በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

© Kim, Hyun-tae/iNaturalist. Licensed under CC-BY-4.0

ንድፍ አውጪ አለው?

የጃፓን የዛፍ እንቁራሪቶች ጥሪ

የጃፓን የዛፍ እንቁራሪቶች ጥሪ

 ወንድ የጃፓን የዛፍ እንቁራሪቶች ተደጋጋሚ የሆነና እምብዛም ዓላማ ያለው የማይመስል ጥሪ በማሰማት ይታወቃሉ። የሚገርመው ግን ብዙ እንቁራሪቶች በሚጮኹበት ጊዜም እንኳ የእያንዳንዱን ወንድ እንቁራሪት ድምፅ መለየት ይቻላል። በእነዚህ እንቁራሪቶች ላይ ጥናት የሚያደርጉ በጃፓን ያሉ ተመራማሪዎች፣ ሚስጥሩ በአንድ አካባቢ ያሉ ወንድ እንቁራሪቶች ሴት እንቁራሪቶችን በሚጠሩበት ጊዜ እጅግ የተቀናጀ የአጠራር ስልት ስለሚጠቀሙ እንደሆነ ደርሰውበታል።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ወንድ የጃፓን የዛፍ እንቁራሪቶች ሴት እንቁራሪቶችን ለመማረክ ጥሪ ያሰማሉ። በእንቁራሪቶቹ ሐብለ ድምፅ ውስጥ የተፈጠረው ድምፅ፣ ጉሮሯቸው ላይ ባለው የሚነፋ የድምፅ ከረጢት ውስጥ ሲያስተጋባ ይበልጥ ጎላ ብሎ ይሰማል።

 ሆኖም የአንዱ ወንድ እንቁራሪት ጥሪ ከሌላው እንቁራሪት ጥሪ ተለይቶ ሊሰማ የሚችለው እንዴት ነው? ተመራማሪዎች በአንድ አካባቢ ያሉ የጃፓን የዛፍ እንቁራሪቶች እንዲሁ ደስ ባላቸው ጊዜ ላይ ከመጮኽ ይልቅ ሁሉም የየራሳቸውን ተራ ጠብቀው እንደሚጮኹ ደርሰውበታል። ይህ ውጤታማ የሆነ ዘዴ የድምፅ መደራረብ እንዳይኖር ስለሚከላከል የእያንዳንዳቸው ድምፅ ጥርት ብሎ እንዲሰማ ከማስቻሉም በላይ ጊዜና ጉልበት ይቆጥባል። በተጨማሪም ተራቸውን ጠብቀው መጮኻቸው በየመሃሉ ክፍተት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

 በገመድ አልባ የመልእክት ማስተላለፊያ ዘዴዎች ላይ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎች፣ ውስብስብ የሆኑ የሒሳብ ስሌቶችን በመጠቀም የጃፓን የዛፍ እንቁራሪቶች ጥሪ የሚያሰሙበትን የተደራጀ ዘዴ ለመኮረጅ ሞክረዋል። ዓላማቸው እያንዳንዱ የመረጃ ጥቅል ከሚተላለፍበት ጊዜ ጋር በተያያዘ ማሻሻያ በማድረግ የመረጃ ጥቅሎቹ እርስ በርስ እንዳይቀላቀሉ ማድረግ ነው። ይህም የመረጃ ልውውጡን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግና ኃይል ለመቆጠብ ያስችላል።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? የጃፓን የዛፍ እንቁራሪቶች ያላቸው የተቀናጀ ጥሪ የማሰማት ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የመጣ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?