በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል?

መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል?

መልስህ ምንድን ነው?

  • ይመጣል?

  • አይመጣም?

  • ወይስ ምናልባት?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” —ራእይ 21:3, 4 አዲስ ዓለም ትርጉም

ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ጥቅም አለው?

በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሱት ችግሮች መንስኤው አምላክ እንዳልሆነ ማረጋገጫ ይሰጥሃል።—ያዕቆብ 1:13

መከራ ሲደርስብህ አምላክ እንደሚያዝንልህ ስለምታውቅ ትጽናናለህ።—ዘካርያስ 2:8

ሁሉም ዓይነት መከራ እንደሚወገድ ተስፋ እንድታደርግ ይረዳሃል።—መዝሙር 37:9-11

መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ እምነት መጣል እንችላለን?

አዎ፣ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦

  • አምላክ መከራንና ኢፍትሐዊነትን ይጠላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ ይሖዋ አምላክ በሕዝቦቹ ላይ ግፍ ሲፈጸም ምን እንደተሰማው እስቲ እንመልከት። ሕዝቡ “በሚጨቁኗቸውና በሚያንገላቷቸው ሰዎች የተነሳ ሲቃትቱ” አምላክ እንዳዘነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—መሳፍንት 2:18

    አምላክ በሌሎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎችን ይጠላል። ለምሳሌ ያህል፣ “ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች” በአምላክ ዘንድ የተጠሉ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ምሳሌ 6:16, 17

  • አምላክ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል። አንድ ሰው መከራ አጋጥሞት ‘ጭንቀትና ሥቃይ’ ሲሰማው ይሖዋም የዚህ ሰው ‘ጭንቀትና ሥቃይ’ ይሰማዋል።2 ዜና መዋዕል 6:29, 30

ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት የእያንዳንዱን ሰው መከራ በቅርቡ ያስወግዳል። (ማቴዎስ 6:9, 10) እስከዚያው ግን እሱን ከልብ የሚፈልጉ ሰዎችን በደግነት ያጽናናቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 17:27፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

ምን ይመስልሃል?

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ሮም 5:12 እና 2 ጴጥሮስ 3:9 ላይ ይገኛል።