በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ወይም ‘የመጨረሻው ዘመን’ ምልክት ምንድን ነው?

‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ወይም ‘የመጨረሻው ዘመን’ ምልክት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 “የዚህ [አሁን ያለንበት] ሥርዓት መደምደሚያ” ወይም “የዓለም መጨረሻ” ተለይቶ የሚታወቅባቸው ክንውኖችና ሁኔታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተገልጸዋል፤ በሰዎች ባሕርይ ላይ የሚታየውን ለውጥም መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማቴዎስ 24:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ እንዲሁም “የፍጻሜ ዘመን” ወይም ‘የመጨረሻው ዘመን’ ብሎ ይጠራዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ዳንኤል 8:19 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ስለ “መጨረሻዎቹ ቀናት” የተነገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች

 መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻዎቹን ቀናት ለይቶ የሚያሳውቀውን “ምልክት” አስቀድሞ ነግሮናል፤ ይህ ምልክት በተመሳሳይ ጊዜ የሚፈጸሙ ብዙ ክስተቶችን ያካተተ ነው። (ሉቃስ 21:7) ከእነዚህ ክንውኖች አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት፦

 በብዙ ቦታዎች ጦርነት ይነሳል። ኢየሱስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል” ሲል አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7) በተመሳሳይም ራእይ 6:4 ምሳሌያዊ ትርጉም ስላለው አንድ ጋላቢ ይናገራል፤ ይህ ጋላቢ ጦርነትን የሚያመለክት ሲሆን “ሰላምን ከምድር [እንደሚወስድ]” ተነግሯል።

 ረሃብ ይከሰታል። ኢየሱስ “የምግብ እጥረት . . . ይከሰታል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7) በራእይ መጽሐፍ ላይ ከተገለጹት ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ጋላቢዎች አንዱ ረሃብን ያመለክታል። ይህም በብዙ ቦታዎች ረሃብ እንደሚከሰት ይጠቁማል።—ራእይ 6:5, 6

 ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ። ኢየሱስ “በተለያየ ስፍራ . . . የምድር ነውጥ ይከሰታል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:7፤ ሉቃስ 21:11) በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱት እነዚህ ታላላቅ የምድር ነውጦች ታይቶ በማይታወቅ መጠን ብዙዎችን ለመከራና ለሞት ይዳርጋሉ።

 ወረርሽኝ ይቀሰቀሳል። ኢየሱስ “ቸነፈር” እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል፤ በሌላ አባባል ‘በበሽታ ብዙ ሕዝብ ያልቃል።’—ሉቃስ 21:11 ሕያው ቃል

 ወንጀል ይበዛል። እርግጥ ነው፣ ወንጀል ከጥንትም ጀምሮ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንደተናገረው በመጨረሻዎቹ ቀናት “ክፋት እየበዛ [ይሄዳል]።”—ማቴዎስ 24:12

 ሰዎች ምድርን ያበላሻሉ። ራእይ 11:18 የሰው ልጆች ‘ምድርን እንደሚያጠፏት’ ይናገራል። ይህን የሚያደርጉት በተለያዩ መንገዶች ነው፤ አንዳቸው በሌላው ላይ የሚፈጽሙት ግፍና ዓመፅ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ በተፈጥሮ ላይም ውድመት ያደርሳሉ።

 የሰዎች ባሕርይ ይበላሻል። መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-4 ላይ እንደሚናገረው ሰዎች በጥቅሉ ሲታይ “የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ . . . ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ” ይሆናሉ። የሰዎች የባሕርይ ዝቅጠት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱ የተነሳ ይህ ጊዜ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ተብሏል።

 የቤተሰብ ዝምድና ይሸረሸራል። በ2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚናገረው ብዙ ሰዎች ለቤተሰባቸው “ተፈጥሯዊ ፍቅር” አይኖራቸውም፤ ልጆችም ‘ለወላጆቻቸው አይታዘዙም።’

 ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ይቀዘቅዛል። ኢየሱስ “የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:12) አብዛኞቹ ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ መናገሩ ነበር። በ2 ጢሞቴዎስ 3:4 ላይ የሚገኘው ተመሳሳይ ትንቢት ሰዎች በመጨረሻዎቹ ቀናት “ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን [እንደሚወዱ]” ይናገራል።

 ሃይማኖተኞች ግብዞች ይሆናሉ። በ2 ጢሞቴዎስ 3:5 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚናገረው ሰዎች ለታይታ ያህል ለአምላክ ያደሩ መስለው ቢታዩም በሕይወታቸው ውስጥ የእሱን ሕጎች አይከተሉም።

 ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያላቸው ግንዛቤ ይጨምራል። የዳንኤል መጽሐፍ አስቀድሞ እንደተናገረው ‘በፍጻሜው ዘመን’ የሚኖሩ ብዙዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያላቸው እውቀት ይጨምራል፤ ለምሳሌ ስለ መጨረሻው ዘመን ትንቢቶች ትክክለኛ ግንዛቤ ይኖራቸዋል።—ዳንኤል 12:4

 ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ይኖራል። ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:14

 ብዙዎች ግድየለሽና ዘባች ይሆናሉ። ኢየሱስ በትንቢት በተናገረው መሠረት በአብዛኛው ሰዎች መጨረሻው እየቀረበ መምጣቱን የሚጠቁመውን ማስረጃ ችላ ይላሉ። (ማቴዎስ 24:37-39) ከዚህም አልፎ አንዳንዶች 2 ጴጥሮስ 3:3, 4 እንደሚናገረው ማስረጃ ሲቀርብላቸው ያፌዛሉ፤ ጨርሶ ሊቀበሉትም አይፈልጉም።

 ሁሉም ትንቢቶች ይፈጸማሉ። ኢየሱስ እንደተናገረው የመጨረሻው ዘመን መድረሱ የሚታወቀው ስለዚያ ጊዜ የተነገሩት ክስተቶች በሙሉ በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ሲፈጸሙ ነው፤ ትንቢቶቹ በከፊል ወይም በአብዛኛው ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ሊፈጸሙ ይገባል።—ማቴዎስ 24:33

“በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ ነን?

 አዎ። በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት እንደሚጠቁመው የመጨረሻዎቹ ቀናት የጀመሩት በ1914 ነው፤ ይህ ዓመት አንደኛው የዓለም ጦርነት የጀመረበት ዓመት ነው። በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንዳለን የሚጠቁሙ የዓለም ሁኔታዎችን ማወቅ ከፈለግህ የሚከተለውን ቪዲዮ ተመልከት፦

 በ1914 የአምላክ መንግሥት በሰማይ መግዛት ጀመረ፤ ይህ መንግሥት ከወሰዳቸው የመጀመሪያ እርምጃዎች አንዱ ሰይጣን ዲያብሎስንና አጋንንቱን ከሰማይ ማባረርና እንቅስቃሴያቸው በምድር አካባቢ ብቻ እንዲወሰን ማድረግ ነው። (ራእይ 12:7-12) ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በግልጽ እየታየ ነው፤ የመጨረሻውን ዘመን “ለመቋቋም የሚያስቸግር” እንዲሆን ያደረገው የሰዎች የባሕርይና የአስተሳሰብ መበላሸት ይህን ይጠቁማል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

 ብዙ ሰዎች የዓለም ሁኔታ በጣም ያስጨንቃቸዋል። ማኅበረሰቡ ራሱ ወደ ከፋ ዝቅጠት እያመራ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች የሰው ልጅ እርስ በርሱ እንዳይጠፋፋ ይሰጋሉ።

 ከዚህ በተቃራኒ ግን ሌሎች በዓለም ላይ ስላሉት ሁኔታዎች መጨነቃቸው ባይቀርም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ መልካም ነገር ይታያቸዋል። የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች በሙሉ እንደሚያስወግድ ይተማመናሉ። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 21:3, 4) አምላክ ቃሉን የሚፈጽምበትን ጊዜ በትዕግሥት ይጠባበቃሉ፤ እስከዚያው ግን ኢየሱስ “እስከ መጨረሻው የጸና . . . ይድናል” በማለት የተናገራቸው ቃላት ያጽናኗቸዋል።—ማቴዎስ 24:13፤ ሚክያስ 7:7