በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለአንድ ሚሊዮን የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት

ለአንድ ሚሊዮን የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት

የይሖዋ ምሥክሮች ከ1999 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት ውስጥ በማዕከላዊ አሜሪካና a በሜክሲኮ ከ5,000 የሚበልጡ የመንግሥት አዳራሾችን ገንብተዋል። በዚያ የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን የይሖዋ ምሥክሮችና በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ ሌሎች ሰዎች በቂ መሰብሰቢያ እንዲያገኙ ከ700 በላይ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ።

ባለፉት ጊዜያት በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ጉባኤዎች የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባት ይቸገሩ ነበር። ለምሳሌ በሜክሲኮ ውስጥ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉት በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነበር። ለምን? አንዱ ምክንያት የአገሪቱ ሕግ፣ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የንብረት ባለቤት መሆን እንደማይችሉ ይደነግግ ስለነበረ ነው። በ1990ዎቹ ግን ይህ ሕግ የተለወጠ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች በርካታ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ጀመሩ። ሆኖም የመንግሥት አዳራሾቹ ግንባታ በአብዛኛው ወራት ይፈጅ ነበር።

ግንባታው ተፋጠነ

በ1999 የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድኖች፣ የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት በተደረገ አዲስ ዝግጅት ሥር ሆነው መንቀሳቀስ ጀመሩ፤ ይህም የግንባታ ሂደቱ እንዲፋጠን አድርጓል። በዚህ ዝግጅት ውስጥ ከታቀፉት መካከል ሜክሲኮና በማዕከላዊ አሜሪካ ውስጥ ያሉት ሰባት አገሮች ይገኙበታል። ከ2010 ጀምሮ፣ በሜክሲኮ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በእነዚህ አካባቢዎች የሚካሄደውን የግንባታ እንቅስቃሴ ሲቆጣጠር ቆይቷል።

የግንባታ አገልጋዮች ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የመንግሥት አዳራሾችን ሲገነቡ ለየት ያሉ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። ለምሳሌ በፓናማ፣ የግንባታ አገልጋዮቹ ወደ አንድ የግንባታ ፕሮጀክት ለመድረስ የባህር ዳርቻውን ተከትለው ለሦስት ሰዓት ገደማ በጀልባ መጓዝ ነበረባቸው። እንዲሁም ቺያፓስ በተባለችው የሜክሲኮ ግዛት፣ የግንባታ ቡድኑ ርቆ ወደሚገኝ አካባቢ የግንባታ ቁሳቁሶችን ለመውሰድ አነስተኛ አውሮፕላን መጠቀም አስፈልጎት ነበር።

አዲስ የመንግሥት አዳራሾች የሚያስገኙት ጥቅም

የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ በአካባቢያቸው የመንግሥት አዳራሽ እንዲገነባ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ በሆንዱራስ የሚኖር አንድ ሰው፣ በአካባቢው የመንግሥት አዳራሽ ከመገንባቱ በፊት አንዳንዶች ቦታውን የምሽት ጭፈራ ቤት ሊገነቡበት ይፈልጉ እንደነበር ተናግሯል። እሱን ግን ይህ ሐሳብ አላስደሰተውም ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ ቦታ የመንግሥት አዳራሽ ሊገነቡ እንደሆነ ሲነግሩት “እንዴት ያለ በረከት ነው!” በማለት ደስታውን ገለጸ።

በብዙ ቦታዎች፣ ሰዎች በግንባታው ላይ የሚካፈሉት ሠራተኞች ባሳዩት ትጋት በጣም ተገርመዋል። በጓቴማላ የሚኖር አንድ ሰው “በእኛ ባህል፣ ሴቶች የሚሠሩት ኩሽና ውስጥ ብቻ ነው። እዚህ ያሉት ሴቶች ግን ከወንዶቹ ጋር ተመሳሳይ ሥራ ይሠራሉ። ሴቶቹ ብረት ሲያስሩ እንዲሁም ግድግዳ ሲለስኑ ስመለከት በጣም ነው የተገረምኩት። የሚያስደንቅ ነው!” እንዲያውም በግንባታ ቦታው አቅራቢያ ካሉት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ለግንባታ ሠራተኞቹ የሚበላና የሚጠጣ ነገር ለመግዛት ተነሳስተዋል።

በመንግሥት አዳራሾቻችን ንድፍም የሚደነቁ በርካታ ሰዎች አሉ። በኒካራጓ የሚኖር አንድ መሐንዲስ ለአንድ ከተማ ከንቲባ፣ በዚያ የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ደረጃቸውን በጠበቁ የግንባታ ቁሳቁሶች የተገነባ ውብ ሕንፃ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲያውም በከተማው ውስጥ ከሚገኙ ሕንፃዎች ሁሉ በጥራት እንደሚበልጥ ገልጿል!

በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮችም ቢሆኑ አመቺ የአምልኮ ቦታ በማግኘታቸው እንደተደሰቱ ጥያቄ የለውም። አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ከተገነባ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይበልጥ እንደሚገኙ አስተውለዋል። በሜክሲኮ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የግንባታ አገልጋዮችን በግንባታ ሥራ ያገዙ ሲሆን አመስጋኝነታቸውን እንዲህ ሲሉ ጠቅለል አድርገው ገልጸዋል፦ “ለስሙ ግርማና ክብር የሚያመጣ የመንግሥት አዳራሽ የመገንባት መብት ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።”

a ሚርያም-ዌብስተርስ ኮሊጂየት ዲክሽነሪ—11ኛ እትም ማዕከላዊ አሜሪካ የሚለው መጠሪያ ሆንዱራስን፣ ቤሊዝን፣ ኒካራጉዋን፣ ኤል ሳልቫዶርን፣ ኮስታ ሪካን፣ ጓቴማላንና ፓናማን የሚያካትት እንደሆነ ይናገራል።