በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙስና ይወገዳል!

ሙስና ይወገዳል!

“እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ . . . ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ።”—መዝሙር 37:34

ብዙ ሰዎች ሙስና የማይቀር ነገር እንደሆነና መቼም ቢሆን ጨርሶ ሊወገድ እንደማይችል ይሰማቸዋል፤ አንተም የሚሰማህ እንደዚህ ነው? ከሆነ ይህ ምንም አያስገርምም። በታሪክ ዘመናት ሁሉ የሰው ልጆች ያልሞከሩት የአገዛዝ ዓይነት የለም። ያም ቢሆን ሙስናን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አልቻሉም። ታዲያ ሁሉም ሰው በሐቀኝነት የሚመላለስበት ጊዜ ይመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን?

የሚያስደስተው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ እንደሚቻል ይናገራል! አምላክ ምድራችንን ከሙስና ለማጽዳት በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። አምላክ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በሰማይ በሚገኘው መንግሥቱ አማካኝነት ምድርን ሙሉ በሙሉ በመለወጥ ነው። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን ባስተማረው ጸሎት ላይ የጠቀሰው ስለዚህ መንግሥት ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ የጌታ ጸሎት ወይም አቡነ ዘበሰማያት ተብሎ በሚጠራው በዚህ ጸሎት ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ . . . በምድር ትሁን።”—ማቴዎስ 6:10 አ.መ.ት

የዚህ መንግሥት ንጉሥ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ትንቢት እንዲህ ይላል፦ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል።” (መዝሙር 72:12-14) ኢየሱስ በሙስና ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ስሜት የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ጭቆናን ለማስወገድ እርምጃ እንደሚወስድ ልብ በል። ይህን ማወቅ ምንኛ ያጽናናል!

የአምላክ መንግሥት፣ ሩኅሩኅ እና ኃያል በሆነው ንጉሡ አማካኝነት ምድራችንን ከሙስና ነፃ ያደርጋታል። እንዴት? ለሙስና መንስኤ የሚሆኑትን ሦስት ነገሮች በማስወገድ ነው።

ኃጢአት

በአሁኑ ጊዜ ሁላችንም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት እንድንፈጽም ከሚገፋፋን የኃጢአት ዝንባሌ ጋር መታገል አለብን። (ሮም 7:21-23) እንደዚያም ሆኖ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚፈልጉ ጥሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች፣ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ከኃጢአት የመቤዠት ኃይል እንዳለው እንደሚያምኑ በተግባር ስለሚያሳዩ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት ይችላሉ። * (1 ዮሐንስ 1:7, 9) እንደነዚህ ያሉት ሰዎች አምላክ በታላቅ ፍቅሩ ተነሳስቶ ከወሰደው እርምጃ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፤ ዮሐንስ 3:16 ይህ ፍቅር የታየው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”

አምላክ፣ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች በጣም አስደናቂ የሆነ ነገር ያደርግላቸዋል። በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ፣ ኃጢአት ያስከተላቸውን ውጤቶች በሙሉ ቀስ በቀስ ያስወግዳል፤ እንዲሁም ታማኝ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርሱና በእሱ ፊት ጻድቃን መሆን እንዲችሉ ያደርጋል። (ኢሳይያስ 26:9፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ከዚያ በኋላ ማንኛውም ሰው፣ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽም የሚገፋፋ የኃጢአት ዝንባሌ አይኖረውም። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ታማኝ የሰው ልጆች “የመጥፎ ሥነ ምግባር ባሪያዎች” አይሆኑም።—2 ጴጥሮስ 2:19

የምንኖርበት ዓለም

ነገሩ የሚያሳዝን ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ሆን ብለው ሌሎችን የሚጎዳ ድርጊት ይፈጽማሉ። ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውንና ድሆችን መጠቀሚያ ያደርጋሉ፤ ሌሎችም እንደ እነሱ የሙስና ድርጊት እንዲፈጽሙ ተጽዕኖ ያደርጉባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ላሉት ሰዎች “ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው” የሚል ምክር ይሰጣል። እነዚህ ሰዎች ንስሐ የሚገቡ ከሆነ የአምላክ ‘ይቅርታ ብዙ’ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ኢሳይያስ 55:7

ይሁንና አንዳንዶች አካሄዳቸውን ለማስተካከል እምቢተኛ ከሆኑ ይሖዋ * እነሱን ከማጥፋት ሌላ ምርጫ አይኖረውም። የአምላክ መንግሥት “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ . . . ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ” የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝ ተስፋ እንዲፈጸም ያደርጋል። (መዝሙር 37:34) ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑት ክፉዎች ሲጠፉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሙስና ከሚያስከትለው ጉዳት ይገላገላሉ።

ሰይጣን ዲያብሎስ

ልበ ደንዳና ከሆኑ ኃጢአተኞች መካከል ቀንደኛው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ደስ የሚለው ነገር፣ ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ይሖዋ በቅርቡ ያግደዋል። ከጊዜ በኋላም አምላክ፣ ሰይጣንን ጨርሶ ያጠፋዋል። ከዚያ በኋላ ይህ ጨካኝ ፍጡር፣ የሰው ልጆች ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽሙ ተጽዕኖ ማሳደር አይችልም።

አምላክ የሙስና መንስኤ የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ያስወግዳል ብሎ ማሰብ የሕልም እንጀራ ይመስል ይሆናል። ‘በእርግጥ አምላክ እንዲህ ያሉ ለውጦች ማምጣት ይችላል? ከሆነ እስካሁን እርምጃ ያልወሰደው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እንዲህ ብለህ መጠየቅህ ተገቢ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም አጥጋቢ መልስ ይሰጥሃል። * በቅርቡ ሙስና ሙሉ በሙሉ እንደሚወገድ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ራስህ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

^ አን.8 የኢየሱስ ሞት ከኃጢአት የሚቤዠን እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።

^ አን.12 የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።

^ አን.15 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3, 8 እና 11 ተመልከት።