በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 25, 2023
ማላዊ

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በቺቼዋ ቋንቋ ወጣ

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በቺቼዋ ቋንቋ ወጣ

ነሐሴ 18, 2023 የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ኬነዝ ኩክ የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በቺቼዋ ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መውጣቱ የተበሰረው በሊሎንግዌ፣ ማላዊ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በተካሄደው “በትዕግሥት ጠብቁ”! የተባለው የ2023 የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ዕለት ነበር። በስብሰባው ላይ የተገኙት ታዳሚዎች የታተመው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ደርሷቸዋል። እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸውን ከ​JW ቦክስ ጋር በማገናኘት የኤሌክትሮኒክ ቅጂውን ማውረድ ችለዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱን ያበሰረው ንግግር በ​JW የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት በቀጥታ ተላልፏል፤ በአገሪቱ ማዕከላዊና ደቡባዊ ክልሎች በሚገኙ ስታድየሞች፣ በገጠራማ አካባቢዎች በሚገኙ ትላልቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱባቸው ቦታዎች እንዲሁም በማላዊ ባሉ አብዛኞቹ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ የተሰበሰቡ ሰዎች ስርጭቱን መከታተል ችለዋል። በተጨማሪም በሞዛምቢክ፣ ቺቼዋ በሚነገርባቸው ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ የተመረጡ የስብሰባ አዳራሾች ስርጭቱ ተላልፏል። በመሆኑም ቁጥራቸው በድምሩ 77,112 የሆነ ሰዎች ንግግሩን ከሁለት ስታዲየሞች፣ በገጠራማ አካባቢ ከሚገኙ ትላልቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱባቸው ቦታዎች እንዲሁም ከተለያዩ የስብሰባ አዳራሾች ሆነው ንግግሩን ተከታትለዋል።

ቺቼዋ የማላዊ ብሔራዊ ቋንቋ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ከአሥር ሚሊዮን የሚበልጡ ተናጋሪዎች አሉት። በሞዛምቢክ፣ በዚምባብዌ፣ በዛምቢያ እና በደቡብ አፍሪካ ባሉ አንዳንድ ክፍሎችም ይነገራል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቺቼዋ ቋንቋ የወጣው በ2006 ሲሆን ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም ደግሞ የወጣው በ2010 ነበር። አሁን ወንድሞችና እህቶች ተሻሽሎ የተዘጋጀውን ሙሉውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቺቼዋ ቋንቋ በማግኘታቸው እጅግ ተደስተዋል።

አንድ አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ብዙዎቹ የቺቼዋ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚጠቀሙት በድሮ ቋንቋ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ነው። ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅሶች እንዲያነብቡ ስንጠይቃቸው በአብዛኛው ነጥቡን መረዳት ይከብዳቸዋል። የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም የሚጠቀማቸው ቃላት ግን በቀላሉ የሚገቡ ናቸው። እኔም በአገልግሎት ላይ ልጠቀምበት በጣም ጓጉቻለሁ!”

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የቺቼዋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ‘በይሖዋ ሕግ ደስ እንዲላቸው’ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 1:2