በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

የጉርምስና ወቅት በተወጠረ ገመድ ላይ ከመሄድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እያንዳንዱ እርምጃ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ አስፈሪ ሊሆን ይችላል። ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁ እንዲህ ባለ “ገመድ” ላይ እንዳይሄዱ ለማድረግ አንዳንድ ጊዜ ትመኙ ይሆናል። ይህን ማድረግ እንደማትችሉ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሚዛንን ለመጠበቅ እንደሚረዳ ዘንግ ልትሆኑላቸው ትችላላችሁ። ልጆቻችሁ ሚዛናቸውን ሳይስቱ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ እንዲሁም ይህን ዕድሜ በተሳካ ሁኔታ አልፈው ኃላፊነት የሚሰማቸው ትልልቅ ሰዎች እንዲሆኑ ከማንም በላይ ልትረዷቸው የምትችሉት እናንተ ናችሁ።

‘እንዲህ ማድረግ የመናገርን ያህል ቀላል አይደለም’ ትሉ ይሆናል። እውነታችሁን ነው። በጉርምስና ዕድሜ ላይ ስላለው ልጃችሁ ስታስቡ ‘ትናንትና እኮ ሮጦ የማይደክመውና አውርቶ የማይጠግብ አንድ ፍሬ ልጅ ነበር’ ትሉ ይሆናል፤ አሁን ግን ከእናንተ ጋር ከማውራት ይልቅ ዝምታን ይመርጣል። ሴት ልጃችሁ በሄዳችሁበት ሁሉ ካልወሰዳችሁኝ ትል የነበረችበት ጊዜ ብዙም ሩቅ አይደለም፤ ዛሬ ግን ከእናንተ ጋር በአደባባይ መታየት ገና ስታስበው እንኳ ያሳፍራታል!

ይሁንና ከጉርምስና ዕድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን እነዚህን ለውጦች መቋቋም ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ሊሰማችሁ አይገባም። ለእናንተም ሆነ ለልጃችሁ አስተማማኝ መመሪያ የሚሆን የጥበብ ምንጭ በእጃችሁ ይገኛል። ይህ የጥበብ ምንጭ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለው መጽሐፍ ልጃችሁ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንዲያገኝ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በገጽ 4 እና 5 ላይ ካለው የርዕስ ማውጫ መመልከት እንደምትችሉት መጽሐፉ የተለያዩ ጉዳዮችን ይዳስሳል። ይሁን እንጂ ይህ መጽሐፍ እውቀት በማስተላለፍ ብቻ አይወሰንም። እንደሚከተሉት ያሉ ጠቃሚ ገጽታዎችም አሉት፦

(1) መጽሐፉ አንባቢውን ያሳትፋል። በበርካታ ቦታዎች ላይ ልጃችሁ ለቀረቡለት የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥና ሐሳቡን በጽሑፍ እንዲያሰፍር ተበረታቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በገጽ 132 እና 133 ላይ የሚገኘው “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” የሚለው ሣጥን ልጃችሁ ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ አስቀድሞ እንዲያስብና እነዚህን ፈተናዎች ለመቋቋም ምን ማድረግ እንደሚችል እንዲዘጋጅ ይረዳዋል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፉ ዘጠኝ ክፍሎች ያሉት ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል መጨረሻ ላይ “የግል ማስታወሻ” የሚል ርዕስ ያለው ገጽ አለ፤ ይህ ገጽ ልጃችሁ በእያንዳንዱ ክፍል ላይ የቀረበውን ትምህርት አስመልክቶ ሐሳቡንና ስሜቱን እንዲገልጽ ያበረታታዋል።

(2) መጽሐፉ ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር በግልጽ እንዲወያዩ ያበረታታል። ለምሳሌ ያህል፣ በገጽ 63 እና 64 ላይ “ከአባባ ወይም ከእማማ ጋር ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማውራት የምችለው እንዴት ነው?” የሚል ሣጥን አለ። በተጨማሪም በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ “ምን ይመስልሃል?” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ይገኛል። በዚህ ሣጥን ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች ለክለሳ ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብ ጋር ውይይት ለማድረግም መጠቀም ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ “ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ይገኛል፤ በሣጥኑ ውስጥ የመጨረሻው ሐሳብ ወጣቶች የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር እንዲያሟሉ ይጠይቃል፦ “ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር . . .”። በዚህ መንገድ መጽሐፉ፣ ወጣቶች በተወጠረ ገመድ ላይ ከመሄድ ጋር በተመሰለው በጉርምስናቸው ወቅት ሚዛናቸውን ሳይስቱ ለመጓዝ የሚያስችላቸውን ምክር ለማግኘት ወደ ወላጆቻቸው ዘወር እንዲሉ ያበረታታቸዋል።

ጥንቃቄ ልታደርጉበት የሚገባ ነጥብ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ በመጽሐፋቸው ላይ ሐሳባቸውን በሐቀኝነት እንዲያሰፍሩ ለማበረታታት በተወሰነ መጠን ነፃነት ስጧቸው። መጽሐፋቸው ላይ ስላሰፈሯቸው ነገሮች ከጊዜ በኋላ በግልጽ ይነግሯችሁ ይሆናል።

ወላጆች፣ የዚህ መጽሐፍ የግል ቅጂ ይኑራችሁ፤ እንዲሁም መጽሐፉን በሚገባ አንብቡት። መጽሐፉን በምታነቡበት ጊዜ እናንተ በጉርምስና ዕድሜ ላይ በነበራችሁበት ወቅት ያጋጠማችሁን ችግር፣ ግራ መጋባትና ጭንቀት ለማስታወስ ሞክሩ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተሞክሯችሁን ለልጆቻችሁ አካፍሏቸው። እንዲህ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ የልባቸውን አውጥተው እንዲነግሯችሁ ያበረታታቸዋል። ስሜታቸውን ሲገልጹላችሁ አዳምጧቸው! ከእነሱ ጋር ለመግባባት ያደረጋችሁት ጥረት እንዳልተሳካ ቢሰማችሁ ተስፋ አትቁረጡ። ልጆቻችሁ የእናንተን እርዳታ እንደማይፈልጉ የሚያሳይ ነገር ቢያደርጉም እንኳ ከእኩዮቻቸው ይልቅ የወላጆቻቸውን ምክር ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ አትዘንጉ።

ለእናንተም ሆነ ለልጆቻችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ይህን መጽሐፍ ስናቀርብላችሁ በጣም ደስ ይለናል፤ ይህ መጽሐፍ ለቤተሰባችሁ በረከት እንዲሆን ጸሎታችን ነው።

አዘጋጆቹ