያን 17:​11, 13) ይሖዋ ይህን ትእዛዝ በተደጋጋሚ ተናግሯል። (ዘዳግም 12:​16, 24፤ 15:​23) ሶንሲኖ ሹማሽ የተባለው የአይሁዳውያን መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ደሙ መቀመጥ የለበትም። ከዚህ ይልቅ ለመብልነት እንዳይውል ምድር ላይ መፍሰስ አለበት።” ማንኛውም እስራኤላዊ ሕይወቱ የአምላክ ንብረት የሆነውን የሌላ ፍጡር ደም መውሰድ፣ ማስቀመጥ ወይም መጠቀም አይችልም ነበር።

መሲሑ ሲሞት የሙሴን ሕግ የመጠበቁ ግዴታ አከተመ። ሆኖም አምላክ ለደም ቅድስና ያለው አመለካከት አልተለወጠም። ሐዋርያት በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ተመርተው ክርስቲያኖች ‘ከደም እንዲርቁ’ አዝዘዋል። ይህ ትእዛዝ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ አልነበረም። ትእዛዙ ከሥነ ምግባር አንጻር ሲታይ ከጾታ ብልግና ወይም ከጣዖት አምልኮ የመራቅን ያህል አስፈላጊ ነበር። (ሥራ 15:​28, 29፤ 21:​25) ደም መስጠትም ሆነ መውሰድ በ20ኛው መቶ ዘመን የተለመደ እየሆነ ሲመጣ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ተግባር ከአምላክ ቃል ጋር እንደሚቃረን ተገነዘቡ። b

አልፎ አልፎ አንድ ዶክተር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የራሱን የታካሚውን ደም መልሶ መስጠት ይችል ዘንድ ቀዶ ሕክምና ከመከናወኑ ከሳምንታት በፊት ታካሚው የራሱን ደም እንዲሰጥ (ከቀዶ ሕክምና በፊት የራስን ደም መለገስ ወይም ፒ ኤ ዲ) ያሳስበዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ደምን የመውሰድ፣ የማስቀመጥና የመስጠት ልማድ ዘሌዋውያንና ዘዳግም ላይ የሠፈረውን ሕግ በቀጥታ ይቃረናል። ደም መቀመጥ የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ምድር ላይ መፍሰስ አለበት። ይህም በምሳሌያዊ አነጋገር ወደ አምላክ የተመለሰ ያህል ነው። በአሁኑ ጊዜ የሙሴ ሕግ የተሻረ መሆኑ እውነት ነው። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ በሙሴ ሕግ ውስጥ ያካተተውን መሠረታዊ ሥርዓት የሚያከብሩ ሲሆን ‘ከደም ለመራቅም’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ከዚህ የተነሳ ደም አንሰጥም እንዲሁም ‘መፍሰስ’ ያለበትን የራሳችንን ደም መልሰን ለመውሰድ ብለን አናስቀምጥም። ይህ ድርጊት ከአምላክ ሕግ ጋር ይጋጫል።

የአንድን ግለሰብ የራሱን ደም በመጠቀም የሚካሄዱ ሌሎች የሕክምና ሂደቶች ወይም ምርመራዎች በጽሑፍ ሰፍረው ከሚገኙት የአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በቀጥታ አይጋጩም። ለምሳሌ ያህል ብዙ ክርስቲያኖች ምርመራ ከተካሄደበት በኋላ የሚጣል እንደ ናሙና ሆኖ የሚያገለግል ደም ለመስጠት ፈቃደኛ ሆነዋል። በተጨማሪም በአንድ ሰው ደም ላይ ይበልጥ ውስብስብ የሆኑ ሌሎች አሠራሮች እንዲካሄዱ ሐኪሞች ሊያዝዙ ይችላሉ።

ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ የቀዶ ሕክምና አሠራሮች ወቅት ሄሞዳይሉሽን በሚባል ሂደት የተወሰነ ደም በሌላ መስመር እንዲያልፍ ሊደረግ ይችላል። በታካሚው ሰውነት ውስጥ የቀረው ደም ፈሳሽ ተጨምሮበት ይቀጥናል። በኋላም ከሰውነቱ ውጪ በተቀጠለው መስመር ውስጥ ያለውን ደም ወደ ሰውነቱ በማስገባት የደሙ መጠን ወደ መደበኛው እንዲጠጋ ይደረጋል። በተመሳሳይም በቆሰለ የሰውነት ክፍል ላይ የሚፈስሰውን ደም በማጣራት ቀይ የደም ህዋሳቱ ተመልሰው ወደ ታካሚው ሰውነት እንዲገቡ የሚደረግበት መንገድ አለ። ይህ አሠራር ህዋስን መልሶ መጠቀም ተብሎ ይታወቃል። በሌላ ሂደት ደግሞ የሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ ያህል ልብ፣ ሳንባ ወይም ኩላሊት) የሚሠሩትን ሥራ ለጊዜው አንድ መሣሪያ እንዲያከናውነው ደም ወደ መሣሪያው ሊገባ ይችላል። ከዚያም መሣሪያው ውስጥ የገባው ደም ተመልሶ ወደ ታካሚው ሰውነት ይገባል። በሌሎች አሠራሮች ደግሞ ጎጂ የሆኑትን ወይም እክል ያለባቸውን የደም ክፍሎች ማስወገድ እንዲቻል ደም በማጣሪያ መሣሪያ ውስጥ እንዲያልፍ ይደረጋል። ወይም አንዳንድ የደም ክፍሎችን መለየትና ለሌላ የሰውነት ክፍል መስጠት ያስፈልግ ይሆናል። ከታካሚው ደም ከተወሰደ በኋላ ላዩ ላይ መለያ ምልክት አድርጎ በማስቀመጥ ወይም ደሙን ከመድኃኒት ጋር በመቀላቀል ከጊዜ በኋላ ተመልሶ ለታካሚው የሚሰጥበት ጊዜም አለ።

ዝርዝር ጉዳዮቹ ሊለያዩ የሚችሉ ከመሆኑም በላይ አዳዲስ አሠራሮች፣ የሕክምና ዘዴዎችና ምርመራዎች መዳበራቸው አይቀርም። እያንዳንዱን የአሠራር ዓይነት መመርመርና ውሳኔ መስጠት የእኛ ፈንታ አይደለም። አንድ ክርስቲያን ቀዶ ሕክምና፣ የጤና ምርመራ ወይም ሌላ ዓይነት ሕክምና በሚደረግለት ወቅት በራሱ ደም ላይ ስለሚከናወነው ነገር በግሉ መወሰን አለበት። ግለሰቡ ሕክምናው በሚሰጥበት ወቅት በደሙ ላይ ስለሚከናወነው ነገር ከሕክምና ባለሙያዎቹ አስቀድሞ ማስረጃዎቹን ማግኘት አለበት። ከዚያም ሕሊናው ከሚፈቅድለት ነገር ጋር የሚስማማ ውሳኔ ማድረግ አለበት። (ሣጥኑን ተመልከት።)

ክርስቲያኖች ለአምላክ የገቡትን ውሳኔና ‘እሱን በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው፣ በፍጹም ኃይላቸውና በፍጹም አሳባቸው በመውደድ’ ረገድ ያለባቸውን ግዴታ ማስታወስ አለባቸው። (ሉቃስ 10:​27) በዓለም ከሚገኙ ከብዙዎቹ ሰዎች በተለየ የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ ጋር ያላቸውን መልካም ዝምድና ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። ሕይወት ሰጪ የሆነው አምላክ ሰዎች ሁሉ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ እምነት እንዲኖራቸው አጥብቆ ያሳስባል። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በውድ ልጁም [በኢየሱስ ክርስቶስ]፣ . . . በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።”​—⁠ኤፌሶን 1:​7

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ፕሮፌሰር ፍራንክ ኤች ጎርማን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ደምን መሬት ላይ ማፍሰስ ግለሰቡ ለእንስሳው ሕይወት እንዲሁም ሕይወት ለሰጠውና እንክብካቤ ለሚያደርግለት አምላክ አክብሮት እንዳለው የሚያሳይ ድርጊት እንደሆነ ይቆጠራል።”

b የሐምሌ 1, 1951 መጠበቂያ ግንብ (የእንግሊዝኛ) የሌላን ሰው ደም መውሰድ ተገቢ ያልሆነበትን ምክንያት በመግለጽ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለሚነሱ ቁልፍ ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ራስህን መጠየቅ ያለብህ ጥያቄዎች

የተወሰነ ደም ከሰውነቴ ውጪ በሌላ መስመር እንዲያልፍ የሚደረግ ከሆነና ይባስ ብሎም ዝውውሩ ለተወሰነ ጊዜ ሊቋረጥ የሚችል ከሆነ ደሙ ልክ ከሰውነቴ እንዳልወጣና ‘መሬት ላይ መፍሰስ’ እንደማይገባው አድርጌ እንድመለከተው ሕሊናዬ ይፈቅድልኛልን?

በምርመራ ወይም በሕክምና ሂደት ወቅት የራሴ ደም ከሰውነቴ ቢወሰድና አንዳንድ ለውጦች ተደርገውበት ወደ ሰውነቴ ቢገባ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናዬ ይረብሸኝ ይሆን?