በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴ እንዲሻሻል የሚረዳኝ እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴ እንዲሻሻል የሚረዳኝ እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የተለየ ነው። የፈጣሪያችንን ምክር የያዘ መጽሐፍ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መልእክቱ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” ይላል። (ዕብራውያን 4:12) መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሕይወታችን እንዲሻሻል ያደርጋል፤ አንደኛ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምንመራበት ምክር ይሰጠናል፤ ሁለተኛ ደግሞ አምላክንና ተስፋዎቹን እንድናውቅ ይረዳናል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ ያዕቆብ 4:8

ሕይወታችንን የምንመራበት ምክር ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስ በግል ሕይወትህ ውስጥ በሚያጋጥሙህ ጉዳዮችም ረገድ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ስለሚከተሉት ጉዳዮች ጠቃሚ ምክር ይሰጣል፦

በእስያ የሚኖሩ ቪሰንትና አነሉ የተባሉ አንድ ወጣት ባልና ሚስት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። እንደ ሌሎቹ አዲስ ተጋቢዎች ሁሉ እነሱም በባሕርይ እርስ በርስ መጣጣም እንዲሁም በግልጽ መነጋገር ከባድ ሆኖባቸው ነበር። በኋላ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበቡትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ቪሰንት እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብኩት ነገር በትዳራችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመፍታት ረድቶኛል። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋላችን ደስተኛ እንድንሆን ረድቶናል።” ባለቤቱ አነሉ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ማንበባችን ረድቶናል። አሁን በትዳራችንም ሆነ በሕይወታችን ውስጥ ባሉን ግቦች ደስተኛ ነኝ።”

አምላክን እንድታውቅ ይረዳሃል። ቪሰንት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከትዳር ሕይወቱ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በሌላ አቅጣጫም እንደረዳው ሲናገር “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ * እንድቀርብ ረድቶኛል” ብሏል። ቪሰንት የተናገረው ሐሳብ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ይኸውም ስለ አምላክ እንድታውቅ እንደሚረዳህ ይጠቁማል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብህ አምላክ ከሚሰጠው ምክር ተጠቃሚ እንድትሆን ብቻ ሳይሆን ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድትመሠርትም ይረዳሃል። በተጨማሪም አምላክ ለሰው ልጆች አስደሳች ተስፋ እንዳዘጋጀ እንድትገነዘብ ያስችልሃል፤ ወደፊት ሁላችንም “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” እያጣጣምን ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) እንዲህ ስላለው ተስፋ ልታውቅ የምትችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከጀመርክና በዚያው ከገፋህበት፣ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሞች ልታገኝ ይኸውም ሕይወትህ ሊሻሻልና አምላክን ልታውቅ ትችላለህ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ብዙ ጥያቄዎች ሊፈጠሩብህ ይችላሉ። ጥያቄዎች ሲፈጠሩብህ፣ ከ2,000 ዓመታት በፊት የኖረ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን የተወውን ጥሩ ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርግ። ይህ ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩት። የሚያነበውን ነገር ይረዳው እንደሆነ ሲጠየቅ “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” በማለት መልሷል። * ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ብቃት ያለው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፊልጶስ የሰጠውን እርዳታ በደስታ ተቀብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 8:30, 31, 34) አንተም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ከፈለግክ www.dan124.com/am በተባለው ድረ ገጽ ላይ የሚገኘውን ቅጽ መሙላት ወይም በዚህ መጽሔት ላይ ካሉት አድራሻዎች ወደ አንዱ መጻፍ ትችላለህ። አሊያም ደግሞ በአቅራቢያህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ወይም በአካባቢህ ወደሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ አዳራሽ መሄድ ትችላለህ። ታዲያ ዛሬውኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ለምን አትጀምርም? እንዲህ ማድረግህ ወደተሻለ ሕይወት ይመራሃል።

መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት ስለመሆኑ ጥያቄ ካለህ መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ መሆኑን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? የሚለውን አጭር ቪዲዮ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን። ቪዲዮውን jw.org/am ላይ የሕትመት ውጤቶች > ቪዲዮዎች > መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው ሥር ማግኘት ትችላለህ።

^ አን.8 መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጣቸው ሌሎች ጠቃሚ ምክሮች ለማወቅ jw.org/am የተባለውን ድረ ገጻችንን መጎብኘት ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው በሚለው ሥር ተመልከት።

^ አን.10 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።

^ አን.11 በተጨማሪም በዚህ መጽሔት ውስጥ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ያለው አደጋ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።