በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ፑኔት አጋርዋል፣ ዴልሮይ ዊልያምሰን፣ አሾክ ፓቴል (በላይ በኩል ከግራ ወደ ቀኝ)፤ ማርክ ስሌገር፣ ጆውኒ ፓልሙ፣ ሂሮሺ አዎኪ (በታች በኩል ከግራ ወደ ቀኝ)

ሐምሌ 10, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የይሖዋ ምሥክሮች ለሁለተኛ ጊዜ ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን አወጡ

የይሖዋ ምሥክሮች ለሁለተኛ ጊዜ ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን አወጡ

የይሖዋ ምሥክሮች ለሁለተኛ ሳምንት ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን አውጥተዋል። ሐምሌ 4, 2020 አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቢስላማ ቋንቋና በኦሮምኛ ወጣ። በቀጣዩ ቀን ማለትም ሐምሌ 5 ደግሞ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በላትቪያኛ እና በማራቲ ቋንቋዎች የወጣ ከመሆኑም ሌላ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቤንጋሊ እና በካረን (ስጋው) ቋንቋዎች ወጥቷል። መጽሐፍ ቅዱሶቹ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት መውጣታቸው የተገለጸው አስቀድመው በተቀረጹ ንግግሮች አማካኝነት ነው። አስፋፊዎች ልዩ ፕሮግራሙን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የተከታተሉ ሲሆን ይህን መንፈሳዊ ስጦታ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል።

ቢስላማ

የፊጂ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ማርክ ስሌገር የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በቢስላማ ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። በቫንዋቱ የሚኖሩት አስፋፊዎች በቢስላማ ቋንቋ ተዘጋጅቶ ወደ ቢስላማ የምልክት ቋንቋ የተተረጎመውን ፕሮግራም ተከታትለዋል።

የትርጉም ሥራው ከሦስት ዓመት በላይ የወሰደ ሲሆን ሁለት የትርጉም ቡድኖች በሥራው ተካፍለዋል። አንዲት ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞች አዲስ ዓለም ትርጉምን እንደሚወዱት እርግጠኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ለማንበብ ቀላል ነው፤ እንዲሁም የፊደል አጣጣሉ ሰዎች በስፋት የሚጠቀሙበትን ዘመናዊ የአጻጻፍ ዘዴ የተከተለ ነው። ይህ ትርጉም ሁላችንም እውነትን ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ እንድንረዳ ያግዘናል።”

ተሻሽሎ የወጣው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከ700 የሚበልጡትን የቢስላማ ቋንቋ ተናጋሪ አስፋፊዎች በግል ጥናታቸውና በአገልግሎታቸው እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።

ኦሮምኛ

የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዴልሮይ ዊልያምሰን አዲስ ዓለም ትርጉም በኦሮምኛ መውጣቱን አብስሯል። ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑትን 2,000 ገደማ አስፋፊዎች ጨምሮ በድምሩ 12,548 ወንድሞችና እህቶች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።

በቴክኒክ ችግር ምክንያት፣ አስቀድሞ የተቀረጸው ፕሮግራም በሳተላይት የቴሌቪዥን ጣቢያ አማካኝነት እንዲተላለፍ የበላይ አካሉ ፈቃድ ሰጥቷል። በተጨማሪም አስፋፊዎች ስብሰባውን በስልክ የሚያዳምጡበት አማራጭ ነበራቸው።

አምስት ተርጓሚዎች ለአምስት ዓመት ያህል በትርጉም ሥራው ተካፍለዋል። ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሰፊ በሆነው የኦሮምኛ መስክ ለሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ጠቃሚ መሣሪያ እንደሚሆን አንጠራጠርም።

ላትቪያኛ

አሥራ ሁለት ዓመት ከፈጀ ሥራ በኋላ አዲስ ዓለም ትርጉም በላትቪያኛ ወጥቷል። በላትቪያ የሚገኙት ሁሉም የላትቪያኛና የሩሲያኛ ጉባኤዎች ፕሮግራሙን እንዲከታተሉ ተጋብዘው ነበር።

መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን ያበሰረው የፊንላንድ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆውኒ ፓልሙ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “ለመረዳት ቀላልና ዘመናዊ የሆነው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በላትቪያኛ በመውጣቱ በጣም ተደስተናል። ይህ ትርጉም የላትቪያኛ ተናጋሪዎች የአምላክን ቃል በማጥናትና በማሰላሰል ይበልጥ ደስታ እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ተስፋ እናደርጋለን።”

አንደኛው ተርጓሚ አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያለውን ለምርምር የሚረዳ ገጽታ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ዘመናዊ ስልኮች ለአጠቃቀም ምቹና ብዙ ነገር ለማከናወን የሚረዱ እንደሆኑ ሁሉ ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምም በጥልቀት የግል ጥናት ለማድረግና ለማሰላሰል የሚረዱ ብዙ ገጽታዎች አሉት።”

ማራቲ

የማራቲ ቋንቋ አዲስ ዓለም ትርጉም የወጣው በሕንድ ለሚገኙ የማራቲ ቋንቋ ጉባኤዎች በሙሉ በተዘጋጀ ልዩ ፕሮግራም ላይ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን ያበሰረው የሕንድ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፑኔት አጋርዋል ነው።

ስድስት ተርጓሚዎች ይህን ሥራ ለማጠናቀቅ ለሦስት ዓመታት ያህል በትጋት ሠርተዋል። አንዷ ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ትርጉም በተለይ ወላጆችና የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚዎች ለልጆቻቸው ወይም ለጥናቶቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች እንዲያስተምሩ ይረዳቸዋል።”

አንዲት ሌላ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የተባለው የአምላክ ስም በበኩረ ጽሑፉ በነበረበት ቦታ ሁሉ እንዲገባ ማድረጉ እጅግ የሚያስደስት ነው። አንባቢዎች በሁሉም ገጽ ላይ ማለት ይቻላል የይሖዋን ስም ማግኘት ይችላሉ፤ ይህም የይሖዋ ስም የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ ያደርጋል።”

በማዕከላዊ ሕንድ የማራቲ ቋንቋን የሚናገሩ ከ83 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች አሉ።

ቤንጋሊ

የሕንድ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አሾክ ፓቴል የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቤንጋሊ ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። በሕንድና በባንግላዴሽ የሚገኙ ከ1,200 የሚበልጡ አስፋፊዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።

ቤንጋሊ በተናጋሪ ብዛት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ያለ ቋንቋ ሲሆን ከ265 ሚሊዮን የሚበልጡ ተናጋሪዎች አሉት። አብዛኞቹ ተናጋሪዎች በቀላሉ የሚረዱት ትርጉም ለማዘጋጀት በሕንድና በባንግላዴሽ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ተርጓሚዎችን ያቀፈ ቡድን ለሦስት ዓመት ያህል በትብብር ሠርቷል።

ወንድም ፓቴል በንግግሩ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ቤንጋሊ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ላይ ከተተረጎመባቸው የሕንድ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነው። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ሙሉ ትርጉም የወጣው በ1801 ነበር። ይህ ጥንታዊ ትርጉም የነበረው ጠንካራ ጎን ይሖዋ የተባለውን መለኮታዊው ስም መያዙ ነበር። በዘመናዊ ትርጉሞች ላይ ግን መለኮታዊው ስም ‘ጌታ’ በሚለው የማዕረግ ስም ተተክቷል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ለብዙዎች የሚጠቅም ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው።”

አንዱ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ትርጉም ይሖዋ አምላክ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እንደሚወድ እንዲሁም ስለ እሱና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲማሩ እንደሚፈልግ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።”

ካረን (ስጋው)

የምያንማር ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሂሮሺ አዎኪ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በካረን (ስጋው) ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። በስድስት ጉባኤዎችና አራት ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 510 ወንድሞችና እህቶች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።

የካረን (ስጋው) መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ ከአራት ዓመት በላይ ወስዷል። አንዱ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም በመስኩ ላይ ያሉት ሰዎች ይህን የካረን (ስጋው) መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ እንደሚያስደስታቸው እርግጠኛ ነኝ፤ ምክንያቱም የይሖዋን ስም በተገቢው ቦታ ላይ መልሶ አስገብቷል እንዲሁም ቀለል ያለ ቋንቋ ይጠቀማል። ግልጽ፣ ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል ነው። ይሖዋ ይህን ግሩም ስጦታ ስለሰጠን በጣም እናመሰግነዋለን፤ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ልባችንን በሚነካው ቋንቋ ማንበባችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳናል።”

አንዲት ሌላ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “አዲስ ዓለም ትርጉም የተዘጋጀው በዕለት ተዕለት በምንጠቀምበት ቋንቋ ነው፤ ስለዚህ አንባቢዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮችን ስሜት መረዳት፣ የነበሩበትን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናቸው መሣል እንዲሁም እነሱን በእምነታቸው መምሰል ይችላሉ።”

ወንድሞቻችን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በማግኘታቸው ተደስተናል። አዲስ የወጡት መጽሐፍ ቅዱሶች እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ አስፋፊዎች ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረባቸውንና እውነትን ለሌሎች ማካፈላቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚረዷቸው እንተማመናለን።—ዮሐንስ 17:17