በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጭፍን ጥላቻ የጸዳ ዓለም ይመጣ ይሆን?

ከጭፍን ጥላቻ የጸዳ ዓለም ይመጣ ይሆን?

“ሕልም አለኝ።” እነዚህ ቃላት የተወሰዱት አሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ማለትም ነሐሴ 28 ቀን 1963 ካቀረበው እጅግ ዝነኛ ንግግሩ ላይ ነው። ኪንግ ይህን ቀልብ የሚስብ አባባል በመጠቀም አንድ ቀን ሰዎች ከዘር ጥላቻ ነፃ የሆነ ሕይወት እንደሚኖራቸው የነበረውን ሕልም ወይም ተስፋ ገልጾ ነበር። ይህን ምኞቱን የገለጸው በዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩ አድማጮች ቢሆንም በብዙ አገሮች ውስጥ የእሱን አርማ አንግበው የተነሱ በርካታ ሰዎች አሉ።

ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለ ሰብዓዊ መብት ንግግር ሲሰጥ

ኪንግ ንግግሩን ካቀረበ ከሦስት ወራት በኋላ ማለትም ኅዳር 20 ቀን 1963 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማንኛውንም ዓይነት የዘር መድልዎ ለማስወገድ ያወጣውን አዋጅ ከመቶ የሚበልጡ አገሮች ተቀበሉ። ከዚያ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታትም ሌሎች ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ከተደረጉ በኋላ ‘ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን መጋቢት 21 ቀን 2012 የሚከተለውን ተናግረዋል፦ “ዘረኝነትን፣ የዘር መድልዎን፣ የሌላ አገር ዜጋን መጠራጠርንና ተዛማጅነት ያላቸውን ሌሎች ችግሮችን ለማስቀረት ብሎም ለማጥፋት ብዙ ጠቃሚ ስምምነቶችና ዝግጅቶች አልፎ ተርፎም የተጠናከሩ ዓለም አቀፋዊ መዋቅሮች አሉ። ያም ሆኖ ዘረኝነት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ሥቃይ ማስከተሉን ቀጥሏል።”

ዘረኝነትንና ሌሎች ዓይነት ጭፍን ጥላቻዎችን በመዋጋት ረገድ አንዳንድ መሻሻሎች በተደረጉባቸው አገሮችም እንኳ ሳይቀር መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ አለ፦ በእርግጥ ሰዎች በውስጣቸው ያለውን ሥር የሰደደ ጭፍን ጥላቻ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ችለዋል? ወይስ መሻሻል ያለ የመሰለው ሰዎቹ እንዲህ ያለውን ስሜት መደበቅ ስለቻሉ ነው? አንዳንዶች እንደሚናገሩት ከሆነ እንዲህ ዓይነቶቹ መሻሻሎች ግፋ ቢል ያስገኙት ውጤት መድልዎን መከላከል እንጂ ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መድልዎ ሊታይና በሕግ ሊያስቀጣ የሚችል ተግባር ነው፤ ጭፍን ጥላቻ ግን ከሰዎች ውስጣዊ አስተሳሰብና ስሜት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በሕግ ቁጥጥር ሊደረግበት አይችልም።

በመሆኑም ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ ከተፈለገ የመድልዎ ተግባሮችን መግታት ብቻ ሳይሆን ሰዎች ከራሳቸው ቡድን ውጪ ላሉ ግለሰቦች ያላቸውን አመለካከትና ስሜት እንዲለውጡ ማድረግም ያስፈልጋል። ታዲያ ይህ በእርግጥ ሊሆን የሚችል ነገር ነው? ከሆነስ እንዴት? ሰዎች ይህን ለውጥ ማድረግ እንደሚችሉ ብቻ ሳይሆን እንዲህ እንዲያደርጉ ሊረዳቸው የሚችለው ነገር ምን እንደሆነ ጭምር የሚያሳዩ አንዳንድ እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎችን እስቲ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ ጭፍን ጥላቻን እንዲያስወግዱ ረድቷቸዋል

“አሁን ከጭፍን ጥላቻ ማነቆ ነፃ እንደወጣሁ ይሰማኛል።”—ሊንዳ

ሊንዳ፦ የተወለድኩት በደቡብ አፍሪካ ነው። ነጭ ያልሆኑ ደቡብ አፍሪካውያንን በሙሉ ዝቅተኛ፣ ያልተማሩ፣ የማይታመኑና ነጮችን ለማገልገል የተፈጠሩ እንደሆኑ አድርጌ እመለከታቸው ነበር። በወቅቱ ባልረዳውም በጭፍን ጥላቻ ማነቆ ተይዤ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስጀምር ግን ይህ አስተሳሰቤ ተለወጠ። “አምላክ እንደማያዳላ” ብሎም ከቆዳ ቀለማችን ወይም ከምንናገረው ቋንቋ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለልባችን መሆኑን ተገነዘብኩ። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ ምሳሌ 17:3) በፊልጵስዩስ 2:3 ላይ ያለው ጥቅስ፣ ሁሉም ሰው ከእኔ እንደሚበልጥ አድርጌ የማስብ ከሆነ ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ እንደምችል እንድገነዘብ ረዳኝ። እነዚህን የመሳሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን በሕይወቴ ተግባራዊ ማድረጌ የቆዳ ቀለማቸው ምንም ይሁን ምን ለሌሎች አሳቢነት እንዳሳይ ረድቶኛል። አሁን ከጭፍን ጥላቻ ማነቆ ነፃ እንደወጣሁ ይሰማኛል።

“አምላክ ሰዎችን የሚመለከተው እንዴት እንደሆነ መረዳት ቻልኩ።”—ማይክል

 ማይክል፦ ያደግሁት አውስትራሊያ ውስጥ ነጮች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ ሲሆን ለእስያውያን፣ በተለይም ለቻይናውያን በጣም ከፍተኛ ጥላቻ አዳብሬ ነበር። መኪና እየነዳሁ እስያዊ የሚመስል ሰው ካየሁ መስተዋቱን ዝቅ አድርጌ “አንተ እስያዊ፣ አገርህ ግባ!” በማለት ደስ የማይሉ ነገሮችን እናገር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ግን አምላክ ሰዎችን የሚመለከተው እንዴት እንደሆነ መረዳት ቻልኩ። አምላክ ከየትም ይምጡ ከየት ወይም ምንም ዓይነት መልክ ይኑራቸው ሁሉንም ሰዎች እንደሚወድ ተረዳሁ። አምላክ ለሰዎች ያለው ፍቅር ልቤን ስለነካው ጥላቻዬ ወደ ፍቅር ተለወጠ። እንዲህ ዓይነት አስደናቂ ለውጥ በራሴ ላይ ማየቴ አስገርሞኛል። አሁን ከሁሉም አገሮች ከመጡና የተለያየ አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር መሆን በጣም ያስደስተኛል። ይህም የአስተሳሰብ አድማሴን ያሰፋው ሲሆን ታላቅ እርካታም አምጥቶልኛል።

“አመለካከቴን በማስተካከል . . . ሰላም ፈጠርኩ።”—ሳንድራ

ሳንድራ፦ እናቴ የተወለደችው ናይጄሪያ ውስጥ ዴልታ በተባለ ግዛት በሚገኘው ኡሙኔዴ ከተማ ነው። የአባቴ ቤተሰቦች ግን የኤዶ ግዛት ተወላጆችና የኤሳን ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። በዚህ ልዩነት የተነሳ እናቴ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ የአባቴ ቤተሰቦች ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸው ያሳዩአት ነበር። በዚህም ምክንያት የኤሳን ቋንቋ ከሚናገር ማንኛውም ሰው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለመፍጠርና ከኤዶ ግዛት የሆነ ሰው ላለማግባት ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ነገሮችን ከተለየ አቅጣጫ ማየት ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንደማያዳላና እሱን የሚፈሩ ሁሉ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው ስለሚናገር ‘እኔ ማን ሆኜ ነው ሰዎችን በጎሣቸው ወይም በቋንቋቸው ምክንያት የምጠላው?’ ብዬ አሰብኩ። በመሆኑም አመለካከቴን በማስተካከል ከአባቴ ቤተሰቦች ጋር ሰላም ፈጠርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጌ ደስታና የአእምሮ ሰላም አስገኝቶልኛል። በተጨማሪም ሰዎች የኑሮ ደረጃቸው፣ ዘራቸው፣ ቋንቋቸው ወይም ብሔራቸው ምንም ይሁን ምን ከእነሱ ጋር ተስማምቼ እንድኖር ረድቶኛል። ደግሞስ ምን ዓይነት ሰው ያገባሁ ይመስላችኋል? የኤዶ ግዛት ተወላጅና የኤሳን ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ሰው ነው።

እነዚህና ሌሎች ብዙ ሰዎች፣ ሥር የሰደደ ጭፍን ጥላቻን እንዲያስወግዱ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳቸው የቻለው ለምንድን ነው? የአምላክ ቃል ስለሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው  ለሌሎች ያለውን አመለካከትና ስሜት እንዲቀየር የማድረግ ኃይል አለው። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውም ዓይነት ጭፍን ጥላቻ ለማስወገድ ምን ነገር እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።

የአምላክ መንግሥት ማንኛውንም ዓይነት ጭፍን ጥላቻ ያስወግዳል

የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ኃይለኛ የጥላቻ ስሜቶችን ለመቆጣጠርና ከሥረ መሠረታቸው ነቅሎ ለማውጣት ሊረዳ ቢችልም ጭፍን ጥላቻን ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገጽ ለማስወገድ ግን በቅድሚያ መጥፋት የሚኖርባቸው ሌሎች ሁለት ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው፣ ኃጢአትና ሰብዓዊ አለፍጽምና ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአት የማይሠራ የለም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (1 ነገሥት 8:46) ስለዚህ የቱንም ያህል ጥረት ብናደርግ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው” በማለት እንደጻፈው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ከራሳችን ጋር ትግል ማድረግ ይኖርብናል። (ሮም 7:21) በመሆኑም በጊዜ ሂደት ልባችን ወደ ጭፍን ጥላቻ ሊያመሩ ወደሚችሉ “ክፉ ሐሳቦች” ሊመለስ ይችላል።—ማርቆስ 7:21

ሁለተኛው፣ የሰይጣን ዲያብሎስ ተጽዕኖ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “ነፍሰ ገዳይ” በማለት የሚጠራው ሲሆን “መላውን ዓለም እያሳሳተ” እንዳለ ይናገራል። (ዮሐንስ 8:44፤ ራእይ 12:9) ጭፍን ጥላቻ ይህን ያህል የተስፋፋውና የሰው ዘር ጠባብነትን፣ መድልዎንና የዘር ማጥፋትን ጨምሮ ከዘር፣ ከሃይማኖት እንዲሁም ከማኅበራዊ ሕይወት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ችግሮችን ማስወገድ ያቃተው ለዚህ ነው።

በመሆኑም ጭፍን ጥላቻ ከምድረ ገጽ ጨርሶ እንዲጠፋ ከተፈለገ ኃጢአት፣ ሰብዓዊ አለፍጽምናና የሰይጣን ዲያብሎስ ተጽዕኖ መወገድ አለባቸው። የአምላክ መንግሥት ይህን እንደሚያከናውን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።

ኢየሱስ ክርስቶስ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለው እንዲጸልዩ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:10) ሁሉንም ዓይነት መድልዎና ጭፍን ጥላቻ ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት የፍትሕ መዛባት የሚወገደው በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ነው።

የአምላክ መንግሥት ሲመጣና ምድርን ሲቆጣጠር ሰይጣን ‘ይታሰራል’ ወይም “ብሔራትን እንዳያሳስት” ሙሉ በሙሉ ይታገዳል። (ራእይ 20:2, 3) ከዚያ በኋላ ‘ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ምድር’ ማለትም ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይኖራል። *2 ጴጥሮስ 3:13

በዚያ ጻድቅ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ወደ ፍጽምና ስለሚደርሱ ከኃጢአት ነፃ ይሆናሉ። (ሮም 8:21) የአምላክ መንግሥት ዜጎች እንደመሆናቸው መጠን “ጕዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም።” ለምን? ምክንያቱም “ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:9) በዚያ ዘመን የሰው ዘር በሙሉ የይሖዋን መንገዶች የሚማር ከመሆኑም ሌላ ፍቅር በማሳየት ረገድ የእሱን ምሳሌ ይከተላል። ይህ በእርግጥም የጭፍን ጥላቻ ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ “ምክንያቱም በአምላክ ዘንድ መድልዎ የለም።”—ሮም 2:11

^ አን.17 ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት በቅርቡ ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3, 8 እና 9 ተመልከት።