በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ሮም 5:8—‘ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ሞቶልናል’

ሮም 5:8—‘ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ሞቶልናል’

 “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።”—ሮም 5:8 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል።”—ሮም 5:8 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የሮም 5:8 ትርጉም

 ይሖዋ a አምላክ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች እንዲሞት በማድረግ ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅር አሳይቷል። (ዮሐንስ 3:16) ሰዎች ኃጢአተኛ ስለሆኑ አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ማስማማት ይከብዳቸዋል። (ቆላስይስ 1:21, 22) ሆኖም አምላክ “በልጁ ሞት አማካኝነት” ከእሱ ጋር መታረቅ የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። (ሮም 5:10) በዚህም የተነሳ አሁን ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት፣ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንችላለን።—ሮም 5:11፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10

የሮም 5:8 አውድ

 ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የጻፈው በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ነው። በሮም ምዕራፍ 5 ላይ ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በተስፋቸው የሚደሰቱበትንና ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ የሚሆኑበትን ምክንያት አብራርቷል። (ሮም 5:1, 2) ተስፋው አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት በገለጠው ታላቅ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ስለሆነ “ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አይዳርገንም።” (ሮም 5:5, 6) ኢየሱስ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም በተለየ መልኩ አምላክን ሙሉ በሙሉ ታዟል። (ሮም 5:19) የአዳም አለመታዘዝ በዘሮቹ ላይ ኃጢአትና ሞት አስከትሏል። (ሮም 5:12) በተቃራኒው ግን ኢየሱስ አምላክን ሙሉ በሙሉ ስለታዘዘና ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ስለሰጠ፣ ታዛዥ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበት አጋጣሚ ከፍቷል።—ሮም 5:21

a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18