ነቅታችሁ ጠብቁ!
2024ን በተስፋ መጀመር—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ብዙዎች በ2024 በዓለም ላይ የተጋረጡት ችግሮች ምንም መፍትሔ እንዳላቸው አይሰማቸውም። ሆኖም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ማግኘት እንችላለን። ከየት?
መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል
መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ሕይወታችንን ተስፋ አስቆራጭ ያደረጉብንን ችግሮች በሙሉ አምላክ እንደሚያስወግድልን ተስፋ ይሰጣል። በቅርቡ አምላክ “እንባን ሁሉ [ከዓይናችን] ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:4
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጣቸውን ተስፋዎች በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜም ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ አሉታዊ ስሜቶችን ለማስወገድና አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ሊረዱህ የሚችሉ ተስፋዎችን ይዟል። (ሮም 15:13) በተጨማሪም በውስጡ የሚገኙት ጠቃሚ ምክሮች በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙህን እንደ ድህነት፣ የፍትሕ መጓደልና ሕመም ያሉ ችግሮች ለመወጣት ሊረዱህ ይችላሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ በድህነት ያደገን አንድ ሰው ሰላምና ደስታ ለማግኘት የረዳው እንዴት ነው? ሁዋን ፓብሎ ስርሜንዮ፦ ይሖዋ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድመራ ረድቶኛል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ የጥፋተኝነት ስሜትን፣ ሐዘንን፣ ጭንቀትንና የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን የባዶነት ስሜት ለመቋቋም የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ተመልከት። “መጽሐፍ ቅዱስ ባነብ የሚያጽናናኝ ሐሳብ አገኝ ይሆን?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
ራሷን “የማስፈራና ለሌሎች ግድየለሽ” በማለት የገለጸች የጦር ሠራዊት አባል የነበረች አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስን መማሯ ተስፋ እንዲኖራት የረዳት እንዴት ነው? መሣሪያዬን ጣልኩ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
አንተም ሆንክ ቤተሰብህ 2024 አስደሳች ዓመት እንዲሆንላችሁ ማድረግ ትችላላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ይበልጥ መማር ትፈልጋለህ? በግለሰብ ደረጃ የምንሰጠውን ከክፍያ ነፃ የሆነ አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለምን አትሞክረውም? አምላክ በአሁኑ ጊዜ “ሰላም” ወደፊት ደግሞ “የተሻለ ሕይወት” የሚሰጥህ እንዴት እንደሆነ ተማር።—ኤርምያስ 29:11