በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥር 16, 2020
ዩናይትድ ኪንግደም

የብሪታንያ ቤቴል ቤተሰብ በቼልምስፎርድ ወደሚገኘው አዲስ ቤቴል መዛወር ጀመረ

የብሪታንያ ቤቴል ቤተሰብ በቼልምስፎርድ ወደሚገኘው አዲስ ቤቴል መዛወር ጀመረ

ጥር 1, 2020 የብሪታንያ ቤቴል ቤተሰብ በቼልምስፎርድ፣ ኤሴክስ አቅራቢያ ወደሚገኘው አዲስ ቤቴል መዛወር ጀመረ። እስከ መጋቢት 2020 ድረስ ሁሉም የሙሉ ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኞች ወደ አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ተዛውረው በዚያ መሥራትና መኖር እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ከ1959 አንስቶ የሚገኘው በሚል ሂል፣ ለንደን ነበር። የስብከቱ ሥራ እየተስፋፋ ሲሄድ በቤቴል የሚሠራውም ሥራ እየጨመረ በመምጣቱ ቅርንጫፍ ቢሮው ተስፋፍቶ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ሕንፃዎችንም እንዲያካትት ተደረገ። ይህም መጠነ ሰፊ የጥገና ሥራ እንዲከናወንና የቤቴል ቤተሰብ አባላትም ብዙ መጓጓዝ እንዲያስፈልጋቸው አድርጓል። ለተወሰነ ጊዜ ያህል በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የሕትመት ሥራም ይከናወን ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ ከሚውሉት ጽሑፎች መካከል ከ10 በመቶ የሚበልጠው የሚታተመው በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ነበር። የሕትመት ማዕከሉ ለ92 ዓመታት አገልግሎት ከሰጠ በኋላ መጋቢት 2018 ሥራውን አቁሞ ተሸጠ። a

በአዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ የግንባታ ሥራ የተካፈሉት ወንድሞችና እህቶች ጥር 1, 2020 ወደ አዲሱ ቤቴል የተዛወሩትን ቤቴላውያን ሲቀበሉ

አዲሱን የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ገንብቶ ለማጠናቀቅ አምስት ዓመት ፈጅቷል። ይህ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ በተለያዩ ቦታዎች ይከናወኑ የነበሩትን ሥራዎች በአንድ ቦታ ለመጠቅለል ያስችላል፤ ይህም ሥራው ቅልጥፍና እንዲኖረውና በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ እንዲቆጠብ ያደርጋል። ይህ ቤቴል ወርክሾፖችን የያዙ ሁለት ሕንፃዎችን፣ ቢሮዎችን እና ከ400 የሚበልጡ ሰዎችን ማኖር የሚችሉ ስድስት የመኖሪያ ሕንፃዎችን ያካትታል። በተጨማሪም የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የመመገቢያ አዳራሽ እና የተለያዩ ፕሮግራሞች ማካሄጃ ሊሆን የሚችል ለተለያየ ዓላማ የሚውል ሕንፃ አለው።

በአሁኑ ወቅት የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ በተለያዩ ክልሎች የሚከናወነውን የስብከት ሥራ በበላይነት ይከታተላል፤ ከእነዚህም መካከል ማልታ፣ አየርላንድ፣ አይል ኦፍ ማን፣ ጀርሲ፣ ገርንዚ እና ፎክላንድ ደሴቶች ይገኙበታል። በአዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በዋነኝነት ኦዲዮዎች እና ቪዲዮዎች እንዲሁም ዲጂታል ጽሑፎች ይዘጋጃሉ። በተጨማሪም ቅርንጫፍ ቢሮው ከ1,800 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ከ150,000 በላይ አስፋፊዎች የሚያከናውኑትን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማደራጀቱን ይቀጥላል።

ከሚያዝያ 6, 2020 ጀምሮ አዲሱን ቤቴል መጎብኘት ይቻላል። ጎብኚዎች ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በብሪታንያና በአየርላንድ’ እንዲሁም ‘በይሖዋ አስደናቂ ድርጅት ውስጥ ቤቴል የሚጫወተው ሚና’ እንደሚሉት ባሉ ርዕሰ ጉዳዮች የተዘጋጁ ኤግዚቢሽኖችን መመልከት ይችላሉ።

የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሃርዲ ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሥራው ሲካፈል ቆይቷል። እንደሚከተለው በማለት የብዙዎችን ስሜት ጠቅለል አድርጎ ገልጿል፦ “ይሖዋ ብሪታንያ ውስጥም ሆነ ውጭ ሀገር ያሉ በርካታ ወንድሞች በፈቃደኝነት እንዲነሳሱ አድርጓል። የተገኘው ውጤት ከጠበቅነው የላቀ ነው፤ ለዚህ ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ ነው።”—ኤፌሶን 3:20

a በአሁኑ ወቅት ለብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያስፈልጉት ጽሑፎች የሚታተሙት በዜልተርስ፣ ጀርመን በሚገኘው የማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ነው።

 

የብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኝበትን ውብ መልክዓ ምድር የሚያሳይ ፎቶግራፍ

አንዲት እህት በእንግዳ መቀበያ ክፍሉ ውስጥ ያለውን የጽሑፍ መደርደሪያ ስታዘጋጅ

ተመላላሽ ወንድሞችና እህቶች ከአዲሶቹ የመሰብሰቢያ ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ተሰብስበው

ወንድሞችና እህቶች በመመገቢያ አዳራሹ ውስጥ ምሳ ሲመገቡ፤ ለተለያየ ዓላማ የሚውለው ሕንፃ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ ይህ ነው

ቤቴል መግቢያ ላይ የሚገኝ “ኪንግደም ዌይ” ወይም “የመንግሥቱ መንገድ” የሚል ጽሑፍ የተጻፈበት የመንገድ ምልክት