በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጥምቁ ዮሐንስ ማን ነው?

መጥምቁ ዮሐንስ ማን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጥምቁ ዮሐንስ የአምላክ ነቢይ ነው። (ሉቃስ 1:76) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረ ሰው ነው፤ የተወለደውም ክርስቶስ ከመወለዱ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው። አምላክ ለመሲሑ ወይም ለክርስቶስ መንገድ እንዲያዘጋጅ ተልእኮ ሰጥቶታል። ዮሐንስ የአምላክን መልእክት ለአይሁዳውያን ወገኖቹ በመስበክና ልባቸው ወደ አምላክ እንዲመለስ በማድረግ ይህን ተልእኮውን ተወጥቷል።—ማርቆስ 1:1-4፤ ሉቃስ 1:13, 16, 17

 የዮሐንስ መልእክት፣ ቅን ልብ ያላቸው አድማጮቹ የናዝሬቱ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን እንዲያውቁ ረድቷቸዋል። (ማቴዎስ 11:10) ዮሐንስ አድማጮቹን ከኃጢአታቸው ንስሐ እንዲገቡና የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት እንዲጠመቁ አሳስቧቸዋል። (ሉቃስ 3:3-6) ዮሐንስ ብዙ ሰዎችን ስላጠመቀ “መጥምቁ” ወይም “አጥማቂው” ተብሎ ተጠርቷል። ካከናወናቸው ጥምቀቶች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የኢየሱስ ጥምቀት a ነው።—ማርቆስ 1:9

በዚህ ርዕስ ውስጥ፦

 መጥምቁ ዮሐንስን ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?

 የሚያከናውነው ሥራ በትንቢት ተነግሯል፦ ዮሐንስ ያከናወነው የስብከት ሥራ የይሖዋን መልእክተኛ በተመለከተ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። (ሚልክያስ 3:1፤ ማቴዎስ 3:1-3) ‘ሰዎችን ለይሖዋ እንደሚያዘጋጅ’ አስቀድሞ የተነገረለት ሰው እሱ መሆኑን አሳይቷል፤ ይህን ያደረገው አይሁዳውያን ወገኖቹ የይሖዋ አምላክ ዋነኛ ወኪል የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን መልእክት እንዲቀበሉ መንገድ በማዘጋጀት ነው።—ሉቃስ 1:17

 የሚታወስበት ታሪክ፦ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከሴት ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ዝቅተኛ የሆነው እንኳ ይበልጠዋል።” (ማቴዎስ 11:11) ዮሐንስ ነቢይ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት “መልእክተኛ” በመሆኑ ከእሱ በፊት ከተነሱት የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ ይበልጣል ሊባል ይችላል። ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ዮሐንስ በሰማይ በሚቋቋመው መንግሥት ነገሥታት ከሚሆኑት መካከል እንደማይሆንም ያሳያል። b ይህ ታማኝ ነቢይ የሞተው ክርስቶስ በሰማይ ሕይወት ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ከመክፈቱ በፊት ነው። (ዕብራውያን 10:19, 20) ይሁንና ዮሐንስ፣ ወደፊት ምድር ላይ ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ከሚያገኙት የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች አንዱ ይሆናል።—መዝሙር 37:29፤ ሉቃስ 23:43

 የመጥምቁ ዮሐንስ ወላጆች እነማን ናቸው?

 የዮሐንስ ወላጆች፣ ዘካርያስ እና ኤልሳቤጥ የተባሉ ባልና ሚስት ናቸው። ዘካርያስ አይሁዳዊ ካህን ነው። ዮሐንስ የተወለደው በተአምር ነው፤ ምክንያቱም እናቱ መሃን ነበረች። በዚያ ላይ እሷና ዘካርያስ “በዕድሜ የገፉ ነበሩ።”—ሉቃስ 1:5-7, 13

 መጥምቁ ዮሐንስን ያስገደለው ማን ነው?

 ንጉሥ ሄሮድስ አንቲጳስ የዮሐንስን ራስ አስቆርጦታል። ዮሐንስን እንዲገድል ያነሳሳችው ሚስቱ ሄሮድያዳ ነች። ይህች ሴት ዮሐንስን ትጠላው ነበር፤ ምክንያቱም አይሁዳዊ እንደሆነ የሚናገረው ሄሮድስ ከሄሮድያዳ ጋር የመሠረተው ጋብቻ ከአይሁዳውያን ሕግ ጋር እንደሚጋጭ ዮሐንስ ይነግረው ነበር።—ማቴዎስ 14:1-12፤ ማርቆስ 6:16-19

 መጥምቁ ዮሐንስ እና ኢየሱስ ተቀናቃኝ ናቸው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ተቀናቃኝ እንደነበሩ የሚጠቁም ምንም ሐሳብ የለውም። (ዮሐንስ 3:25-30) እንዲያውም ዮሐንስ ተልእኮው ለመሲሑ መንገድ ማዘጋጀት እንጂ ከእሱ ጋር መፎካከር እንዳልሆነ በይፋ ተናግሯል። ዮሐንስ “እኔ በውኃ እያጠመቅኩ የመጣሁበት ምክንያት . . . እሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው” ብሏል። አክሎም “እሱም የአምላክ ልጅ [ነው]” በማለት መሥክሯል። (ዮሐንስ 1:26-34) በመሆኑም ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በአገልግሎቱ ያገኘውን ስኬት ሲሰማ በጣም ተደስቷል።

a ኢየሱስ “ምንም ኃጢአት አልሠራም።” (1 ጴጥሮስ 2:21, 22) በመሆኑም ኢየሱስ የተጠመቀው ንስሐ መግባቱን ለማሳየት ሳይሆን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን እንዳቀረበ ለማሳየት ነው። የአምላክ ፈቃድ ሕይወቱን ለእኛ መስጠትንም ይጨምራል።—ዕብራውያን 10:7-10

bወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።