በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በጥንት ዘመን

አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በጥንት ዘመን

ሕዝቡ በጭቆና ቀንበር ሥር ወድቋል። እፎይታ ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ አምላክ ቢጸልዩም ወዲያውኑ መፍትሔ አላገኙም። እነዚህ ሰዎች የአምላክ ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን ናቸው። ሲጨቁናቸው የነበረው ደግሞ ኃያሉ የግብፅ ብሔር ነው። (ዘፀአት 1:13, 14) አምላክ፣ ከግብፅ የጭቆና ቀንበር እስኪያላቅቃቸው ድረስ እስራኤላውያን ለብዙ ዓመታት መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። በመጨረሻም አምላክ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ። (ዘፀአት 3:7-10) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ግብፃውያንን የተዋጋው አምላክ ራሱ እንደሆነ ይናገራል። በግብፅ ላይ አውዳሚ መቅሰፍቶችን በተከታታይ ያወረደ ከመሆኑም ሌላ የግብፅ ንጉሥንና ሠራዊቱን ቀይ ባሕር ውስጥ አሰጠማቸው። (መዝሙር 136:15) ይሖዋ አምላክ ለሕዝቡ ሲል “ኃያል ተዋጊ” መሆኑን አሳየ።—ዘፀአት 15:3, 4

አምላክ ራሱ ግብፃውያንን የተዋጋ መሆኑ ጦርነትን በደፈናው እንደማይቃወም ያሳያል። እንዲያውም ሕዝቡ የሆኑት እስራኤላውያን እንዲዋጉ የፈቀደባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ እጅግ ክፉ የነበሩትን ከነአናውያንን እንዲወጉ አዟቸው ነበር። (ዘዳግም 9:5፤ 20:17, 18) አምላክ፣ ጨቋኝ የነበሩትን ፍልስጤማውያን እንዲዋጋ የእስራኤል ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት መመሪያ ሰጥቶታል። አልፎ ተርፎም ዳዊት ድል እንዲቀዳጅ የሚያስችለውን የጦር ስልት ነግሮታል።—2 ሳሙኤል 5:17-25

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ የክፋትና የጭቆና ድርጊቶች የእስራኤላውያንን ሕልውና ስጋት ላይ ሲጥሉ አምላክ ሕዝቡንና እውነተኛውን አምልኮ ከአደጋ ለመጠበቅ ሲል እስራኤላውያን እንዲዋጉ ፈቅዶላቸዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ ትእዛዝ ስለተካሄዱት እንዲህ ያሉ ጦርነቶች ቀጥሎ የቀረቡትን ሦስት ቁልፍ ነጥቦች ልብ በል፦

  1. በጦርነቱ ላይ ማን መሰለፍ እንዳለበት የሚወስነው አምላክ ራሱ ነበር። በአንድ ወቅት አምላክ ለእስራኤላውያን “እናንተ ይህን ጦርነት መዋጋት አያስፈልጋችሁም” ብሏቸዋል። ለምን? አምላክ ራሱ ስለሚዋጋላቸው ነው። (2 ዜና መዋዕል 20:17፤ 32:7, 8) በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ ከተጠቀሰው ጋር በሚመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ወቅቶችም እሱ ራሱ ተዋግቶላቸዋል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አምላክ በጥንቷ እስራኤል የነበሩት ሕዝቦቹን እሱ በሚደግፋቸው ጦርነቶች ላይ እንዲዋጉ አዟቸው ነበር፤ ለምሳሌ ያህል የተስፋይቱ ምድር ይዞታቸውን ለማስከበርና ከጥቃት ለመከላከል በሚደረጉ ጦርነቶች ተካፍለዋል።—ዘዳግም 7:1, 2፤ ኢያሱ 10:40

  2. ጦርነቱ መቼ መካሄድ እንዳለበት የሚወስነው አምላክ ራሱ ነበር። የአምላክ አገልጋዮች፣ ጭቆናና ክፋት ይፈጽሙ የነበሩትን በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦች ለመዋጋት አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ በትዕግሥት መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በራሳቸው ውሳኔ ጦርነት እንዲያካሂዱ አይፈቀድላቸውም ነበር። በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ጦርነት በገቡባቸው ወቅቶች የአምላክን ድጋፍ አጥተዋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው እስራኤላውያን አምላክ ሳይፈቅድ ጦርነት ሲያካሂዱ አብዛኛውን ጊዜ ለሽንፈት ተዳርገዋል። *

  3. አምላክ በከነአናውያን ላይ ጦርነት እንዲታወጅ ቢያዝም እንደ ረዓብና ቤተሰቦቿ የመሰሉ አንዳንድ ግለሰቦች ከሞት እንዲተርፉ አድርጓል

    አምላክ ክፉዎችን ጨምሮ በሰዎች ሞት አይደሰትም። ይሖዋ አምላክ የሕይወት ምንጭና የሰው ዘር ፈጣሪ ነው። (መዝሙር 36:9) በመሆኑም ሰዎች ሲሞቱ የማየት ፍላጎት የለውም። የሚያሳዝነው ግን ሌሎችን ለመጨቆን አልፎ ተርፎም ለመግደል በክፋት የሚያሴሩ ሰዎች አሉ። (መዝሙር 37:12, 14) አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ክፋት ለማስቆም በክፉዎች ላይ ጦርነት እንዲካሄድ የፈቀደባቸው ጊዜያት አሉ። ያም ሆኖ እስራኤላውያን እንደዚህ ባሉት ጦርነቶች እንዲካፈሉ ባደረገባቸው ዘመናት በሙሉ እስራኤላውያንን ለሚጨቁኑት ጭምር “መሐሪ” እና “ለቁጣ የዘገየ” መሆኑን አሳይቷል። (መዝሙር 86:15) ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ከአንዲት ከተማ ጋር ጦርነት ከመግጠማቸው በፊት የከተማዋ ነዋሪዎች አቋማቸውን የሚለውጡበትና ጦርነቱ መቅረት የሚችልበት አጋጣሚ ለመስጠት “የሰላም ጥሪ” እንዲያስተላልፉ አምላክ ደንግጎ ነበር። (ዘዳግም 20:10-13) በዚህ መንገድ አምላክ ‘በክፉው ሰው ሞት ደስ እንደማይሰኝ ይልቁንም ክፉው ሰው አካሄዱን አስተካክሎ በሕይወት እንዲኖር እንደሚፈልግ’ አሳይቷል።—ሕዝቅኤል 33:11, 14-16 *

ቀደም ሲል እንዳየነው አምላክ በጥንት ዘመን ጦርነትን የተለያዩ የጭቆናና የክፋት ድርጊቶችን ለማስቆም የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ አድርጎ ተመልክቶታል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት መቼ መካሄድ እንዳለበትና በጦርነቱ ማን መካፈል እንደሚኖርበት የመወሰን መብት ያለው አምላክ እንጂ ሰዎች አልነበሩም። ይሁንና አምላክ ጦርነት እንዲካሄድ ሲፈቅድ ደም እንደተጠማ የሚጠቁም ዝንባሌ ታይቶበታል? በጭራሽ፤ እሱ ዓመፅን ይጠላል። (መዝሙር 11:5) ለመሆኑ አምላክ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን በጀመረበት በአንደኛው መቶ ዘመን ለጦርነት የነበረው አመለካከት ተለውጦ ይሆን?

^ አን.7 ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት እስራኤላውያን አምላክ ከአማሌቃውያንና ከከነዓናውያን ጋር እንዳይዋጉ የሰጣቸውን ትእዛዝ ጥሰው ጦርነት በገጠሙ ጊዜ ተሸንፈዋል። (ዘኁልቁ 14:41-45) ከብዙ ዓመታት በኋላ ደግሞ ታማኙ ንጉሥ ኢዮስያስ የአምላክን ፈቃድ ሳይጠይቅ ጦርነት ገጥሞ ነበር፤ ይህ በችኮላ የወሰደው እርምጃ ሕይወቱን አሳጥቶታል።—2 ዜና መዋዕል 35:20-24

^ አን.8 እስራኤላውያን ከከነአናውያን ጋር ጦርነት ከመግጠማቸው በፊት የሰላም ጥሪ አላስተላለፉም ነበር። ለምን? ምክንያቱም ከነአናውያን ክፉ አካሄዳቸውን ማስተካከል የሚችሉበት 400 ዓመታት ነበራቸው። እስራኤላውያን ጦርነት ሊገጥሟቸው በመጡበት ጊዜ ከነአናውያን በክፉ አቋማቸው ቀጥለው ነበር። (ዘፍጥረት 15:13-16) ስለዚህ ሙሉ በሙሉ መጥፋት ነበረባቸው። ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ አካሄዳቸውን የለወጡ ከነአናውያን ከጥፋት ተርፈዋል።—ኢያሱ 6:25፤ 9:3-27