በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ከልጆቻችሁ ጋር ስለ ፆታ አውሩ

ከልጆቻችሁ ጋር ስለ ፆታ አውሩ

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው አሊስያ * እንዲህ ትላለች፦ “ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነገሮችን ለማወቅ እፈልጋለሁ፤ ይሁን እንጂ ወላጆቼን ስለዚህ ጉዳይ ብጠይቃቸው መጥፎ ነገር እየፈጸምኩ እንደሆነ ያስባሉ ብዬ እፈራለሁ።”

የአሊስያ እናት የሆነችው ኢኔዝ እንዲህ ትላለች፦ “ከልጄ ጋር ቁጭ ብለን ስለ ፆታ ብናወራ ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖም በግል ጉዳዮቿ ስለምትጠመድ ነፃ ሆና የምናወራበት ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።”

በዛሬው ጊዜ ከፆታ ጋር የተያያዙ ነገሮች በማንኛውም ቦታ ይኸውም በቴሌቪዥን፣ በፊልሞችና በማስታወቂያዎች ላይ ይታያሉ። ስለዚህ ጉዳይ ማንሳት እንደ ነውር የሚቆጠረው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሲያወሩት ብቻ ሳይሆን አይቀርም። በካናዳ የሚኖረውና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ማይክል እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆች ከእነሱ ጋር ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራት ምን ያህል እንደሚያስጨንቅና እንደሚያሳፍር ቢረዱ ደስ ይለኝ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ከጓደኞቻችን ጋር ብናወራ ይቀለናል።”

ብዙውን ጊዜ ወላጆችም ቢሆኑ ይህን ጉዳይ አንስተው ከልጆቻቸው ጋር ማውራት ይከብዳቸዋል። የሥነ ጤና ባለሙያ የሆነችው ዴብራ ሃፍነር፣ ቢዮንድ ዘ ቢግ ቶክ በተሰኘው መጽሐፏ ላይ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ወላጆች፣ ስለ ፆታ ወይም ስለ ጉርምስና የሚናገር መጽሐፍ ገዝተው ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ እየተቃረበ ባለው ልጃቸው ክፍል ውስጥ እንዳስቀመጡለትና ከዚያ በኋላ ስለ ጉዳዩ ፈጽሞ አንስተው እንደማያውቁ ነግረውኛል።” ሃፍነር፣ ወላጆች እንዲህ ማድረጋቸው ለልጃቸው “ስለ ሰውነትህና ስለ ፆታ ግንኙነት እንድታውቅ እንፈልጋለን፤ ሆኖም ስለዚህ ጉዳይ ልናዋራህ አንፈልግም” የሚል መልእክት እንደሚያስተላልፍ ገልጻለች።

ወላጅ ከሆንክ ከላይ ከተጠቀሰው የተለየ አቋም ሊኖርህ ይገባል። አንተ ራስህ ከልጆችህ ጋር ስለ ፆታ ማውራት አለብህ። እንዲህ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው የምንልባቸውን ሦስት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት፦

  1. ዓለም ለፆታ ግንኙነት የሚሰጠው ፍቺ ተለውጧል። “ሰዎች፣ የፆታ ግንኙነትን በባልና በሚስት መካከል ብቻ የሚፈጸም ነገር እንደሆነ አድርገው መመልከታቸው እየቀረ ነው” በማለት የ20 ዓመቱ ጄምስ ተናግሯል። “አሁን አሁን በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ የፆታ ግንኙነት እንዲሁም ሳይበርሴክስ [በኢንተርኔት የብልግና ወሬ በማውራት የፆታ ስሜትን ማርካት] አልፎ ተርፎም በሞባይል ስልክ አማካኝነት ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዘ መልእክት ወይም ምስል መላላክ የተለመደ ሆኗል።”

  2. ልጆቻችሁ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ስለ ፆታ የተሳሳተ ነገር መስማታቸው አይቀርም። ሺላ የምትባል አንዲት እናት “ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ስለ ፆታ የሚሰሙ ሲሆን ይህም ስለ ጉዳዩ እንዲኖራቸው የምትፈልጉት ዓይነት አመለካከት እንዳይኖራቸው ያደርጋል” ብላለች።

  3. ልጆቻችሁ ስለ ፆታ ጥያቄ ቢኖራቸውም ጉዳዩን ለማንሳት ላይደፍሩ ይችላሉ። “እንደ እውነቱ ከሆነ ከወላጆቼ ጋር ስለ ፆታ ግንኙነት አንስቼ ማውራት የምችለው እንዴት እንደሆነ ምንም የማውቀው ነገር የለም” በማለት በብራዚል የምትኖረው የ15 ዓመቷ አና ትናገራለች።

አምላክ ለወላጆች የሰጣቸው ኃላፊነት ከልጆቻቸው ጋር ስለ ፆታ ማውራትንም ይጨምራል። (ኤፌሶን 6:4) እውነት ነው፣ ከፆታ ግንኙነት ጋር ስለተያያዙ ነገሮች ማውራት ለእናንተም ሆነ ለልጆቻችሁ የሚያሳፍር ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን እንዲህ ማድረጋችሁ የሚያስገኘው ጥቅም አለ፤ በርካታ ወጣቶች “ስለ ፆታ መማር የምንፈልገው ከአስተማሪ ወይም ከቴሌቪዥን ፕሮግራም ሳይሆን ከወላጆቻችን ነው” በማለት ከተናገረችው የ14 ዓመቷ ዳኒየል ጋር ይስማማሉ። ታዲያ ይህን አስፈላጊ ሆኖም ለማውራት የሚከብድ ርዕሰ ጉዳይ አንስታችሁ ከልጆቻችሁ ጋር መነጋገር የምትችሉት እንዴት ነው? *

ዕድሜያቸውን ያገናዘበ

ልጆች ሙሉ በሙሉ ከሰው ተገልለው ካልኖሩ በቀር ከፆታ ጋር የተያያዙ ነገሮችን መስማት የሚጀምሩት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነው። ከሁሉ ይበልጥ የሚረብሸው ደግሞ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ክፉ ሰዎች “በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” የሚሄዱ መሆኑ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) የሚያሳዝነው ብዙ ልጆች በትልልቅ ሰዎች በፆታ ይነወራሉ።

በመሆኑም ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ ለልጆቻችሁ ስለ ፆታ ማስተማራችሁ አስፈላጊ ነው። ሬናቴ የምትባል በጀርመን የምትኖር አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “ልጆቻችሁ ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ እስኪደርሱ የምትጠብቁ ከሆነ ከጉርምስና ጋር አብሮ በሚመጣው የማፈር ስሜት የተነሳ በግልጽ ማውራት ላይፈልጉ ይችላሉ።” እንግዲያው ለልጆች ዕድሜያቸውን ያገናዘበ ትምህርት መስጠት አስፈላጊ ነው።

ትምህርት ቤት ላልገቡ ሕፃናት፦

የፆታ ብልቶችን ተገቢ ስሞች በማስተማርና እነዚህን የሰውነታቸውን ክፍሎች ማንም ሰው መንካት እንደሌለበት አጥብቃችሁ በመግለጽ ላይ ትኩረት አድርጉ። ሁልያ የምትባል በሜክሲኮ የምትኖር አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “ወንድ ልጄን ማስተማር የጀመርኩት ሦስት ዓመት ሲሆነው ነበር። አስተማሪዎች፣ ሞግዚቶች ወይም በዕድሜ ከእሱ የሚበልጡ ልጆች ሊጎዱት እንደሚችሉ ማወቄ ነገሩ በጣም እንዲያሳስበኝ አደረገኝ። ራሱን መከላከል የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገው ነበር።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ልጃችሁ ማንም ሰው የፆታ ብልቱን ለመነካካት ቢሞክር ጠንከር ያለ መልስ እንዲሰጥ አሠልጥኑት። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ “ተው! እናገርብሃለሁ!” እንዲል ልታሠለጥኑት ትችላላችሁ። ልጃችሁ ያጋጠመውን ሁኔታ መናገሩ ምንጊዜም ተገቢ መሆኑን ግለጹለት፤ ግለሰቡ ቢያስፈራራው ወይም ስጦታ እንደሚሰጠው ቃል ቢገባለትም እንኳ ሁኔታውን ለወላጆቹ መናገሩ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘብ እርዱት። *

አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለገቡ ልጆች፦

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የልጆቻችሁን እውቀት ቀስ በቀስ ለማሳደግ ጥረት አድርጉ። ፒተር የሚባል አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችሁን ማስተማር ከመጀመራችሁ በፊት ስለዚህ ጉዳይ ምን ያህል እንደሚያውቁ እንዲሁም የበለጠ ለማወቅ ይፈልጉ እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። ልጆቹ ስለዚህ ርዕስ ማውራት ካልፈለጉ አታስገድዷቸው። ከልጆቻችሁ ጋር አዘውትራችሁ ጊዜ የምታሳልፉ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ውይይት መነሳቱ አይቀርም።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ልጆቻችሁ ሊያውቁት ይገባል የምትሉትን ነገር ሁሉ በአንድ ቀን ከመዘርገፍ ይልቅ በየጊዜው በትንሽ በትንሹ ንገሯቸው። (ዘዳግም 6:6-9) እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ለልጆቻችሁ የምትነግሯቸው ነገር ከአቅማቸው በላይ አይሆንባቸውም። ከዚህም በላይ እያደጉ ሲሄዱ እንደ ዕድሜያቸው የሚያስፈልጋቸውን እውቀት ያገኛሉ።

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኙ፦

በዚህ ወቅት ልጆቻችሁ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ አካላዊ፣ ስሜታዊና ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በቂ እውቀት እንዳላቸው ማረጋገጥ ይኖርባችኋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው የ15 ዓመቷ አና እንዲህ ብላለች፦ “በትምህርት ቤታችን ያሉ ልጆች ገና ከአሁኑ የፆታ ግንኙነት መፈጸም ጀምረዋል። ክርስቲያን እንደመሆኔ መጠን ስለዚህ ጉዳይ በቂ እውቀት ማግኘት እንዳለብኝ ይሰማኛል። ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራት የሚያሳፍር ሊሆን ቢችልም ላውቀው የሚገባ ነገር ነው።” *

ልብ ልትሉት የሚገባ ነገር፦ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች፣ ተገቢ ያልሆነ ነገር እየፈጸሙ ነው ብለው ወላጆቻቸው እንዳይጠረጥሯቸው ስለሚፈሩ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። ስቲቨን የሚባል አንድ አባት ይህን አስተውሏል። “ወንድ ልጃችን ስለ ፆታ ግንኙነት ለመወያየት ያን ያህል ደስተኛ አልነበረም። ይህም የሆነው እንደጠረጠርነው ስለተሰማው መሆኑን በኋላ ላይ ተረዳን። በመሆኑም ይህን ጉዳይ አስመልክተን ልናዋራው የፈለግነው ስለጠረጠርነው ሳይሆን የሚደርስበትን መጥፎ ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል በቂ እውቀት እንዲኖረው ፈልገን መሆኑን ገለጽንለት።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁን ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ጥያቄ ከመጠየቅ ይልቅ አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሰማቸው ጠይቋቸው። ለምሳሌ እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ፦ “በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በአፍ የሚፈጸም የፆታ ግንኙነት እንደ ፆታ ግንኙነት እንደማይቆጠር ይሰማቸዋል። አብረውህ የሚማሩት ልጆች እንደዚህ ነው የሚያስቡት?” እንዲህ ያሉት ቀጥተኛ ያልሆኑ ጥያቄዎች፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ በዚህ ርዕስ ላይ ነፃ ሆነው እንዲያወሩና አመለካከታቸውን እንዲገልጹ ሊያነሳሷቸው ይችላሉ።

የእፍረት ስሜትን ማሸነፍ

እርግጥ ነው፣ ወላጅ በመሆንህ ካሉብህ ኃላፊነቶች ሁሉ ከባድ የሚሆነው ከልጆችህ ጋር ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጉ የሚክስ ነው። ዳያን የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ስለዚህ ርዕስ ማውራት የሚያሳፍር መሆኑ እየቀነሰ ይመጣል፤ እንዲያውም ከልጃችሁ ጋር ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራት ይበልጥ ሊያቀራርባችሁ ይችላል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ስቲቨንም በዳያን አባባል ይስማማል። “በቤተሰባችሁ ውስጥ ስለሚያጋጥማችሁ ስለ ማንኛውም ርዕስ በግልጽ የመነጋገር ልማድ ካላችሁ እንደ ፆታ ግንኙነት ያሉትን የሚያሳፍሩ ጉዳዮች አንስቶ መወያየት ቀላል ይሆናል” ብሏል። አክሎም “ስለዚህ ጉዳይ ሲነሳ የሚኖረውን የማፈር ስሜት ጨርሶ ማስወገድ ባይቻልም ክርስቲያኖች ጥሩ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው ግልጽ የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው የግድ አስፈላጊ ነው” በማለት ተናግሯል።

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.11 ይህ ርዕስ ከልጆቻችሁ ጋር ስለ ፆታ የማውራትን አስፈላጊነት የሚዳስስ ነው። በሚቀጥለው ጊዜ በዚህ አምድ ሥር የሚወጣው ርዕስ ከልጆቻችሁ ጋር እንዲህ ዓይነት ውይይት ስታደርጉ ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎችን እንዴት ማስተማር እንደምትችሉ ያብራራል።

^ አን.16 በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ከታላቁ አስተማሪ ተማር ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 171 ላይ የተወሰደ።

^ አን.19 በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኝ ልጃችሁ ጋር ስለ ፆታ ግንኙነት ለመወያየት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ከምዕራፍ 1-5 እንዲሁም ምዕራፍ 28, 29 እና 33⁠ን ተመልከቱ።

ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶች የሰነዘሯቸውን ከዚህ በታች የቀረቡትን ሐሳቦች ካነበብህ በኋላ ለጥያቄዎቹ ምን መልስ እንደምትሰጥ አስብ።

“ወላጆቼ ከፆታ ጋር የተያያዙ ርዕሶችን እንዳነብና ጥያቄ ካለኝ እንድጠይቃቸው ይነግሩኛል። እኔ ግን ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ቢያዋሩኝ ደስ ይለኝ ነበር።”—አና፣ ብራዚል

ለልጅህ ስለ ፆታ የሚያወሱ ጽሑፎችን ከመስጠት ያለፈ ነገር ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምን ይመስልሃል?

“ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ሰዎች የሚያደርጓቸው ብዙ መጥፎ ነገሮች እንዳሉ አውቃለሁ፤ አባቴ ስለ እነዚህ ነገሮች ጨርሶ የሚያውቅ አይመስለኝም። ስለዚህ ጉዳይ ብጠይቀው ይዘገንነው ይሆናል።”—ኬን፣ ካናዳ

ልጅህ ስለሚያሳስቡት ጉዳዮች ከአንተ ጋር ከማውራት ወደኋላ እንዲል የሚያደርጉት ምን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ?

“እንደምንም ራሴን አደፋፍሬ ወላጆቼን ስለ ፆታ ግንኙነት ስጠይቃቸው ‘እንዴት ስለዚህ ጉዳይ ጠየቅሽ? ያጋጠመሽ ነገር አለ እንዴ?’ የሚል ወቀሳ አከል ምላሽ ሰጡኝ።”—ማሳሚ፣ ጃፓን

ልጅህ ስለ ፆታ ግንኙነት ሲጠይቅህ የምትሰጠው ምላሽ በሌላ ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ መወያየት ቀላል እንዲሆንለት አሊያም እንዲከብደው ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው?

“ወላጆቼ በእኔ ዕድሜ ሳሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንደነበሯቸውና እኔም እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች መጠየቄ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ቢነግሩኝ ይቀለኝ ነበር።”—ሊዜት፣ ፈረንሳይ

ልጅህ ስለ ፆታ ግንኙነት ሳይሸማቀቅ እንዲያዋራህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

“እናቴ ከፆታ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ትጠይቀኛለች፤ ሆኖም የድምፅዋ ቃና የሚያሸማቅቅ አይደለም። አንድ ልጅ እንደሚወቀስ እንዲሰማው በማያደርግ መንገድ መነጋገሩ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል።”—ዤራልድ፣ ፈረንሳይ

ልጅህን ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነገር ስታዋራው የድምፅህ ቃና ምን ይጠቁማል? በዚህ ረገድ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን?