በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ዘፍጥረት 1:1—“በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ”

ዘፍጥረት 1:1—“በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ”

 “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።”—ዘፍጥረት 1:1 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።”—ዘፍጥረት 1:1 የ1954 ትርጉም

የዘፍጥረት 1:1 ትርጉም

 የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ሐሳብ የሆነው ይህ ጥቅስ ሁለት ወሳኝ እውነቶችን ይዟል። አንደኛ ‘ሰማያትና ምድር’ (ማለትም ግዑዙ ጽንፈ ዓለም) መጀመሪያ እንዳላቸው ይጠቁማል። ሁለተኛ ‘ሰማያትና ምድር’ የተፈጠሩት በአምላክ እንደሆነ ይገልጻል።—ራእይ 4:11

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ጽንፈ ዓለምን የፈጠረው ከምን ያህል ጊዜ በፊት እንደሆነ አይናገርም፤ ጽንፈ ዓለም የተፈጠረው እንዴት እንደሆነም አይገልጽም። ሆኖም አምላክ ‘ገደብ በሌለው ብርቱ ጉልበቱና በሚያስደምመው ኃይሉ’ አማካኝነት ጽንፈ ዓለምን እንደፈጠረ ይናገራል።—ኢሳይያስ 40:26

 “ፈጠረ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ አምላክ ከሚያከናውናቸው ነገሮች ጋር ብቻ በተያያዘ የሚሠራበት ቃል ነው። a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈጣሪ እንደሆነ የተገለጸው ይሖዋ b አምላክ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 42:5፤ 45:18

የዘፍጥረት 1:1 አውድ

 የዘፍጥረት መጽሐፍ መጀመሪያ የሆነው ይህ ጥቅስ በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2 ላይ የሚገኘውን የፍጥረት ዘገባ ያስተዋውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት 1:1 እስከ 2:4 ላይ አምላክ ምድርን እንዲሁም የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ጨምሮ በውስጧ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ደረጃ በደረጃ የፈጠረው እንዴት እንደሆነ አጠር አድርጎ ይገልጻል። ይህን ጠቅለል ያለ መረጃ ካቀረበ በኋላ ስለ መጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት አፈጣጠር ይበልጥ በዝርዝር ይናገራል።—ዘፍጥረት 2:7-25

 ዘፍጥረት አምላክ የፍጥረት ሥራውን ያከናወነው በስድስት “ቀናት” ውስጥ እንደሆነ ይናገራል። እነዚህ ቀናት ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ያላቸውን ቀናት ሳይሆን እያንዳንዳቸው በውል ያልተጠቀሰ ርዝማኔ ያላቸውን የጊዜ ክፍልፋዮች የሚያመለክቱ ናቸው። ደግሞም “ቀን” የሚለው ቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ካለው ቀን በተጨማሪ ሌሎች የጊዜ ርዝማኔዎችን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ዘፍጥረት 2:4 ላይ “ቀን” የሚለው ቃል “ጊዜ” ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ለማስተላለፍ የተሠራበት ሲሆን ጥቅሱ በስድስት ቀናት ውስጥ የተከናወኑትን የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች በሙሉ ጠቅለል አድርጎ በአንድ “ቀን” ውስጥ እንደተከናወኑ ይገልጻል።

ሰዎች ስለ ዘፍጥረት 1:1 ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ አምላክ ግዑዙን ጽንፈ ዓለም የፈጠረው ከተወሰኑ ሺህ ዓመታት በፊት ነው።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ጽንፈ ዓለም የተፈጠረው መቼ እንደሆነ አይናገርም። በዘፍጥረት 1:1 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዓመታት ዕድሜ እንዳለው ከሚሰጡት ሐሳብ ጋር አይጋጭም። c

 የተሳሳተ ግንዛቤ፦ በዘፍጥረት 1:1 ላይ የገባው “አምላክ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የተቀመጠው በብዙ ቁጥር ስለሆነ ጥቅሱ አምላክ ሥላሴ እንደሆነ ይጠቁማል።

 እውነታው፦ “አምላክ” የሚለው የማዕረግ ስም ኤሎሂም ከሚለው በብዙ ቁጥር የተቀመጠ የዕብራይስጥ ቃል የተተረጎመ ሲሆን ይህ የዕብራይስጥ ቃል ብዛትን ሳይሆን ግርማዊነትን ወይም ክብርን የሚያመለክት ነው። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ የተባለው ጽሑፍ እንደገለጸው በዘፍጥረት 1:1 ላይ የተሠራበት በብዙ ቁጥር የተቀመጠው ኤሎሂም የሚለው ቃል “ሁሌም አብሮ የሚመጣው ከነጠላ ግስ ጋር ነው፤ ይህም ነገሥታት ራሳቸውን እኛ ብለው እንደሚጠሩ ሁሉ ኤሎሂም የሚለው ቃልም ብዙ ቁጥርን ሳይሆን አክብሮትን የሚያመለክት እንደሆነ ይጠቁማል።”—ሁለተኛው እትም፣ ጥራዝ 6፣ ገጽ 272

ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 አንብብ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግርጌ ማስታወሻዎቹንና ማጣቀሻዎቹን ተመልከት።

a ሆልማን ክሪስቲያን ስታንዳርድ ባይብል የተባለው ለጥናት የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ቃል አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “‘መፍጠር’ የሚል ትርጉም ያለው ባራ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል አድራጊ ግስ ሆኖ በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰዎች ከሚያከናውኑት ነገር ጋር በተያያዘ ተሠርቶበት አያውቅም። በመሆኑም ባራ የሚለው ግስ አምላክ ያከናወነውን ነገር ብቻ የሚያመለክት ቃል ነው።”—ገጽ 7

b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18

c ዚ ኤክስፖዚተርስ ባይብል ኮሜንታሪ የተባለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንታኔ የሚሰጥ ጽሑፍ “በመጀመሪያ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ አገላለጽ ስለሚሸፍነው ጊዜ ሲናገር “ይህ አገላለጽ ስለ ጊዜው ርዝማኔ ምንም የሚጠቁመው ነገር የለም” ብሏል።—ተሻሽሎ የወጣው እትም፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 51