በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ሰዎች አምላክ ጨካኝ ነው የሚሉት ለምንድን ነው?

ሰዎች አምላክ ጨካኝ ነው የሚሉት ለምንድን ነው?

“አምላክ ጨካኝ ነው?” የሚለው ጥያቄ አስደንግጦሃል? አንዳንዶች ይህ ጥያቄ ያስደነግጣቸው ይሆናል፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ግን አምላክ ጨካኝ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ አላቸው፤ አምላክ ጨካኝ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎችም አልጠፉም። ሆኖም ሰዎች እንዲህ የሚያስቡት ለምንድን ነው?

ከተፈጥሮ አደጋዎች የተረፉ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ብለው ይጠይቃሉ፦ “አምላክ እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱ የሚፈቅደው ለምንድን ነው? በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው ነገር ግድ የለውም ማለት ነው? ወይስ ጨካኝ ነው?”

ሌሎች ደግሞ እንደዚህ የሚሰማቸው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ ነው። እነዚህ ሰዎች ስለ ኖኅ የጥፋት ውኃ በሚያነቡበት ጊዜ ‘አፍቃሪ የሆነ አምላክ እነዚያን ሁሉ ሰዎች እንዴት ያጠፋል? ጨካኝ ነው ማለት ነው?’ ብለው ያስባሉ።

አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ይፈጠሩብሃል? ወይም ደግሞ አምላክ ጨካኝ እንደሆነ ለሚሰማቸው ሰዎች ምን መልስ እንደምትሰጥ ግራ ይገባሃል? በዚያም ሆነ በዚህ፣ ቀጥሎ የቀረበውን ጥያቄ መመርመሩ ጠቃሚ ነው።

ጭካኔን የምንጠላው ለምንድን ነው?

በአጭር አነጋገር፣ ጭካኔን የምንጠላው ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ስላለን ነው። በዚህ ረገድ ከእንስሳት በእጅጉ እንለያለን። ፈጣሪያችን የሠራን “በራሱ መልክ” ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ይህ ምን ማለት ነው? የእሱን ባሕርያት የማንጸባረቅ፣ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን የመከተል እንዲሁም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ሰጥቶናል ማለት ነው። እስቲ አስበው፦ ጭካኔን የምንጠላው ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ከአምላክ በማግኘታችን ከሆነ አምላክም ቢሆን ጭካኔን ይጠላል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም?

በተጨማሪም አምላክ “መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው” በማለት የተናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ አምላክ ከእኛ የበለጠ ጭካኔን እንደሚጠላ ያረጋግጣል። (ኢሳይያስ 55:9) አምላክ ጨካኝ ነው ብለን የምንደመድም ከሆነ ከዚህ ጥቅስ በተቃራኒ ‘የእኛ መንገድ ከእሱ መንገድ ይበልጣል’ ብለን መናገር አይሆንብንም? በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ከመድረሳችን በፊት ተጨማሪ ማስረጃዎችን መመልከታችን ብልህነት ነው። ምናልባትም ጥያቄያችን ሊሆን የሚገባው አምላክ ጨካኝ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ሳይሆን ‘አምላክ የወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች ጭካኔ የሚመስሉት ለምንድን ነው?’ የሚለው ነው። የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ ‘ጭካኔ’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።

አንድ ሰው ጨካኝ ነው ስንል አንድን ነገር ለመፈጸም ያነሳሳው ምክንያት መጥፎ እንደሆነ እየተናገርን ነው። ጨካኝ የሆነ ሰው በሌሎች ሥቃይ ይደሰታል፤ ወይም ለጭንቀታቸው ደንታ የለውም። አንድ አባት ልጁን የሚቀጣው ልጁ ስሜቱ ሲጎዳ ማየት ስለሚያስደስተው ከሆነ ጨካኝ ነው። ይሁን እንጂ ልጁን የሚቀጣው እሱን ለማስተማር ወይም ከጉዳት ለመጠበቅ ብሎ ከሆነ ጥሩ አባት ነው። ከዚህ ቀደም ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ተረድተውህ ያውቁ ከነበረ፣ አንድ ሰው አንድን ነገር ለመፈጸም የተነሳሳበትን ምክንያት በትክክል መረዳት ሊከብደን እንደሚችል ሳታውቅ አትቀርም።

አንዳንድ ሰዎች አምላክ ጨካኝ ነው ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጓቸውን ሁለት ምክንያቶች፣ ይኸውም በዛሬው ጊዜ የምናያቸውን የተፈጥሮ አደጋዎችና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን መለኮታዊ የጥፋት ፍርዶች እንመልከት። ታዲያ እውነታውን ስንመረምር ምን ድምዳሜ ላይ እንደርስ ይሆን?