በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ዕዳ በሚኖርባችሁ ጊዜ

ዕዳ በሚኖርባችሁ ጊዜ

ያኒስ፦ * “በግሪክ በደረሰው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ንግዴ ከሰረ፤ በመሆኑም የቤታችንን እና የክሬዲት ካርድ ዕዳችንን ክፍያዎች መፈጸም አቃተን። በጣም ከመጨነቄ የተነሳ እንቅልፍ መተኛት አልቻልኩም።”

ካተሪና፦ “ቤታችንን ራሳችን ስለሠራነው በጣም እንወደዋለን፤ በመሆኑም ይህን ቤት ልናጣው እንደምንችል ማሰብ በጣም ከበደኝ። ዕዳችንን መክፈል ስለምንችልበት መንገድ ከያኒስ ጋር ብዙ ጊዜ እንጨቃጨቅ ነበር።”

ዕዳ በቤተሰብ ውስጥ ውጥረት እንዲሰፍን አልፎ ተርፎም ቤተሰቡ እንዲፈርስ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ጄፍሪ ዱ የተባሉ ተመራማሪ፣ ዕዳ ያለባቸው ባልና ሚስት አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ እንደሚቀንስ፣ ብዙ እንደሚጨቃጨቁ እንዲሁም ደስታ እንደሚያጡ ደርሰውበታል። ከሌሎች ጉዳዮች ይበልጥ ከዕዳና ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚነሳ ጭቅጭቅ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ እንዲሁም ባልና ሚስት እንዲጯጯሁና እንዲደባደቡ ብሎም ከዚህ ጋር ተያያዥነት በሌላቸው ጉዳዮችም እንዲነታረኩ ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ አንጻር ዋነኛው የፍቺ መንስኤ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር አለመግባባት መሆኑ አያስደንቅም።

በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው ዕዳ እንቅልፍ ማጣት፣ ራስ ምታት፣ የሆድ ሕመም፣ ድንገተኛ ልብ ድካም፣ የመንፈስ ጭንቀትና የመሳሰሉትን የጤና ችግሮች ያስከትላል። ማርታ የምትባል አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ሉዊስ ያለብን ዕዳ በጣም ስለሚያስጨንቀው በቀን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በመኝታ ነበር። እተማመንበት የነበረው ሰው ምንም ማድረግ የማይችል ሆነ።” እንዲያውም አንዳንዶች ውጥረቱ ከአቅማቸው በላይ ይሆንባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቢቢሲ እንደዘገበው በደቡብ ምሥራቅ ሕንድ የምትኖርና 840 የአሜሪካ ዶላር የሚያህል ዕዳ የነበረባት አንዲት እናት ክፍያዋን በጊዜው መፈጸም ስላቃታት ሕይወቷን አጥፍታለች። ይህች እናት ገንዘቡን የተበደረችው ልጆቿን ለማሳከም ነበር።

የአንተም ቤተሰብ በዕዳ ምክንያት ውጥረት ውስጥ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? ባለትዳሮች ከዕዳ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸውን አንዳንድ የተለመዱ ተፈታታኝ ሁኔታዎችና እነዚህን ሁኔታዎች ለመቋቋም ሊረዷችሁ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመልከት።

ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ እርስ በርስ እንወቃቀሳለን።

ሉላሽ እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል፦ “ባለቤቴን ‘ገንዘብ ታባክኛለሽ’ እያልኩ እወቅሳት ነበር፤ እሷ ደግሞ በቂ ገንዘብ የሌለን እኔ ቋሚ ሥራ ስለሌለኝ እንደሆነ በመግለጽ ታማርር ነበር።” ታዲያ አንድ ባልና ሚስት፣ ዕዳ በመካከላቸው መቃቃር እንዳይፈጥር ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

ቁልፉ፦ ዕዳውን ለመክፈል ተባብራችሁ ሥሩ።

ምናልባት ቤተሰቡ ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቅ ምክንያት የሆነው አንደኛው የትዳር ጓደኛ ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን ይህን ባደረገው ግለሰብ ላይ በቁጣ መገንፈል ችግሩን ለመፍታት የሚፈይደው ነገር አይኖርም። በኤፌሶን 4:31 ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችሁ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው በዚህ ወቅት ነው፤ ጥቅሱ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ” ይላል።

እርስ በርሳችሁ ከመጣላት ይልቅ ችግሩን ለመፍታት ተባብራችሁ ሥሩ። ስቴፋኖስ የሚባል አንድ ባል እሱና ሚስቱ እንዴት በኅብረት እንደሠሩ ሲገልጽ “ዕዳችንን እንደጋራ ጠላታችን አድርገን ተመለከትነው” ብሏል። እንዲህ ዓይነቱ ትብብር በምሳሌ 13:10 ላይ ከሚገኘው “ጥበብ . . . ምክርን በሚቀበሉ [“እርስ በርስ በሚመካከሩ፣” NW] ዘንድ ትገኛለች” ከሚለው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ስለዚህ ብቻችሁን መፍትሔ ለመፈለግ ከመሞከር ይልቅ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የገጠማችሁን ችግር በግልጽ ከተነጋገራችሁ በኋላ ተስማምታችሁ እርምጃ ውሰዱ።

ልጆቻችሁም ዕዳውን ለመወጣት በምታደርጉት ጥረት ሊያግዟችሁ ይችላሉ። በአርጀንቲና የሚኖር ኤድጋርዶ የሚባል አንድ አባት ቤተሰቡ ምን እንዳደረገ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ትንሹ ልጄ አዲስ ብስክሌት እንዲገዛለት ፈልጎ ነበር፤ ይህን ለማድረግ አቅማችን የማይፈቅድበትን ምክንያት አስረዳነው። አዲስ በመግዛት ፋንታ የአያቱን ብስክሌት ሰጠነው፤ እሱም በጣም ወደደው። በቤተሰብ መተባበር ጥቅም እንዳለው ከዚህ ተምሬያለሁ።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ስላለባችሁ ዕዳ በግልጽና በተረጋጋ ሁኔታ መነጋገር የምትችሉበት ጊዜ መድቡ። የሠራችሁት ጥፋት ካለ አምናችሁ ተቀበሉ። ይሁንና ስላለፈው ነገር በመወያየት ጊዜ ከማባከን ይልቅ ከዚህ በኋላ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ በምታደርጓቸው ውሳኔዎች ለመስማማት ጥረት አድርጉ።—መዝሙር 37:21፤ ሉቃስ 12:15

ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ ከዕዳ ጨርሶ የምንላቀቅ አይመስልም።

ኤንሪኬ “በንግድ ሥራዬ ምክንያት ከፍተኛ ዕዳ ነበረብኝ፤ በአርጀንቲና የተከሰተው የገንዘብ ቀውስ ደግሞ ሁኔታውን አባባሰው” በማለት ያስታውሳል። “በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ባለቤቴ ቀዶ ሕክምና አስፈለጋት። በሸረሪት ድር ተተብትቤ የተያዝኩ ያህል ጭራሽ ከዕዳ መውጣት እንደማልችል ተሰማኝ።” በብራዚል የሚኖር ሮቤርቶ የሚባል ሰው ንግዱ ሲከስር ያጠራቀመውን ገንዘብ በሙሉ አጣ፤ በዚያ ላይ ደግሞ ከ12 ባንኮች ብድር ነበረበት። “የጓደኞቼን ዓይን ማየት በጣም አሳፍሮኝ ነበር። የማልረባ እንደሆንኩ ተሰማኝ” ብሏል።

በዕዳችሁ ምክንያት በተስፋ መቁረጥ፣ በጥፋተኝነት ስሜት ወይም በኀፍረት ብትዋጡ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ቁልፉ፦ ወጪና ገቢያችሁን ተቆጣጠሩ። *

 

1. ገቢያችሁንና ወጪያችሁን እወቁ። ለሁለት ሳምንት አሊያም ለአንድ ወር ያህል ገቢና ወጪያችሁን በሙሉ መዝግቡ። ለግብርና ለኢንሹራንስ ወይም ለልብስ መግዣና ለመሳሰሉት ነገሮች አልፎ አልፎ የምታወጡትን ወጪም በዚህ መዝገብ ላይ አስፍሩ፤ እነዚህን ወጪዎች በየወሩ ከፋፍሏቸው።

2. ገቢያችሁን አሳድጉ። ተጨማሪ ሰዓት በመሥራት፣ ልጆች በማስጠናት፣ የባልትና ውጤቶች በመሸጥ፣ የእጅ ሙያ ካላችሁ በዚህ መስክ በመሥራት እና በመሳሰሉት መንገዶች ገቢያችሁን ማሳደግ ትችላላችሁ። ልትጠነቀቁበት የሚገባ ነገር፦ ሥራችሁ መንፈሳዊ ነገሮችን ጨምሮ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ሌሎች ጉዳዮች የምታውሉትን ጊዜ እንዳይሻማባችሁ ተጠንቀቁ።

ዕዳውን ከቤተሰባችሁ ጋር ተባብራችሁ ለመወጣት የሚያስችሏችሁ መንገዶች ፈልጉ

3. ወጪዎቻችሁን ቀንሱ። አንድ ነገር በእርግጥ የሚያስፈልጋችሁ ካልሆነ በቀር በርካሽ ዋጋ ስላገኛችሁት ብቻ አትግዙ። (ምሳሌ 21:5) ከላይ የተጠቀሰው ኤንሪኬ “አንድን ነገር ለመግዛት አለመቸኮል ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ዕቃው በእርግጥ ያስፈልጋችሁ ይሁን አይሁን ለመወሰን ጊዜ ይሰጣችኋል” ብሏል። ቀጥሎ አንዳንድ ተጨማሪ ምክሮች ቀርበዋል።

  • መኖሪያ ቤት፦ የሚቻል ከሆነ ኪራዩ አነስተኛ ወደሆነ ቤት ተዛወሩ። ኤሌክትሪክ፣ ውኃና ነዳጅ በመቆጠብ ለእነዚህ ነገሮች የምታወጡትን ወጪ ቀንሱ።

  • ምግብ፦ አዘውትራችሁ ውጭ በመብላት ፋንታ ምሳችሁን ወይም መክሰሳችሁን ከቤት ይዛችሁ ሂዱ። ለምግብ የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች በርካሽ ወይም በጅምላ ከሚሸጥባቸው ቦታዎች ግዙ። በብራዚል የምትኖረው ዦኤልማ “የመንገድ ዳር ገበያዎች ከመነሳታቸው በፊት ከገዛሁ አትክልትና ፍራፍሬ በቅናሽ ዋጋ አገኛለሁ” በማለት ትናገራለች።

  • መጓጓዣ፦ መኪና የግድ የማያስፈልጋችሁ ከሆነ ሽጡት፤ እንዲሁም መኪናችሁን በአዲስ ሞዴል ለመለወጥ ከመቸኮል ይልቅ በጥሩ ሁኔታ ያዙት። የሕዝብ መጓጓዣ ተጠቀሙ፤ አለዚያም በምትችሉበት ጊዜ ሁሉ በእግር ሂዱ።

ወጪዎቻችሁን ከቀነሳችሁ ያላችሁን ገንዘብ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ማዋል ትችላላችሁ።

4. ዕዳችሁ ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ካወቃችሁ በኋላ እርምጃ ውሰዱ። በመጀመሪያ፣ ለእያንዳንዱ ዕዳ የሚከፈለውን ወለድና ሌሎች ተጨማሪ ክፍያዎች፣ ዕዳውን በወቅቱ አለመክፈል የሚያስከትለውን ቅጣት እንዲሁም ውዝፍ ክፍያ ካለባችሁ አጣሩ። አበዳሪዎች ሊያጭበረብሩ ስለሚችሉ በብድር ስምምነቱ ወይም በሒሳብ መጠየቂያው ላይ የሰፈሩትን ቃላት በጥንቃቄ መርምሩ። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የአጭር ጊዜ የብድር አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ተቋም፣ ከ400 በመቶ በላይ ወለድ ቢያስከፍልም 24 በመቶ ብቻ እንደሚያስከፍል አድርጎ ገልጿል።

ቀጥሎ ደግሞ ዕዳችሁን የምትከፍሉበትን ቅደም ተከተል ወስኑ። አንደኛው ዘዴ፣ ከፍተኛ ወለድ የሚጠይቁ ዕዳዎችን አስቀድሞ መክፈል ነው። ሌላው አማራጭ ደግሞ ትናንሽ ዕዳዎችን አስቀድሞ መክፈል ነው፤ እንዲህ ስታደርጉ በየወሩ የምትከፍሏቸው ዕዳዎች ብዛት ስለሚቀንስ ዕዳችሁ ቀለል እንዳለ ይሰማችኋል። ከፍተኛ ወለድ የሚጠይቁ ብድሮች ካሉባችሁ አነስተኛ ወለድ የሚጠይቅ አዲስ ብድር በመውሰድ የቀድሞውን ብድር መክፈሉ የተሻለ ሊሆን ይችላል።

በመጨረሻም፣ ዕዳችሁን መክፈል ካቃታችሁ የምትከፍሉበትን መንገድ በተመለከተ አዲስ ውል መፈጸም እንድትችሉ ከአበዳሪዎቻችሁ ጋር ለመደራደር ጥረት አድርጉ። የምትከፍሉበት ጊዜ እንዲራዘምላችሁ ወይም የወለዱን መጠን እንዲቀንሱላችሁ መጠየቅ ትችሉ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንድ አበዳሪዎች ሙሉውን ብድር ወዲያውኑ መክፈል የምትችሉ ከሆነ የዕዳችሁን መጠን ሊቀንሱላችሁ ይስማሙ ይሆናል። ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ያላችሁበትን ሁኔታ በምታስረዱበት ጊዜ ሐቀኞችና ትሑቶች ሁኑ። (ቆላስይስ 4:6፤ ዕብራውያን 13:18) ማንኛውንም ውል በጽሑፍ አስፍሩ። መጀመሪያ ያቀረባችሁት ጥያቄ ተቀባይነት ባያገኝ እንኳ ማስተካከያ እንዲደረግላችሁ ደጋግማችሁ መጠየቅ ካስፈለጋችሁ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትበሉ።—ምሳሌ 6:1-5

እርግጥ ነው፣ ገንዘባችሁን ስለምትጠቀሙበት መንገድ እቅድ ስታወጡ እውነታውን ማገናዘብ ያስፈልጋችኋል። ብዙውን ጊዜ ገንዘብ ‘ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር ክንፍ አውጥቶ ስለሚበርር’ በጣም ጥሩ እቅድ ብታወጡም እንኳ ከእናንተ ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ያሰባችሁት ላይሳካ ይችላል።—ምሳሌ 23:4, 5

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በጀት ካወጣችሁ በኋላ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ወጪ መቀነስ ወይም ገቢ መጨመር የሚችለው እንዴት እንደሆነ ተወያዩ። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ሲያደርግ መመልከታችሁ ያለባችሁን ዕዳ ለመክፈል ሁላችሁም ተባብራችሁ እንድትሠሩ ያነሳሳችኋል።

ተፈታታኝ ሁኔታ 3፦ ዕዳ አእምሯችንን ተቆጣጥሮታል።

ዕዳን ለመክፈል የሚደረገው ትግል በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቦታ እንዳንሰጥ ሊያደርግ ይችላል። ዮርዮስ የሚባል አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ትልቁ ችግራችን መላ ሕይወታችን በዕዳው ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆኑ ነበር። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ቸል ተባሉ።”

ቁልፉ፦ ለገንዘብ ከተገቢው በላይ ቦታ አትስጡ።

ከዕዳ ለመገላገል ከፍተኛ ጥረት ብታደርጉም ዕዳችሁን ከፍላችሁ ለመጨረስ ብዙ ዓመታት ሊፈጅባችሁ ይችላል። እስከዚያው ድረስ ግን ስላላችሁበት ሁኔታ የሚኖራችሁ አመለካከት በእናንተ ላይ የተመካ ነው። ስለ ገንዘብ ወይም ስለ ዕዳችን ብቻ ከማሰብ ይልቅ “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተላችን ብልኅነት ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:8

ባለን ረክቶ መኖር ሀብት ከማካበት የበለጠ ደስታ ያስገኛል

በገንዘብ ረገድ ባላችሁ ረክታችሁ መኖራችሁ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እንድታውቁ]” ያስችላችኋል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች’ ከተባሉት መካከል ከአምላክና ከቤተሰባችሁ ጋር ያላችሁ ወዳጅነት ይገኝበታል። ከላይ የተጠቀሰው ዮርዮስ እንዲህ ይላል፦ “ዕዳዎቻችንን ሙሉ በሙሉ ከፍለን ባንጨርስም አሁን በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ይህ ጉዳይ አይደለም። እርስ በርሳችንና ከልጆቻችን ጋር እንዲሁም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አብረን የበለጠ ጊዜ ስለምናሳልፍ ትዳራችን ደስታ የሰፈነበት ሆኗል።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸውን ትልቅ ቦታ የምትሰጧቸው ነገሮች በዝርዝር ጻፉ። ከዚያም በዝርዝራችሁ ላይ ለጠቀሳችሁት ለእያንዳንዱ ነገር የምታውሉትን ጊዜና ጉልበት እንዴት መጨመር እንደምትችሉ አስቡ።

ዕዳ የሚያመጣቸው ችግሮች ውጥረት የሚፈጥሩ ከመሆኑም ሌላ ዕዳን ለመክፈል የሚደረገው ጥረት መሥዋዕትነት ይጠይቃል፤ ይሁን እንጂ ውጤቱ ሲታይ ያደረጋችሁት ጥረት አያስቆጭም። በፖላንድ የሚኖረው አንጄይ እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል፦ “ባለቤቴ አንዲት የሥራ ባልደረባዋ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ስትበደር ዋስ ሆና እንደነበርና ሴትየዋ ብድሯን ሳትከፍል እንደተሰወረች ሳውቅ በቤታችን ውስጥ ውጥረት ነግሦ ነበር።” እሱና ባለቤቱ ምን እንዳደረጉ መለስ ብሎ ሲያስታውስ እንዲህ ብሏል፦ “ችግሩን በጋራ ለመወጣት ያደረግነው ጥረት ይበልጥ አቀራርቦናል።”

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.17 ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው የመስከረም 2011 ንቁ! ላይ “ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም—እንዴት?” በሚል የሽፋን ርዕስ ሥር የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ . . .

  • ቤተሰቤ ከዕዳ እንዲላቀቅ መርዳት የምችለው እንዴት ነው?

  • ያለብን ዕዳ በትዳራችን ውስጥ ውጥረት እንዳይፈጥር አልፎ ተርፎም ትዳራችንን እንዳያፈርሰው ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?