በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ንባብ ለልጆች አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?—ክፍል 2፦ ስክሪን ወይስ ወረቀት?

ንባብ ለልጆች አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?—ክፍል 2፦ ስክሪን ወይስ ወረቀት?

 ልጃችሁ ማንበብ የሚመርጠው ምን ላይ ነው? ወረቀት ላይ ወይስ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ?

 ብዙ ልጆች ማንበብ የሚመርጡት ስክሪን ላይ ነው። ዶክተር ጂን ትዌንጂ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የአሁኑ ትውልድ የለመደው አንድ ሊንክ ብቻ ጠቅ አድርጎ ወይም ስክሪኑን ወደ ላይና ወደ ታች በማድረግ በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ የፈለገው ገጽ ጋ መሄድ ነው፤ መጽሐፍ እያገላበጥክ አንብብ ቢባል ግን አሰልቺ ይሆንበታል።” a

 በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ተጠቅሞ ማንበብ ጥቅሞች እንዳሉት አይካድም። የ20 ዓመቱ ጆን እንዲህ ብሏል፦ “ተማሪ እያለሁ፣ የትምህርት መጽሐፎቻችንን የምናነበው በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ ነበር። ይህም ‘ፈልግ’ የሚለው ሣጥን ላይ ሄጄ የፈለግኩትን ቃል በማስገባት የምፈልገውን መረጃ ወዲያውኑ እንዳገኝ ያስችለኛል።”

 የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ የሚያነቡ ሰዎች በቀላሉ የሚያገኟቸው ሌሎች ጥቅሞችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዴ ክሊክ ወይም ጠቅ በማድረግ ብቻ የፈለጉትን ቃል ፍቺ ማንበብ፣ ኦዲዮ ማጫወት ወይም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ቪዲዮ ማየት ይችላሉ፤ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ወደሚያገኙበት ቦታ የሚመራቸው ሊንክም ያገኛሉ። ይህ ሲባል ታዲያ፣ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ማንበብ ወረቀት ላይ ከማንበብ ይሻላል ማለት ነው?

 አንዳንዶች ጠለቅ ያለ ጥናት ማድረግ ሲፈልጉ ወረቀት ላይ ማንበብ ይመርጣሉ። ለምን?

  •   ትኩረት ለመሰብሰብ ይረዳል። ናታን የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ስክሪን ላይ ሳነብ፣ በመሃል ብቅ የሚሉ ማስታወቂያዎችና መልእክቶች ይረብሹኛል፤ ብዙውን ጊዜ ትኩረቴን ይከፋፍሉታል።”

     የ20 ዓመቷ ካረንም ይህ ተፈታታኝ ሆኖባታል። “ስልኬ ላይ ወይም ታብሌቴ ላይ ሳነብ፣ በመሃል ሌላ አፕሊኬሽን ለመክፈት ወይም ጌም ለመጫወት እፈተናለሁ” ብላለች።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ [ተጠቀሙበት]።”—ቆላስይስ 4:5

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጃችሁ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ ሲያነብ ወይም ሲያጠና ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን እንቢ ለማለት ቆራጥነቱ አለው? ልጃችሁ ይህ ድክመት ካለበት፣ ትኩረቱን መሰብሰብን እንዲማር ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው?

     ጠቃሚ ምክር፦ ልጃችሁን እንዲህ ብላችሁ አስረዱት፦ ‘ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን ካስተናገድክ፣ የቤት ሥራህ የሚፈጅብህን ጊዜ ከማራዘም ውጪ የምታገኘው ጥቅም የለም፤ ትኩረትህን ሰብስበህ ቶሎ ከጨረስክ ግን ሌላ የምትፈልገውን ነገር ለማድረግ ጊዜ ታገኛለህ።’

  •   የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት ይረዳል። ቢ ዘ ፓረንት ፕሊስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “በብዙ ሙከራዎች እንደተረጋገጠው፣ ሰዎች ስክሪን ላይ ከሚያነቡ ይልቅ ወረቀት ላይ ሲያነቡ ከንባቡ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት ይችላሉ።”

     ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሰዎች ስክሪን ላይ ሲያነቡ ገረፍ ገረፍ አድርገው ያልፉታል እንጂ ሐሳቡን ትኩረት ሰጥተው አያስቡበትም። ኒኮላስ ካር የተባሉ ደራሲ እንዲህ ብለዋል፦ “ኢንተርኔት ላይ ስንሆን፣ ገጹን አንዴ ገረፍ አድርገን በማየት የምንፈልገውን መረጃ በቅጽበት ማግኘት እንፈልጋለን።” b

     እርግጥ ነው፣ ገረፍ ገረፍ እያደረጉ ማንበብ ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ችግሩ ግን፣ ኒኮላስ ካር እንደተናገሩት “ሁሉንም ነገር በዚህ መንገድ የማንበብ ልማድ እየተጠናወተን” መሆኑ ነው። ታዲያ የልጃችሁ የንባብ ልማድስ እንዲህ ዓይነት ይሆን? አንድ ነገር በሚያነብበት ወቅት ትርጉሙን እንኳ ሳያገናዝብ አንብቦ ይጨርሳል?

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ባለህ ነገር ሁሉ ማስተዋልን ለማግኘት ጥረት አድርግ።”—ምሳሌ 4:7

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጃችሁ ወረቀት ላይም ሆነ ስክሪን ላይ አንድን ጉዳይ በጥልቀት ማጥናትን እንዲማር ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው?

     ጠቃሚ ምክር፦ ምክንያታዊ ሁኑ። ዋናው ነገር፣ ልጃችሁ ምን ላይ ያነባል የሚለው አይደለም። ሁለቱም የራሳቸው ጥቅሞች አሏቸው። በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ተጠቅመን ስናነብም ጠለቅ ያለ ጥናት ለማድረግ የሚያግዙ አንዳንድ ገጽታዎች ልናገኝ እንችላለን። እንግዲያው ስለ ሁለቱም የማንበቢያ መንገዶች ከልጆቻችሁ ጋር ስትነጋገሩ ጥቅማቸውንም ሆነ ጉዳታቸውን በምክንያታዊነት አስረዷቸው። ሁኔታው ከልጅ ልጅ እንደሚለያይም አትርሱ።

  •   ለማስታወስ ይረዳል። ፌሪስ ጄበር፣ የወረቀትና የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ንባብን በማነጻጸር ሳይንቲፊክ አሜሪካን ላይ አንድ ርዕስ አውጥቶ ነበር፤ በንጽጽር ሲታይ፣ ስክሪን ላይ ማንበብ “አእምሯችን ይበልጥ እንዲዝል ያደርጋል፤ . . . በመሆኑም ያነበብነውን ነገር ማስታወስ እንቸገራለን” በማለት ጽፏል።

     ለምሳሌ ያህል፣ በወረቀት ላይ የታተመ መጽሐፍ ስናነብ አንድን ሐሳብ ያነበብንበት ገጽና ቦታው አእምሯችን ላይ በደንብ ይሣላል። ሌላ ጊዜ ያንን ሐሳብ ብንፈልግ የቱ ጋ እንደምናገኘው እናስታውሳለን።

     በተጨማሪም ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ ወረቀት ላይ የሚያነቡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ መረጃው ወደ አእምሯቸው ጠልቆ ይገባል። መጀመሪያም ያነበቡት በጥልቀት ስለሆነ ለማስታወስ አይቸገሩም።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ።”—ምሳሌ 3:21

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጃችሁ ያነበበውን ወይም ያጠናውን ነገር መረዳትም ሆነ ማስታወስ ይቸገራል? ከሆነ የጥናት ልማዱን እንዲያሻሽል ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው? ምናልባት ወረቀት ላይ ቢያነብ የተሻለ ይሆን?

     ጠቃሚ ምክር፦ ልጄ ማንበብ የሚመርጠው ምን ላይ ነው የሚለውን ሳይሆን ለትምህርቱ እየጠቀመው ያለው የቱ ነው የሚለውን አስቡ። አንዳንድ ሰዎች፣ ስክሪን ላይ ሲሆን በአንዴ ብዙ ነገር እንደሚያነቡ ሲያወሩ ሰምታችሁ ከሆነ ሐሳቡ የተጋነነ ሊሆን እንደሚችል አትርሱ።

a አይጄን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

b ዘ ሻሎውስ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።