በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

የአንዱ ትርፍ የሌላውን ጉድለት ይሸፍናል

የአንዱ ትርፍ የሌላውን ጉድለት ይሸፍናል

ጥቅምት 1, 2020

 የይሖዋ ምሥክሮች ከ200 በሚበልጡ አገሮች ሃይማኖታዊና የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ። ከእነዚህ አገሮች መካከል ግን በአገራቸው የሚደረገውን መዋጮ ተጠቅመው ወጪያቸውን መሸፈን የሚችሉት 35 የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ታዲያ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው አገሮች ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን የሚችሉት እንዴት ነው?

 የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ይገመግማል። ከዚያም በጥንቃቄ በጀት ወጥቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ በአገሪቱ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሚጠይቀው ወጪ በላይ መዋጮ ካገኘ የተረፈውን ገንዘብ በቂ ገንዘብ ለሌላቸው አገሮች እንዲሰጥ ዝግጅት ተደርጓል። ይህ ዝግጅት የተደረገው ‘በአንዳቸው ትርፍ የሌላውን ጉድለት ይሸፍኑ’ የነበሩትን የጥንት ክርስቲያኖች ምሳሌ በመከተል ነው። (2 ቆሮንቶስ 8:14) እነዚህ ክርስቲያኖች በዚህ መንገድ እርስ በርስ ይረዳዱ ነበር።

 ከሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የገንዘብ ድጋፍ ያገኙ ወንድሞች ምን ተሰምቷቸዋል? ለምሳሌ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ነዋሪ በቀን ውስጥ ከሁለት ዶላር ያነሰ ገቢ በሚያገኝባት በታንዛንያ የሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ በዚህ ዝግጅት አማካኝነት እድሳት ተደርጎለት ነበር። ይህን የስብሰባ አዳራሽ የሚጠቀመው የማፊንጋ ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእድሳቱ በኋላ የተሰብሳቢዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል! የይሖዋ ድርጅትና ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ላሳዩን ልግስና በጣም አመስጋኞች ነን፤ እንዲህ ያለ ውብ የአምልኮ ቦታ ማግኘት ችለናል።”

 በስሪ ላንካ የሚኖሩ አንዳንድ ወንድሞቻችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለምግብ እጥረት ተዳርገዋል። ከእነዚህ መካከል ኢማራ ፈርናንዶ እና ትንሹ ልጇ ኢኖሽ ይገኙበታል። ኢማራ እና ኢኖሽ በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች ባደረጉት መዋጮ ምክንያት የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ማግኘት ችለዋል። ራሳቸው ባዘጋጁት ካርድ ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ፍቅር ያሳዩንን ወንድሞች በጣም እናመሰግናለን። የዚህ ቤተሰብ አባል በመሆናችን በጣም ደስተኞች ነን፤ ደግሞም በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ ወንድሞቻችንን ሁሉ እንዲረዳቸው መጸለያችንን እንቀጥላለን።”

ኢማራ እና ኢኖሽ

 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚኖሩት የትም ይሁን የት ያላቸውን ነገር ለማካፈል ፈቃደኞች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢኖሽ ችግር ላይ የወደቁ ቤተሰቦችን ለመርዳት በሚደረገው ጥረት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሲል ትንሽ የመዋጮ ሣጥን ሠርቷል። ጓደሉፔ አልቫሬዝም ተመሳሳይ የልግስና መንፈስ አሳይታለች። በምትኖርበት የሜክሲኮ ግዛት ውስጥ አብዛኞቹ ሰዎች የሚያገኙት ገቢ በጣም አነስተኛ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ምንም የገቢ ምንጭ የላቸውም። ያም ሆኖ ግን ጓደሉፔ የምትችለውን ያህል መዋጮ ታደርጋለች። እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ላሳየኝ ደግነትና ታማኝ ፍቅር ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። እኔ የማደርገው መዋጮ ከሌሎቹ ጋር ተዳምሮ ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቼን ለመርዳት እንደሚጠቅም አውቃለሁ።”

 እርዳታ ወደሚያስፈልግባቸው አካባቢዎች ገንዘብ የሚልኩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲህ ማድረግ በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው። “ለበርካታ ዓመታት በአገራችን ሥራው የሚከናወነው ሌሎች አገሮች በሚያደርጉልን የገንዘብ ድጋፍ ነበር” በማለት በብራዚል ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለው አንቶኒ ካርቫልሆ ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ምክንያት አስደናቂ እድገት ማድረግ ችለናል። አሁን የኢኮኖሚ ሁኔታችን ስለተሻሻለ ሌሎችን የመርዳት መብት አግኝተናል። ወንድሞቻችን የስብከቱ ሥራ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው ይገነዘባሉ፤ በመሆኑም የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ሌሎችን መርዳት የሚችሉበትን መንገድ ይፈልጋሉ።”

 የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? በሌላ አገር ላሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በቀጥታ ገንዘብ በመላክ ሳይሆን ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ በማድረግ ነው። ይህን ማድረግ የሚችሉት “ለዓለም አቀፉ ሥራ” የሚል ጽሑፍ በተለጠፈበት የጉባኤው የመዋጮ ሣጥን ወይም በ​donate.dan124.com አማካኝነት ነው። በዚህ መልኩ ለምታደርጉት መዋጮ በጣም አመስጋኞች ነን።