በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

ጭንቀት የሌለበት ቦታ የለም!

ጭንቀት የሌለበት ቦታ የለም!

“ምግብ ለመግዛት ስሄድ ያገኘሁት ብስኩት ብቻ ነበር፤ ያውም ከተለመደው ዋጋ በ10,000 እጥፍ ጨምሮ ነበር! በቀጣዩ ቀን በየትኛውም ሱቅ ውስጥ ምንም የሚሸጥ ምግብ አልነበረም።”—ፖል፣ ዚምባብዌ

“ባለቤቴ ትቶን እንደሚሄድ ቁጭ አድርጎ ነገረኝ። እንዲህ ዓይነቱን ክህደት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው? ልጆቼስ ምን ይሆናሉ?”—ጃኔት፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደወሉ ሲጮኽና ሮኬቶች ሲተኮሱ ከአደጋው የምሸሸግበት ቦታ ለማግኘት ሮጬ በመሄድ ወለሉ ላይ ተኛሁ። ሰዓታት ካለፉ በኋላም እንኳ እጆቼ ይንቀጠቀጡ ነበር።”—አሎና፣ እስራኤል

የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ በሆነ’ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ብዙዎች በኢኮኖሚ ቀውስ፣ በቤተሰብ መፍረስ፣ በጦርነት፣ ገዳይ በሆኑ በሽታዎችና በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ አደጋዎች የተነሳ ይጨነቃሉ። ይህ አልበቃ ብሎ ‘በሰውነቴ ላይ የወጣብኝ እብጠት ወደ ካንሰርነት ይቀየርብኝ ይሆን?’ ‘የልጅ ልጆቼ ወደፊት ምን ዓይነት ዓለም ይጠብቃቸው ይሆን?’ እንደሚሉት ያሉ በግለሰብ ደረጃ የሚያስጨንቁ ነገሮች ያጋጥሙናል።

ጭንቀት ሁሉ መጥፎ አይደለም። ፈተና ልንፈተን ስንል፣ አንድ ልዩ ችሎታ የሚጠይቅ ትዕይንት እንድናሳይ ስንጠየቅ ወይም ሥራ ለመቀጠር ለቃለ መጠይቅ ስንቀርብ ትንሽ መረበሻችን አይቀርም። በተጨማሪም አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን በተመለከተ ተገቢውን ፍርሃት ማሳየታችን ከጉዳት ይጠብቀናል። ይሁን እንጂ ከመጠን ያለፈ ወይም የማያባራ ጭንቀት ጎጂ ነው። በቅርቡ ከ68,000 በላይ በሆኑ አዋቂዎች ላይ የተደረጉ ተከታታይ ጥናቶች መጠነኛ የሚባለው ጭንቀትም እንኳ ዕድሜን ሊያሳጥር እንደሚችል አረጋግጠዋል። እንግዲያውስ ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ይኖራል?” ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። በእርግጥም ጭንቀት የማንንም ዕድሜ አያስረዝምም። በመሆኑም ኢየሱስ “መጨነቃችሁን ተዉ” በማለት መክሯል። (ማቴዎስ 6:25, 27 የግርጌ ማስታወሻ) ይሁንና መጨነቃችንን መተው የምንችለው እንዴት ነው?

ይህን ማድረግ የምንችለው ጥበብን በሥራ ላይ በማዋል፣ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት በማዳበርና ስለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ በመገንባት ነው። አሁን የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ባያጋጥሙንም እንኳ ወደፊት ሊያጋጥሙን ይችላሉ። በመሆኑም ፖል፣ ጃኔትና አሎና እነዚህን እርምጃዎች መውሰዳቸው ጭንቀትን እንዲቋቋሙ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።