በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

1 ቆሮንቶስ 10:13—“እግዚአብሔር ታማኝ ነው”

1 ቆሮንቶስ 10:13—“እግዚአብሔር ታማኝ ነው”

 “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም። ይሁንና አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የ1 ቆሮንቶስ 10:13 ትርጉም

 ይህ ጥቅስ አምላክን እንድንወደው የሚያደርገንን አንድ ባሕርይ ይገልጻል፤ ይህም ታማኝነቱ ነው። እሱን በታማኝነት የሚያገለግሉት ሰዎች በችግራቸው እንደሚደርስላቸው መተማመን ይችላሉ፤ በተለይ የሕይወት ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸው ወይም የተሳሳተ ነገር ለማድረግ ሲፈተኑ።

 “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም።” የአምላክ አገልጋዮች እሱን የሚያሳዝነውን ነገር ለማድረግ ይፈተኑ ይሆናል። እንዲህ ያሉት ፈተናዎች ከባድ ቢሆኑም ያልተለመዱ ወይም እንግዳ አይደሉም፤ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸው ነገሮች ናቸው። በመሆኑም የአምላክ አገልጋዮች፣ እነሱም እንዲህ ያሉትን ፈተናዎች መቋቋም እንደሚችሉ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።

 “አምላክ ታማኝ ነው።” ይሖዋ a እምነት የሚጣልበት አምላክ ነው። የሚወዱትን፣ በታማኝነት የሚያገለግሉትንና የሚታዘዙትን ሰዎች ፈጽሞ እንደማይተው የገባውን ቃል ያልጠበቀበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም። (ዘዳግም 7:9፤ መዝሙር 9:10፤ 37:28) ስለዚህ አገልጋዮቹ በዚህ ጥቅስ ላይ ቃል የገባቸውን ሁለት ነገሮችም እንደሚያደርግ መተማመን ይችላሉ።

 “ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም።” አምላክ ፈተናዎች በጣም ከባድ ከመሆናቸው የተነሳ ልንቋቋማቸው ከምንችለው በላይ እንዲሆኑ አይፈቅድም፤ በዚህም ታማኝነቱን ያሳየናል። እያንዳንዱ አገልጋዩ አቅሙ ምን ያህል እንደሆነ ያውቃል።—መዝሙር 94:14

 “ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።” አምላክ ፈተናውን ሊያስወግድልን ይችላል፤ ካልሆነም ጸንተን ለማለፍ የሚያስፈልገንን ነገር ይሰጠናል። ለምሳሌ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይመራናል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ያጽናናናል እንዲሁም በእምነት ባልንጀሮቻችን ተጠቅሞ የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል።—ዮሐንስ 14:26፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ቆላስይስ 4:11

የ1 ቆሮንቶስ 10:13 አውድ

 ይህ ጥቅስ የሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ ላሉ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ነው። በዚህ ምዕራፍ ላይ ጳውሎስ የጥንት እስራኤላውያንን ታሪክ በማንሳት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እንደሚሆናቸው ተናገረ። (1 ቆሮንቶስ 10:11) ጳውሎስ እስራኤላውያን ያጋጠሟቸውን የተለያዩ ፈተናዎች ዘረዘረ፤ ከእነዚህም መካከል ጣዖት አምልኮና የፆታ ብልግና ይገኙበታል። (1 ቆሮንቶስ 10:6-10) አንዳንድ እስራኤላውያን ለፈተናዎቹ እጅ ሰጥተዋል። ክርስቲያኖች ከእስራኤላውያን ምሳሌ በመማር፣ ከልክ በላይ በራሳቸው ሊተማመኑ እንደማይገባ ጳውሎስ አሳሰበ፤ መቼም ቢሆን በፈተና እንደማይወድቁ ሊያስቡ አይገባም። (1 ቆሮንቶስ 10:12) ይሁንና ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ የሚገኙትን ቃላት በመጻፍ ዋስትና ሰጣቸው። የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ማንኛውንም ፈተና መወጣት ይችላሉ።

 የ1 ቆሮንቶስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።