በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ

የአምላክን ስም ታውቀዋለህ? በስሙስ ትጠቀማለህ?

የአምላክን ስም ታውቀዋለህ? በስሙስ ትጠቀማለህ?

ስሙን የማታውቀው የቅርብ ጓደኛ ሊኖርህ ይችላል? ሊኖርህ እንደማይችል የታወቀ ነው። ኢሪና የምትባል በቡልጋሪያ የምትኖር አንዲት ሴት እንዳለችው “የአምላክን ስም ሳታውቅ ወደ እሱ መቅረብ አትችልም።” ደስ የሚለው ነገር ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው አምላክ ወደ እሱ እንድትቀርብ ይፈልጋል። በመሆኑም አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው” በማለት ራሱን አስተዋውቆሃል።—ኢሳይያስ 42:8 NW

አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው” በማለት ራሱን አስተዋውቆሃል።—ኢሳይያስ 42:8 NW

ይሖዋ የሚለውን ስም ማወቅህና በስሙ መጠቀምህ ያን ያህል አስፈላጊ ነው? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የአምላክ ስም የሚጻፍባቸው ቴትራግራማተን ተብለው የሚጠሩት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ ላይ 7,000 ጊዜ ገደማ ይገኛሉ። የዚህን ስም ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ ሌላ ስም የለም። ይህ በእርግጥም ይሖዋ ስሙን እንድናውቅና እንድንጠቀምበት እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው። *

ብዙውን ጊዜ ሁለት ሰዎች ጓደኝነት የሚጀምሩት ስም በመተዋወቅ ነው። አንተስ የአምላክን ስም ታውቀዋለህ?

ይሁንና አንዳንዶች፣ አምላክ ቅዱስና ሁሉን ቻይ ስለሆነ የእሱን ስም መጥራታችን ክብሩን ዝቅ እንደሚያደርግበት ይሰማቸዋል። እርግጥ ነው፣ የቅርብ ጓደኛህን ስም አላግባብ እንደማታነሳ ሁሉ የአምላክንም ስም ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጥራት አይኖርብህም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እሱን የሚወዱ ሰዎች ስሙን እንዲያከብሩና እንዲያሳውቁለት ይፈልጋል። (መዝሙር 69:30, 31፤ 96:2, 8) ኢየሱስ፣ “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ ተከታዮቹን ማስተማሩን አስታውስ። እኛም የአምላክን ስም ለሌሎች የምናሳውቅ ከሆነ ስሙ እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እናደርጋለን። እንዲህ ማድረጋችን ከእሱ ጋር ይበልጥ ያቀራርበናል።—ማቴዎስ 6:9

አምላክ “ስሙን ለሚያከብሩ” ሰዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሚልክያስ 3:16) እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎችን በተመለከተ ይሖዋ እንዲህ የሚል ቃል ገብቷል፦ “ስሜን አውቆአልና እከልለዋለሁ። ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ።” (መዝሙር 91:14, 15) ከይሖዋ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ከፈለግን ስሙን ማወቃችንና በስሙ መጠቀማችን በጣም አስፈላጊ ነው።

^ አን.4 የአምላክ ስም በተለምዶ ብሉይ ኪዳን እየተባለ በሚጠራው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፤ የሚያሳዝነው ግን ይህ ስም ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል። ተርጓሚዎቹ የአምላክን ስም “ጌታ” ወይም “አምላክ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ መጠሪያዎች ተክተውታል። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 195-197 ተመልከት።