በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላል?

የሞቱ ሰዎች ያላቸው ተስፋ—እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

የሞቱ ሰዎች ያላቸው ተስፋ—እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

የሞቱ ሰዎች ዳግመኛ ሕያው ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ አላሰበም። በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በክርስቶስ ተስፋ ያደረግነው ለዚህ ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ይሁንና ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል።” (1 ቆሮንቶስ 15:19, 20) ጳውሎስ የትንሣኤ ተስፋ እርግጠኛ መሆኑን ያምን ነበር። ኢየሱስ ራሱ ከሞት መነሳቱ ለዚህ ዋስትና ይሆናል። * (የሐዋርያት ሥራ 17:31) ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ረገድ የመጀመሪያው ሰው ስለነበር ጳውሎስ “በኩራት” ሲል ጠርቶታል። ኢየሱስ የመጀመሪያ ከሆነ ሌሎች ሰዎችም ይኖራሉ ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።

ኢዮብ አምላክን “የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ” ብሎታል። —ኢዮብ 14:14, 15

የትንሣኤ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንድትሆን የሚያስችልህን ሌላ ማስረጃ እንመልከት። ይሖዋ የእውነት አምላክ ነው። ደግሞም ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም።’ (ቲቶ 1:2) ይሖዋ ዋሽቶ አያውቅም፤ ወደፊትም ቢሆን አይዋሽም። የትንሣኤን ተስፋ ከሰጠና ሊፈጽመው እንደሚችል ካሳየም በኋላ ተስፋው ውሸት ሆኖ እንዲቀር ያደርጋል? እንዲህ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!

ይሖዋ የትንሣኤን ተስፋ የሰጠው ለምንድን ነው? አፍቃሪ ስለሆነ ነው። ኢዮብ “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?” በማለት ጠይቆ ነበር። ከዚያም “አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ። የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ” ብሏል። (ኢዮብ 14:14, 15) ኢዮብ አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባቱ ከሞት ሊያስነሳው እንደሚጓጓ እርግጠኛ ነበር። አምላክ ተለውጧል? “እኔ ይሖዋ ነኝና፤ አልለወጥም” በማለት ተናግሯል። (ሚልክያስ 3:6) አምላክ አሁንም ቢሆን የሞቱ ሰዎች ዳግም ሕያው ሆነው የተሟላ ጤና እንዲሁም ደስታ አግኝተው ሲኖሩ ለማየት ይጓጓል። ይህ ደግሞ ማንኛውም አፍቃሪ የሆነ ወላጅ ልጁን በሞት ሲያጣ የሚያድርበት ምኞት ነው። ልዩነቱ ግን አምላክ ምኞት ብቻ ሳይሆን የተመኘውን ነገር መፈጸም የሚያስችል ኃይልም አለው።—መዝሙር 135:6

ሞት አስከፊ ችግር ነው፤ አምላክ ግን ለዚህ ችግር መፍትሔ አዘጋጅቷል

ይሖዋ የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ቅስማቸው ለተሰበረ ሰዎች ወደር የሌለው ደስታ ማጎናጸፍ እንዲችል ለልጁ ኃይል ሰጥቶታል። ኢየሱስ ስለ ትንሣኤ ምን ይሰማዋል? ኢየሱስ አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት የአልዓዛር እህቶችና ወዳጆች የደረሰባቸው ከባድ ሐዘን ተሰምቶት ነበር፤ እንዲያውም ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:35) በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ አንድ ልጇን በሞት ያጣችውን በናይን የምትኖር መበለት ሲያይ “በጣም አዘነላትና ‘በቃ፣ አታልቅሺ’ አላት።” ከዚያም ልጇን ወዲያውኑ አስነሳላት። (ሉቃስ 7:13) በመሆኑም ኢየሱስ ሐዘንና ሞት የሰዎችን ስሜት በጥልቅ እንደሚጎዳ ይገነዘባል። ወደፊት በመላው ምድር ላይ ሐዘን ተወግዶ በደስታ እንዲተካ ሲያደርግ ደግሞ ምን ያህል በሐሴት ይሞላ ይሆን!

ሐዘን ደርሶብህ ያውቃል? ሞት መፍትሔ የሌለው ችግር እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም መፍትሔ አለው፤ ይህም አምላክ በልጁ አማካኝነት ወደፊት የሚያከናውነው ትንሣኤ ነው። አምላክ ይህ ችግር መፍትሔ ሲያገኝ በገዛ ዓይንህ እንድታይ ይፈልጋል። በዚያ ተገኝተህ የምትወዳቸውን ሰዎች እቅፍ አድርገህ እንድትቀበል ይመኝልሃል። የዘላለም ሕይወት አግኝታችሁ የረጅም ጊዜ እቅድ ስታወጡ ይታይህ፤ በዚያን ጊዜ መለያየት የሚባል ነገር አይኖርም!

ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ላየነል እንዲህ ብሏል፦ “ከጊዜ በኋላ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ሰማሁ። መጀመሪያ ላይ መቀበል በጣም ከብዶኝ ነበር፤ እንዲያውም ስለዚህ ጉዳይ የነገረኝን ሰው አላመንኩትም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ስመረምር ይህ ተስፋ እውነት መሆኑን ተረዳሁ! አያቴን ዳግመኛ ለማየት በጣም እጓጓለሁ።”

ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ለማወቅ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር እርግጠኛ የሆኑበትን ምክንያት ከራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለማሳየት ፈቃደኞች ናቸው። *

^ አን.3 ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ለማየት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 78-86 ተመልከት።