በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጃችሁን ከፖርኖግራፊ ጠብቁ

ልጃችሁን ከፖርኖግራፊ ጠብቁ

 “ፖርኖግራፊ ስላለው አደጋ ሳናውቅ ቀርተን አይደለም፤ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በደንብ እናውቃለን። ግን ልጃችን በቀላሉ ተጋላጭ ልትሆን እንደምትችል አላሰብንም ነበር።”—ኒኮል

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

 ልጆች ገና በትንሽነታቸው ለፖርኖግራፊ ሊጋለጡ ይችላሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ለፖርኖግራፊ የሚጋለጡበት ዕድሜ አሁን 11 ዓመት ሆኗል።

 ልጆች ሳይፈልጉ ለፖርኖግራፊ ሊጋለጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ኢንተርኔት ላይ ምንም ጉዳት የሌለው ነገር በሚፈልጉበት ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ በሚቃኙበት ጊዜ ፖርኖግራፊ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ኢንተርኔት ላይ ቪዲዮ ጌሞችን ሲጫወቱ የፖርኖግራፊ ማስታወቂያዎች ብቅ ይሉባቸው ይሆናል። ፖርኖግራፊ በተለያየ መልኩ ሊቀርብ ቢችልም በአብዛኛው የተለመደው በፎቶግራፍና በቪዲዮ መልክ የሚቀርበው ነው። ሆኖም የፆታ ስሜትን የሚያነሳሱና ድርጊቱን በግልጽ የሚያቀርቡ ጽሑፎች ወይም የድምፅ ቅጂዎችም በቀላሉ ይገኛሉ፤ እነዚህን በቀጥታ ከኢንተርኔት ላይ ማጫወት ወይም ማውረድ ይቻላል።

 ሊዘነጋ የማይገባው ሌላው ነገር ደግሞ፣ ግለሰቦች የመልእክት መላላኪያ አፕሊኬሽኖችን ወይም ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም ለልጆች የብልግና መልእክቶችን ሊልኩላቸው ይችላሉ። ከ900 በሚበልጡ ልጆች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፣ 90 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ሴቶችና 50 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ወንዶች አብረዋቸው ከሚማሩ ልጆች እርቃንን የሚያሳይ ፎቶግራፍ በተደጋጋሚ እንደሚላክላቸው ተናግረዋል።

 በስፋት የሚገኘው የፖርኖግራፊ ዓይነት፣ በአብዛኛው ዓመፅ የሚንጸባረቅበት ነው። በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውና በቀላሉ የሚገኘው የፖርኖግራፊ ዓይነት፣ በአብዛኛው ጥቃት ሲፈጸም የሚያሳይ ነው፤ እንዲህ ያለው ጥቃት ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚፈጸመው በሴቶች ላይ ነው።

 ፖርኖግራፊ ልጆችን ይጎዳል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ልጆች ከማይመለከቱ ልጆች ይበልጥ የሚከተሉት ነገሮች ያጋጥሟቸዋል፦

  •   በትምህርታቸው ወደ ኋላ ይቀራሉ

  •   ውጥረትና ጭንቀት ያጋጥማቸዋል፣ ለራሳቸው ያላቸው ግምትም ይቀንሳል

  •   ፆታዊ ጥቃት መፈጸም ምንም ችግር እንደሌለው አድርገው ያስባሉ

 ዋናው ነጥብ፦ ልጆች ፖርኖግራፊ ለሚያስከትለው መዘዝ የተጋለጡ ናቸው፤ ከማንም በተሻለ እርዳታ ሊያደርጉላቸው የሚችሉት ደግሞ ወላጆች ናቸው።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እኔ ዛሬ የማዝህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ፤ በልጆችህም ውስጥ ቅረጻቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድ ላይ ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሳ ስለ እነሱ ተናገር።”—ዘዳግም 6:6, 7

 ልጃችሁን ከፖርኖግራፊ መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

 ግንዛቤያችሁን አስፉ። ልጃችሁ a ለፖርኖግራፊ ይበልጥ ተጋላጭ የሚሆነው የት እና መቼ እንደሆነ አስቡ። ለምሳሌ ትምህርት ቤት በእረፍት ሰዓት ላይ ያለማንም ቁጥጥር ኢንተርኔት መጠቀም የሚችልበት አጋጣሚ አለ?

ልጃችሁ በተለያዩ መንገዶች ለፖርኖግራፊ ሊጋለጥ ይችላል

 ወደ ስልኩ የሚገባውን መረጃ ለመቆጣጠር ስለሚያስችሉ በሞባይሉ ላይ ያሉ ገጽታዎች ለማወቅ ሞክሩ፤ እንዲሁም ስለሚጠቀምባቸው አፕሊኬሽኖችና ስለሚጫወታቸው ጌሞች እወቁ። ለምሳሌ በአንዳንድ የመልእክት መላላኪያ አፕሊኬሽኖች ላይ የብልግና ይዘት ያላቸው መልእክቶች፣ ምስሎች ወይም ቪዲዮዎች ለአጭር ጊዜ ስክሪኑ ላይ ብቅ ይላሉ። በተጨማሪም ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣ የኢንተርኔት የቪዲዮ ጌሞች ላይ፣ ተጫዋቾች ፖርኖግራፊ መመልከት አልፎ ተርፎም ጨዋታው ላይ የፆታ ብልግና መፈጸም ይችላሉ።

 “ከልምድ የምናገረው ነገር ቢኖር፣ ልጃችሁ ዘመናዊ ስልክ ካለው እናንተም አጠቃቀሙን፣ ስልኩ ላይ የሚያያቸውን ነገሮች መቆጣጠር የሚቻልበትን ገጽታ እንዲሁም ልጃችሁ ስልኩ ላይ የሚያደርገውን ነገር መከታተል የምትችሉበትን መንገድ ማወቅ አለባችሁ።”—ዴቪድ

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የአስተዋይ ሰው ልብ እውቀትን ያገኛል፤ የጥበበኛም ጆሮ እውቀትን ለማግኘት ይጥራል።”—ምሳሌ 18:15

 ለፖርኖግራፊ ተጋላጭ እንዳይሆን የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ። ተጋላጭነቱን ለመቀነስ የሚያስችሏችሁን እርምጃዎች ውሰዱ። ለምሳሌ ያህል፦ በልጃችሁ ሞባይልም ሆነ በቤታችሁ ባሉ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ላይ ያሉትን የመቆጣጠሪያ ገጽታዎች በመጠቀም የፖርኖግራፊ ይዘት ያላቸው ነገሮች የትኛውም መሣሪያ ላይ ብቅ እንዳይሉ ተከላከሉ። “የወላጅ ቁጥጥር (parental control)” የሚለውን ገጽታ አብሩ። እንዲሁም ልጃችሁ የሚጠቀምባቸውን የይለፍ ቃሎች በሙሉ እወቁ።

 “በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችን ላይ ‘የወላጅ ቁጥጥር’ የሚለውን ገጽታ ማብራታችን፣ ልጃችን በስማርት ቴሌቪዥናችን ላይ መመልከት የሚችላቸውን ፕሮግራሞች መገደባችን እና በዘመናዊ ስልኩ ላይ የሚጠቀምበትን የይለፍ ቃል ማወቃችን ጠቅሞናል።”—ማውሪትስዮ

 “ወንዶች ልጆቼ ቪዲዮ ሲያዩ የክፍላቸውን በር እንዲዘጉ አልፈቅድላቸውም። የመኝታ ሰዓታቸው ሲደርስ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ክፍላቸው መግባትም አይችሉም።”—ጃንሉካ

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል።”—ምሳሌ 22:3

 ልጃችሁን አዘጋጁት። ፍላቪያ የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ስትል በሐቀኝነት ተናግራለች፦ “አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው ይህ ችግር ፈጽሞ እንደማያጋጥመው በማሰብ ከልጃቸው ጋር ስለ ፖርኖግራፊ ከማውራት ወደኋላ ይላሉ።” ሌሎች ወላጆች ደግሞ ‘ስለዚህ ጉዳይ ካነሳሁ፣ ልጄ ያላሰበውን ላሳስበው እችላለሁ’ ብለው ሊሰጉ ይችላሉ። ሆኖም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ስህተት ነው። ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጃቸው ለፖርኖግራፊ ከመጋለጡ በፊት አስቀድመው ያስተምሩታል። እንዲህ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

 የብልግና ምስሎች ብቅ ቢሉባቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ትናንሽ ልጆቻችሁን አስተምሯቸው። ለምሳሌ ዓይናቸውን መጨፈን ወይም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያቸውን ማጥፋት ይችላሉ። በተጨማሪም ስላዩት ወይም ስለሰሙት ነገር ለእናንተ እንዲነግሯችሁ አበረታቷቸው። b

 “ከልጃችን ጋር ፖርኖግራፊ ስላለው አደጋ ማውራት የጀመርነው በጣም ትንሽ እያለ ነው። አሥራ አንድ ዓመት ገደማ እያለ፣ ሞባይሉ ላይ ያወረደውን ጌም ሲጫወት የፖርኖግራፊ ማስታወቂያዎች ብቅ ማለት ጀመሩ። የራሱን ፎቶግራፍ እንዲልክ የሚጠይቅ መልእክትም ከምስሎቹ ጋር ተያይዞ ይመጣ ነበር። ምን ማድረግ እንዳለበት ቀደም ብለን ተነጋግረን ስለነበር ወዲያውኑ ወደ እኔ መጥቶ ስለተፈጠረው ነገር ነገረኝ።”—ማውሪትስዮ

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው፤ በሚያረጅበት ጊዜም እንኳ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።”—ምሳሌ 22:6

 ትላልቅ ልጆች ፖርኖግራፊ ለመመልከት፣ ለማዳመጥ ወይም ለማንበብ የሚቀርብላቸውን ፈተና እንዲቋቋሙ እርዷቸው። ለምሳሌ ልጃችሁ የቤተሰቡን መተዳደሪያ ሕጎች የያዘ የአቋም መግለጫ እንዲያዘጋጅ እርዱት፤ ለፖርኖግራፊ ከተጋለጠ ምን ማድረግ እንዳለበትና ይህን እርምጃ የሚወስደው ለምን እንደሆነ በአቋም መግለጫው ላይ እንዲጽፍ አድርጉ። ሆን ብሎ ፖርኖግራፊ መመልከት ያለውንም መዘዝ በጽሑፍ እንዲያሰፍር አድርጉ፤ እንዲህ ያለው ልማድ ለራሱ ያለው አክብሮት እንዲቀንስ ሊያደርግ፣ የወላጆቹን አመኔታ ሊያሳጣው፣ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ሊያበላሽበትና ሌሎች ብዙ መዘዞች ሊያስከትልበት ይችላል። c

 “ልጆች ከፍ እያሉ ሲሄዱ፣ ለቅጽበታዊ ደስታ ሲሉ ለፈተና እጅ መስጠታቸው ምን ዓይነት ዘላቂ ጉዳት እንደሚያስከትልባቸው አሻግረው እንዲያዩ እርዷቸው።”—ሎሬታ

 “ልጆቻችን ፖርኖግራፊ ስላለው አደጋ ብቻ ሳይሆን ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማው ካወቁ ፈተናውን መቋቋም ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል።”—ዴቪድ

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጥበብ . . . ጥበቃ ታስገኛለች።”—መክብብ 7:12

 አዘውትራችሁ ተነጋገሩ። ለማመን ሊከብዳችሁ ቢችልም ልጆች ፖርኖግራፊን ጨምሮ ስለ ፆታ ጉዳይ ከወላጆቻቸው ጋር ማውራት ይፈልጋሉ። “ልጆች የሚፈልጉት ወላጆቻቸው ገና ከትንሽነታቸው አንስቶ ስለዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ እንዲያነጋግሯቸው ነው” በማለት በእንግሊዝ የልጆች ኮሚሽነር የሆኑት የተከበሩ ሬቸል ደ ሱዛ ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ልጆች ከብስለታቸው ጋር አብሮ እየጨመረ የሚሄድ ዕድሜን ያገናዘበ ውይይት ማድረግ ይፈልጋሉ።”

 “ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ ፈጽሞ የማያነሱልኝ አንዳንድ ጉዳዮች ነበሩ። በግልጽና በነፃነት ማውራት ብንችል ደስ ይለኝ ነበር። አሁን እናት ስለሆንኩ ከልጆቼ ጋር ስለ ፆታ ጉዳይ በተደጋጋሚና ዘና ባለ መንፈስ ለማውራት የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።”—ፍላቪያ

 ልጃችሁ ፖርኖግራፊ እንደተመለከተ ካወቃችሁ

 ተረጋጉ። ልጃችሁ ፖርኖግራፊ እንደተመለከተ፣ እንዳዳመጠ ወይም እንዳነበበ ካወቃችሁ የምትሰጡትን ምላሽ ለመቆጣጠር ጥረት አድርጉ። እሱም ቢሆን በተፈጠረው ነገር ምክንያት አዝኖ፣ ደንግጦ ወይም የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ተበሳጭታችሁ ምላሽ መስጠታችሁ የባሰ እንዲከፋውና ወደፊትም ስለዚህ ጉዳይ እናንተን ማነጋገር እንዲከብደው ሊያደርግ ይችላል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፤ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰውም የተረጋጋ ነው።”—ምሳሌ 17:27

 ሙሉ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። ፈጥናችሁ ድምዳሜ ላይ ከመድረስ ይልቅ ልጃችሁ ለፖርኖግራፊ የተጋለጠው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ የሚረዷችሁን ጥያቄዎች ጠይቁት። ለምሳሌ ምስሉን የሆነ ሰው ልኮለት ነው ወይስ በራሱ ነው ያገኘው? አንዴ ብቻ ያጋጠመ ነገር ነው ወይስ ከዚህ በፊትም ፖርኖግራፊ ተመልክቶ ያውቃል? እየተጠቀመበት የነበረው መሣሪያ ላይ፣ የሚደርሱትን መረጃዎች ለመገደብ የሚረዳው ገጽታ በርቷል? ከሆነ ልጃችሁ ይህ ገጽታ እያለም ፖርኖግራፊ ለማየት የሚያስችል የሆነ ዘዴ ተጠቅሞ ይሆን? ግባችሁ ልጃችሁን እንደ መርማሪ ፖሊስ በጥያቄ ማፋጠጥ ሳይሆን ሐሳቡን እንዲገልጽ ማበረታታት እንደሆነ አስታውሱ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ቀድቶ ያወጣዋል።”—ምሳሌ 20:5

 እርምጃ ውሰዱ። ለምሳሌ ልጃችሁ ፖርኖግራፊ የተመለከተው ድንገት ብቅ ብሎበት ከሆነ ወደ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያው የሚመጡትን መረጃዎች ለመቆጣጠር በሚያስችሉት ገጽታዎች ላይ ማስተካከያ ማድረግ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል።

 ፖርኖግራፊ የተመለከተው ራሱ ፈልጎ ከሆነ ፍቅራዊ ሆኖም ጠንከር ያለ ተግሣጽ ስጡት። እንደ ኢዮብ 31:1፣ መዝሙር 97:10 እና መዝሙር 101:3 ባሉ ጥቅሶች ላይ እንዲያመዛዝን በማድረግ ልጃችሁ ፖርኖግራፊ ላለመመልከት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያጠናክር እርዱት። d የሚያደርገውን ለውጥ ለመከታተልና እሱን መርዳት የምትችሉበት ተጨማሪ መንገድ ይኖር እንደሆነ ለማወቅ በየሳምንቱ እንደምታነጋግሩት አሳውቁት።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።”—ኤፌሶን 6:4

a በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሴቶችም ይሠራሉ።

b ዕድሜውን ባገናዘበ መልኩ ልጃችሁን ስለ ፆታ ማነጋገር የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ፆታ ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።

c በአቋም መግለጫው ላይ ምን ነገሮችን ማካተት እንደሚቻል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ፖርኖግራፊ ለመመልከት እንዳትፈተን ምን ማድረግ ትችላለህ?” የሚለውን የመልመጃ ሣጥን ተመልከቱ።

dፖርኖግራፊ መመልከት የሌለብህ ለምንድን ነው?” የሚለውንም ርዕስ ልትወያዩበት ትችላላችሁ።